Print this page
Saturday, 16 November 2019 11:11

በ19ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 • የ10 ኪ.ሜ. ሩጫው ተሳታፊዎች ብዛት 564 ,890 ይደርሳል
         • ከ400 በላይ የክለብ አትሌቶች፤ ከ500 በላይ የውጭ አገር ተሳታፊዎች ከ20 የተለያዩ አገራት
         • በገቢ ማሰባሰብ 2 ሚሊዮን ብር ታቅዶ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ
         • ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ
         • 9 የሙዚቃ ጣቢያዎች፤ 2 የሻወር ቦታዎች፤ የመጀመርያ እርዳታ በየ500 ሜትር
         • ከ400 በላይ በጎ ፈቃደኞች፤ ከ150 በላይ የመጀመርያ ርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች፤ ከ200 በላይ የፅዳት ሰራተኞች


           19ኛው የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 45000 ተሳታፊዎችን  ነገ ህዳር 7 መነሻውና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ላይ በማድረግ ይካሄዳል፡፡ ከትናንት በስቲያ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በሐያት ሬጀንሲ አዲስ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተገለፀው  ባለፉት 19 ዓመታት በዓለምአቀፍ የ10 ኪ.ሜ. ሩጫ ውድድር የተሳተፉት ብዛት ዘንድሮ 564 ,890 ይደርሳል፡፡
በዋናው የአትሌቶች ውድድር ከመቸውም ጊዜ የላቀ ፉክክር  የሚጠበቅ ሲሆን፤  ከተሳታፊዎች መሀከል ከ400 በላይ የክለብ አትሌቶች እንደሚገኙበትና ከኬንያ፤ ከኤርትራ እና ከኡጋንዳ የመጡት ምርጥ አትሌቶች የውድድሩን የፉክክር ያሳድጉታል፡፡ በሌላ በኩል በ10 ኪሜትር የሩጫ ውድድሩ ላይ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ከተለያዩ 20 የውጭ አገራት የሚገቡ ሲሆን ብዙዎቹ ከእንግሊዝ በተለይም ከአውሮፓ አህጉር የሚመጡ ናቸው፡፡
ከትናንት በስቲያ በሐያት ሬጀንሲ አዲስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያዘጋጀው መግለጫ የተከፈተው በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫውን በሚያስጀምረው የዳንስ ትእይንት ነው፡፡ በየዓመቱ አዳዲስ ሁኔታዎችን የሚፈጥረው ውድድሩ ዘንድሮ ከሃሁ የዳንስ ኢንተርቴይመንት ጋር በመተባበር 45000 ተሳታፊዎቹን በጋራ የሚያንቀሳቅስ አስደሳች እና አዝናኝ የግሩፕ ዳንስ አዘጋጅቷል::  የግሩፕ ዳንሱ እንደ ቅድመ ውድድር የሰውነት ማሟሟቂያ ሆኖ ሩጫው ከመጀመሩ 10 ደቂቃ በፊት እንደሚደረግ ያስታወቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፤ ዳንሱ /እንቅስቃሴው/ በሁሉም እድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎች ሊተገብሩት የሚችሉት መሆኑን በመግለፅ፤  ተሳታፊዎች የሩጫው ቀን ከመድረሱ በፊት ልምምድ አርገው እንዲመጡ በታላቁ ሩጫ ማህበራዊ ገጾች ላይ (ፌስቡክ፤ ኢንስታግራምና ዩትዩብ) ቪዲዮውን በመልቀቅ ያለፈውን 1 ወር አስተዋውቆታል:: በነገው 19ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላይ በሃሁ ዳንስ ኢንተርቴይመንት የተዘጋጀውን የዳንስ ትእይንት ከ45ሺዎቹ ተሳታፊዎች መካከል ብዙዎቹ ከደነሱት ለሩጫው አስደናቂና ደማቅ መክፈቻ ይሆናል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስቀድሞ ልዩ ምስጋናውን ለዘንድሮ የውድድሩ ልዩ የክብር እንግዳ ኬንያዊ አትሌት ሄለን ኦብሪ ያቀረበ ሲሆን፤ በዓለም አትሌቲክስ ኬንያ ለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ለኬንያ ጥንካሬ ይፈላለጋሉ ብሏል፡፡ ሄለን ኦብሪ ዘንድሮ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን የሆነችና በ5ሺ ሜትር ከዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ተርታ እንደምትጠቀስ ይታወቃል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መግለጫ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ለመጭው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ለምታደርገው ዝግጅት ጠቃሚ ምክር ለግሷታል፡፡ የ10 ኪሜትር ሩጫውን ልዩ ውበት እና ድምቀት ሙሉውን ርቀት ጨርሶ በመሮጥ ማወቅ እንደሚቻል የተናገረው ኃይሌ፤ የውድድሩ የፉክክር እና የጥራት ደረጃን የሚፎካከር በሌላ ዓለም ክፍል አይገኝም ብሏል፡፡ ባለፉት 19 ዓመታት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ታላላቅ አትሌቶች በክብር እንግድነት ከተለያዩ የዓለም አገራት መምጣታቸውን ያስታወሰው ኃይሌ፤ በውድድሩ ላይ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች እንዲሁም የዓለም ሪከርድ ያስመዘገቡ አትሌቶች መሳተፋቸውንና ማሸነፋቸውን ጠቃቅሶ ከ500 ሜትር እስከ ማራቶን ለሚወዳደሩ አትሌቶች የሚያመች መሆኑን አስመዝግቧል፡፡ በ10 ኪሜትር ሩጫው ተሳትፈው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች  በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች፤ በለንደን፣ ቦስተንና ሌሎች ማራቶኖች እንደሚሳካላቸውም አመልክቷል፡፡
በ19ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በኩል የቀረበው መሪ ቃል “ሴቶች ልጆች በእኩል ሊታዩ፤ ሊደመጡ እና ቦታ ሊሠጣቸው ይገባል” መሆኑን በመጥቀስ በመግለጫው ላይ ባሰሙት ንግግር ያደነቁት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር  ዶክተር ሂሩት  በቀጣይ ዓመት ለወንዶች ሴቶች እኩል እድል ይስጡ ተብሎ ቢካሄድስ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  The Challenge Awards ላይ በጎዳና ላይ ሩጫ ዝግጅት ዘርፍ በአለም ቀዳሚ ሆኖ በመመረጥ ልዩ ሽልማት ማግኘቱን በአድናቆት ያነሱት ክብር ሚኒስትሯ ‹‹በራሳችሁ ጥረት በማሸነፋችሁ ጀግኖች ናችሁ፤ ታላቁ ሩጫ አገራችንን ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋት ነው፡፡ ሚኒስትር መስርያ ቤቱም ይህን እውቅና የሚሰጠውና በአርዓያነት የሚከተለው ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ አየለ በመግለጫው ላይ እንደተናገረው፤ የ10 ኪሜ ሩጫው በዓለም ከሚካሄዱ ውድድሮች በብዙ መልኩ ልዩ ገፅታ አለው፡፡ ከውድድሩ ጋር በማያያዝ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ከ1.5 ሚሊዮን ብር ላይ መሰብሰቡን ያመለከተው አቶ ኤርምያስ፤ ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት የሚሳተፉበት መሆኑ፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ካርኒቫል የሚመለከቱት መሆናቸው፤ በዋናው የአትሌቶች ውድድር የዓለማችን ፈጣን ሯጮችን የሚፎካከሩበት እና   የዓለማችን ቀርፋፋ ሯጮች ማሳተፉ ልዩ ያደርገዋል ብሏል፡፡ የ10 ኪሜትር ውድድር በሚካሄድበት የመሮጫ ጎዳናው ላይ በ9 የተለያዩ ስፍራዎች የሙዚቃ ጣቢያዎች እንደሚቆሙ፤ ሁለት የሻወር ቦታዎች እንደሚተከሉ፤ በውድድሩ መነሻ እና መድረሻ የአርኪ ውሃ እንደሚቀርብ እንዲሁም በየ500 ሜትር ርቀት የመጀመርያ ርዳታ ይሰጣል ያለው አቶ ኤርምያስ፤ 19ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አማካኝነት ለሶስት ሰዓታት የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝም ነው የገለፀው፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከውድድሩ አብይ ስፖንሰር ከሆነው ቶታል ኩባንያ ጋር ላለፉት 6 ዓመታት በአጋርነት መስራቱም ያነሳው አቶ ኤርምያስ አየለ፤ ከኩባንያው ጋር የነበራቸውን ስምምነት ከ2 ዓመታት በፊት ማደሳቸውን በ2020 እኤአ 20ኛውን እንዲሁም በ2020 እኤአ 21ኛውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በቶታል አብይ ስፖንሰርነት እንቀጥላለን ሲልም ተናግሯል:: የቶታል ኩባንያ ተወካይ በበኩላቸው በሚቀጥለው ዓመት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 20ኛውን ውድድር በልዩ ሁኔታ ሲያከብር ኩባንያቸውም ወደ ኢትዮጵያ የገባበትን 70ኛ ዓመት እንደሚያከብር ተናግረዋል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖንሰሮቹ እና ከሌሎች አጋሮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ተምሳሌት ሆኖ ለመጠቀስ የበቃው በብራንዲንግ፤  በዲኮሬሽን፤ በሰዓት አያያዝ እና ቁጥጥር በአጠቃላይ የስራ ሂደቱና ጥራት ያለው ዝግጅቱ እንደሆነ ለስፖርት አድማስ የተናገረችው ደግሞ የስትራቴጂ እና ኢኖቬሽን ማናጀሯ ዳግማዊት አማረ ናት፡፡  ዋና ዓላማችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይና ተቀባይነት ያለው ውድድር ማዘጋጀት ነው ያለችው ዳግማዊት፤  ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በቀጣይ ውድድሮቹ በተለይ በዲጂታል ማርኬቲንግ በከፍተኛ ሁኔታ በመስራት ከተለያዩ የውጭ  አገራት የሚመጡ ተሳታፊዎችን በየዓመቱ ከ1ሺ በላይ ለማድረግ ፍላጎት አለው ብላለች፡፡
በየዓመቱ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን የ10 ኪሜትር ሩጫ ለማዘጋጀት በ5ኛው እና 6ኛው ውድድሮች  እስከ 4 ሚሊዮን ብር የሚጠይቀው የወጪ በጀት ዘንድሮ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ሲገመት የዝግጅቱ ወጭ የናረው 45ሺ ተሳታፊዎች መኖራቸው፤ በየዓመቱ የሚጨመሩ አዳዲስ ሁኔታዎችና ለውድድሩ ፀጥታ፤ ደህንነትና ውበት በሚከናወኑ ስራዎች ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ የተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ዛሬ የሚካሄደው የህፃናት ሩጫ እንዲሁም የነገው የ10 ኪሜትር ሩጫ በማስተናበር  ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ 15 ቋሚ የውድድር አዘጋጅ ቡድን አባላት ሲሆኑ በውድድሩ ቀን በዝግጅት እና በሌሎች አጠቃላይ ስራዎች የሚሰማሩት ከ800 በላይ ናቸው፡፡ ከእነሱም መካከል 400 በጎ ፈቃደኞች፤ ከ150 በላይ የመጀመርያ ርዳታ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች፤ ከ200 በላይ የፅዳት ሰራተኞች ይገኙበታል፡፡


Read 11741 times