Saturday, 09 November 2019 13:06

የቻይናዊቱ ፍቅር እስከ ባሕር

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)


             ክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” በተሰኘ ልቦለድ ድርሰታቸው፤ የበዛብህና የሰብለ ፍቅር፣ እስከ መቃብር የዘለቀ መሆኑን አሳይተውናል፡፡ ይህ ጽሑፍ ደግም የቻይናዊቱ ሚንግ  ፍቅር፣ እስከ ባሕር እንዴት እንደዘለቀ ያሳየናል፡፡ ቀደም ሲል ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ቻይና ሄጀ በነበረበት ወቅት የጠላት መከላከያ ምሽግ የሆነውን ታላቁን የቻይና ግንብ ለመጎብኘት፣ እኔና ጓደኞቼ እድል አግኝተን  ነበር፡፡ ቦታውን ስንጎበኝ የአፍሪካ ቱሪስቶች መሪና አስተርጓሚ ሆና ትሠራ የነበረቺው ሆው  ሉዊስ (ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ፣ ጫልቱ እያሉ ይጠሯት ነበር)፤ ከቻይና ሥነ-ቃል  ተነሥታ ስለ ታማኝቱ አፍቃሪ .ስለ ሚንግ ጂያንግ፤ ስለ ባለቤቷና በታላቁ  የቻይና  ግንብ  ሥራ ስለነበረው ተሳትፎ አጫውታን ነበር፡፡ ሉዊስ እንደተረከችልን፤ ቆንጆይቱ  ሚንግ ጂያንግ፣ በቻይና ስለ ታላቁ ግንብ  ከሚነገሩ ታሪኮች ውስጥ ዐራተኛው ሥነ ተረት ተደርጎ ይታያል:: ይህ ከ 2ሺ200 ዓመት በላይ እድሜ ያለው፤ በኲዊን ሥርዎ መንግሥት ዘመን  የታወቀና በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተ  ሥነ ተረት ነው፡፡
ሥነ ተረቱ የተገኘው በብራና ላይ (ማኑስክሪፕት) በእጅ ተጽፎ ነው፡፡ ወይዘሪት ሉዊስ እንዳለቺው፤ ሚንግ በመልካም እንክብካቤ ያደገች፣ እጅግ በጣም ቆንጆ፣ ሙዚቃ የመድረስና  ግጥም የመግጠም ችሎታን የታደለችና የፈላስፋው የኮንፊሺየስ ዓይነት አስተሳሰብ የነበራት ወጣት ናት፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ከሰዓት በኋላ  ሚንግ ጂያንግ፣ በቤተሰቦቿ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የአጸድና አትክልት ቦታ ውስጥ አበቦችን ተመስጣ በመመልከት ላይ እንዳለች፣ በአጸዱ አጥር በኩል ያያት በነበረ አንድ ወጣት ስሜቷ ተሰረቀ፡፡ ወጣቱ  ዋን ጂሊያንግ እንደሚባልና ታላቁን ግንብ ይገነባ ከነበረው የመጀመሪያው ንጉሥ አምልጦ የመጣ ሠራተኛ እንደሆነ  ነገራት፡፡ በረሀብና በችግር በጣም እንደተሠቃየም ገለጸላት፡፡ ቆንጆይቱ ሚንግና ቤተሰቦቿ፣ ወጣቱ እንግዳ፣ አብሯቸው እንዲቆይ ፈቀዱለት፡፡ በእውነትም ወጣቱ የተማረና መልካም ሥነ ምግባር ያለው ሰው ነበር፡፡ ከዚያም  ቆንጆይቱ ሚንግና ወጣቱ ዋን ጂሊያንግ  በፍቅር ወደቁ፡፡ የሚንግ  ቤተሰቦች፣ ተወዳጇ ልጃቸው  ትዳር ለመመሥረት እጮኛ በማግኘቷ  በእጅጉ ተደሰቱ፡፡
ብዙም ሳይቆዩ ጋብቻ መሠረቱ፡፡ ነገር ግን በሰፈሯ በውበቷ የተነደፈ ሌላ ሰው ጋብቻዋን በምቀኝነት ተነሣሥቶ ለማደናቀፍ ስለፈለገ፣ በአካባቢው ለሚገኙ ባለሥልጣናት አቤቱታ አቀረበ፡፡ በሠርጋቸው ቀንም  የወደፊት ባለቤቷ ዋን ጂሊያንግ ተይዞ፣ በሰሜን ቻይና ታላቁ ግንብ  ወደሚገነባበት ቦታ  ተላከ፡፡ ወጣቷ ሚንግ፣ አዲሱ የትዳር አጋሯ ወደ እርሷ ይመለስላት ዘንድ ቀንም፣ ሌትም ትጠብቀው ጀመር፡፡ የበጋው ወቅት ገብቶ እስኪያልፍ  ድረስ በጉጉት ስሜት ሆና  ስለ እርሱ ብታስብና ብትጨነቅም፣ ምንም ዓይነት ቃል፤ አንዳችም መልእክት ከዋን ጂሊያንግ ሊመጣላት አልቻለም፡፡ ለብዙ ቀናት በሐሳብ ስትሰቃይ ከቆየች በኋላ በመጨረሻ፣ ክረምቱ ሲገባ፣ ለባለቤቷ የሚበረከቱ የክረምት ልብሶችን አዘጋጅታ፣ ያለበት የታላቁ ግንብ ፕሮጀክት ድረስ ሄዳ ዓይኑን ለማየት ወሰነች፡፡
ቤተሰቦቿ እንዳትሄድ ቢቃወሟትም፣ የእነርሱን ተቃውሞ ችላ ብላ ተራራዎችንና ወንዞችን እያቆራረጠች፣ ታላቁ ግንብ እስካለበት ቦታ ድረስ ተጓዘች፡፡ እዚያም ስትደርስ ወፈ ሰማያት የሆነ  የቀን ሠራተኛ በበዛበት መኻል ዋን ጂሊያንግን  ፈልጋ ለማግኘት  በማትችልበት ሁኔታ፣ ላይ ታች ትባዝን ጀመር፡፡ በመጨረሻ ስታጠያይቅ፣ ባለቤቷ  ዋን ጂሊያንግ፣ በታላቁ ግንብ ሥራ ብዙ ሥቃይና እንግልት ከደረሰበት በኋላ በዚሁ የሥራ ጫና ምክንያት  እንደሞተ አረዷት፡፡ እሪ ብላ ራስዋን ስታ መሬት ወደቀች:: ራሷን ስታውቅ ኀዘኑ ልቧን ይበላው ጀመር:: ዕንባዋም እንደ ጎርፍ እየወረደ ጩኸቷን አቀለጠችው፡፡ የት እንደተቀበረ ለማወቅ ተቸገረች፡፡
እዚያው ለሦስት ቀናት ያህል ስታለቅስ ቆይታ እስከ ታላቁ ግንብ ጫፍ ድረስ በእግርዋ ወጣች፡፡ ይሄኔ በድንገት ተአምራዊ ነገር ተፈጠረ፡፡ በሚንግ የሦስት ቀናት ለቅሶና ዕንባ ምክንያት የግንቡ 800 ማይል የሆነው ክፍል በታላቅ ፍንዳታ ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ በዚህ ሰዓትም የእርሷን ባለቤት ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ነጫጭ ዐፅሞች፣ ከድንጋይ ስብርባሪና ከአቧራ ጋር ተደባልቀው መታየት ጀመሩ፡፡ ዐፅሞቹን ስትመለከት የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ገባች፡፡ ወዲያው ጣቶቿን አደማችና፤  «ይህ የምመለከተው ባለቤቴ ከሆነ፣ ደሜ  ወደ መሬት ሰርጎና የባለቤቴን ዐፅም ሰርስሮ እንዲገባ ምኞቴ ጥልቅ ነው» ስትል  ጸለየች፡፡ የሙታን የራስ ቅሎችን ስትመለከት ለየቤተሰቦቻቸው መልእክት ለማድረስ ትችል ዘንድ ጠየቀቻቺው:: የራስ ቅሎቹም ለጥያቄዋ  በግጥም  እንዲህ ሲሉ መለሱላት፡-
በፀደይ   በክረምት እንዲሁም በበጋ፤
በቢጫማው ዐፈር በአሽዋው መሬት ላይ          ተኝተናል ባልጋ፡፡
በይ ቃል አድርሽልን  ጽንዓት ቢሆናቸው፤
ለየሚስቶቻችን ለተለየናቸው፡፡
መዝሙር አሰሚልን ለየነፍሶቻቸው፤
የእኛ መሥዋዕትነት  መድኅን ቢሆናቸው፡፡
ዋን ጂሊያንግ ሲሞት ሰውነቱ ከታላቁ ግንብ ጋር ተጣብቆ  የግንቡ አካል ሆኗል፡፡ ነፍሱ በአየር ላይ እየተቅበዘበዘች ባለቤቱን ሚንግን እንዲህ አለቻት፡- «ከመሬት ውስጥ የምገኘው እኔ አንድ  ድሃ ወታደር ለምንጊዜም አልረሳሽም፤ ከድንጋይ ክምር  ጋር ስዋደቅ ነው የወደቅሁት»:: ባለቤቱም ይህንን ስትሰማ፤ «አሁን አባትም ሆነ ምንም ዓይነት ዘመድ የለኝም፤ ባልም ልጅም የለኝም፤ የምሄድበት ቦታም የለኝም፤ የምፈልገው እንዳንተ እዚሁ መሞት ብቻ ነው፡፡»
ይህ ስለ ታላቁ የቻይና ግንብ የሚነገረው ሥነ ተረት፣ በይዘትም በቅርጽም እየተሻሻለና በጥናትና ምርምር እየዳበረ ከመምጣቱ ባሻገር በብዙ የዓለም ቋንቋዎች ተተርጉሟል:: በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግን ገና የተተረጎመ አይመስልም፡፡ የቻይና የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ የሚንግንና የዋን ጂሊያንግን ፍቅር  መነሻ አድርገው «የወጣቷ ሚንግ ያንግ የ12 ወራት አበባዎች» በሚል ሳቢና ማራኪ በሆነ መንገድ ኅብረ ዝማሬ ሠርተውላቸዋል፡፡
የመጀመሪያው ወቅት የአበባ፤ ሁለተኛው የፍቅርና የተስፋ ፤ ሦስተኛው የድንጋጤና የጥርጣሬ--እያለ እስከ አሥራ ሁለተኛው ወር ይደርሳል፡፡ ይህ ወር ለሚንግ የመከራና የጭንቀት ጊዜ ሆኖ ተሥሏል፡፡ ሚንግ ለብቻዋ ሆና «ሁሉም ቤተሰብ ከደስታ ብዛት የተነሣ  በየቤቱ ቀይ መብራት እያበራ ነው፤የጎረቤቶቼ ባለቤቶች ወደ ቤታቸው በሰላም ተመልሰው ከፍቅረኞቻቸው ጋር ተገናኝተዋል፤ የእኔ ባለቤት ብቻ ታላቁን የቻይና ግንብ እገነባለሁ ብሎ እንደወጣ ቀረብኝ፤ ዐፅሙ ከግንቡ ጋር ተላትሞ ግድግዳ ሆነ፤ ደሙ አሸዋና ሲሚንቶ  ሆኖ ግንቡን አጸናው፤» እያለች ስታለቅስ፤ ስታዝንና ስትተክዝ ትታያለች፡፡ ነፍሱ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረች በደሏን በመናገር፤ «ውድ ሚስቴ ሆይ፤ እኔ ድሀው ባለቤትሽ  ሞቼና ተቀብሬ ከመሬት በታች ብሆንም፣ ለምንጊዜም አልረሳሽም» ስትል ትሰማታለች፡፡
ወጣቷን ለከፍተኛ ኀዘንና ሰቆቃ የዳረጋት በኵይን ሥርዎ መንግሥት የመጀመሪያ የነበረው ጨካኙና አምባገነኑ ንጉሥ ነው፡፡ የመሠረተውን አዲስ መንግሥት ከጠላት ለመከላከል ሲል በርካታ የቻይና ወጣቶችን እያስገደደና እያዘዘ ታላቁን ግንብ ለማስገንባት፣ ለሕይወታቸው ሳይጨነቅ  እንደ ባሪያ  ሌትም ቀንም ያለ ዕረፍት እንዲሠሩ ያደርጋቸው ነበር፡፡ ከዚህም ተነሣ በርካታ ወጣቶች በናዳ፤ በመሬት ነውጥና በእሳት ቃጠሎ፤ በተስቦ በሽታ አልቀዋል፡፡ ጭካኔ በተሞላበት የግንባታ ሥራ ልጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ ባለቤቶቻቸውንና ልጆቻቸውን አጥተው ዕድለ-ቢስ ከሆኑ ወጣት ሴቶች ውስጥ አንዷ ሚንግ ሆነች፡፡ ቻይናውያን ለሚንግ ማስታወሻ እንዲሆን በኪንግሁዋንግ የደሴት ከተማ ቤተ መቅደስ ሠርተውላታል፡፡    
ቻይናዊው ንጉሠ ነገሥት የሞተ ባለቤቷን እያስታወሰች ስለምትጨነቀው ስለ ሚያንግ ሁኔታ በሰማ ጊዜና በእርስዋ ምክንያት ግንቡ እንደተናደ እንዳወቀ በጣም ተበሳጭቶና ተናድዶ ሊቀጣት ፈለገና  ወደ እርሱ ዘንድ እንዲያመጧት አዘዘ፡፡ ወደ እርሱ ዘንድ መጥታ ባያት ጊዜ ግን የቅጣት ክንዱን ያሳርፍባት ዘንድ አልወደደም:: ይልቁንም በውበቷ ተማረከና ሊያገባት ወሰነ:: ሚንግም ንጉሡ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ካሟላላት  ልታገባው እንደምትችል  ተስማማች:: የጠየቀቻቸው ሦስት ነገሮች፡- አንደኛ ለሟች ባለቤቷ ክብር ሲባል  ለ49 ቀናት ብሔራዊ  የኀዘን መታሰቢያ በዓል እንዲደረግለት፤ ሁለተኛ የባለቤቷ ዐፅም ተለቃቅሞና ተሰባስቦ እንዲቀበርና በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ንጉሠ ነገሥቱና ባለሥልጣናቱ እንዲገኙ፤ ሦስተኛ ለሞተው  ባለቤቷ መሥዋእት ለማቅረብ እንድትችል በወንዙ ዳር 49 ሜትር ርዝመት ያለው ሰገነት (ማማ) እንዲሠራላት  የሚያሳስብ ነው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱም ወጣቷ የጠየቀቻቸው ሦስት መሠረታዊ ነገሮች በአንድ ጊዜ እንደሚፈጸሙላት ማለላት፡፡ በመሐላው መሠረትም የጠየቀቺውን ሁሉ ፈጸመላት፡፡ ሁሉ ነገር ከተዘጋጀ በኋላ ከሰገነቱ ላይ ወጥታ ደካማነቱንና ጨካኝነቱን እያነሣች፣ ንጉሠ ነገሥቱን ኲይንን  በኃይለ ቃል ትዘልፈውና  ታወግዘው ጀመር፡፡ በመጨረሻም  ከማማው ላይ ዘልላ ወደ ባሕሩ ራስዋን በመጣል ሰምጣ ሞተች፡፡                         

Read 716 times