Saturday, 16 November 2019 11:24

ኢህአፓ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካሂድ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


             በኢትዮጵያ የፓርቲ ምስረታ ታሪክ ውስጥ በቀዳሚነት የሚሠለፈውና የአራት አስርት ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የፓርቲው አመራሮች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ ባለፈው አንድ አመት ገደማ በመላ ሀገሪቱ የሚገኘውን የፓርቲውን አደረጃጀት በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጐ ሲሰራ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ የኢህአፓ አዲሷ ሊቀ መንበር ሆነው በቅርቡ የተመረጡት ወ/ሮ ቆንጅት ብርሃኑ፤ ፓርቲው ባለፈው አንድ አመት በአብዛኛው የማደራጀት ስራ ላይ አተኩሮ ሲሰራ እንደነበር አስገንዝበዋል:: በአሁኑ ወቅት ኢህአፓ በክልሎችም ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠሩንና የነባር አባላትን ተሳትፎ እያጠናከረ፣ አዳዲሶችን እየመለመለ መሆኑንም ወ/ሮ ቆንጅት አስታውቀዋል፡፡ ኢህአፓ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት አመራሮቹ፣ በቅርቡ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ጥቃቶችና ግጭቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ፣ ለተጐጂዎች ካሣ እንዲከፈልም ጠይቋል፡፡ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርም አሳስቧል፡፡
ኢህአፓ በሀገር ጉዳይ ላይ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በህብረት እንደሚሰራና በሀገሪቱ የሚፈጠሩ የሰብአዊ ቀውሶችን በጥብቅ እንደሚያወግዝም በመግለጫው ላይ አስታውቋል፡፡


Read 1120 times