Print this page
Saturday, 16 November 2019 11:21

የመንግሥት ልክ ያጣ ትዕግስት ዜጎችን ለጥቃት እያጋለጠ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ዋንኛው ምክንያት የመንግሥት ልክ ያጣ ትዕግስትና ዳተኝነት መሆኑን የሃይማኖት መሪዎች ተናገሩ፡፡ መንግሥት እያሳየ ያለው ትዕግስት ገደብ ሊኖረው ይገባልም ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ሳቢያ የበርካቶች ሕይወት እያለፈ፣ በርካታ ቤተ እምነቶችም እየተቃጠሉ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በተቃራኒው ሁኔታው እየተባባሰ በአስከፊ ሁኔታ እየተገደሉ፣ ቤተ እምነቶችም እየተቃጠሉና እየፈራረሱ እንደሚገኙ ተገልጿል::  
ይህንን ሁኔታ ለማስቆምና ሕገወጦች በዜጎችና በቤተ እምነቶች ላይ እያደረሱ ያሉትን ጥቃት ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ የተለሳለሰ መሆኑን የጠቆሙት የሃይማኖት መሪዎቹ፤ መንግስት አጥፊዎቹ በሕግ በሚጠየቁበት ሁኔታ ላይ ሊሰራና ዜጎችንና ቤተ እምነቶችን ከጥቃት ሊታደግ ይገባል ብለዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱትን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መላ ለመፈለግና ዜጎች በአንድነትና በመተሳሰብ ሊኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል፡፡ ለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ አገር አቀፍ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ መድረክ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
የሃይማኖት መሪዎቹም እንደየ እምነት ሁኔታቸው በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ በዜጎች መካከል የነበረውን አብሮ የመኖር፣ የመተሳሰብና የመቻቻል እሴቶች ለማጠናከር የሚረዱ ተግባራትን በመከወን፣ ለየእምነት ተከታዮቻቸው ስለ ሰላምና አንድነት አስፈላጊነት ሊያስተምሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

Read 1447 times