Print this page
Saturday, 16 November 2019 11:34

የበረሃ አንበጣ መንጋ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ዙር ሊያጠቃ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       “ጥቃቱ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በእጅጉ የሚፈታተን ነው”

           ኢትዮጵያ በታሪኳ እይታ በማታውቀው መጠን በበረሃ አንበጣ መንጋ እየተጠቃች መሆኑን የገለፀው የአለም የእርሻ ድርጅት (ፋኑ)፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ ለሁለተኛ ዙር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሰብሎችን ሊያጠቃ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጥቃቱ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና በእጅጉ የሚፈታተን እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
መነሻውን ከየመን ያደረገው ለሁለተኛ ዙር ጥቃት እየተዘጋጀ ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ፤ በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ላንድ ኮረብታዎች ሰፍሮ ምቹ ጊዜ እየተጠባበቀ ነው ያለው የፋኦ ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከወዲሁ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ተቋሙ አሳስቧል፡፡
ከሁለት ሣምንት በፊት ሀገር ውስጥ የገባውና በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች በስፋት ጥቃት ያደረሰው የበረሃ አንበጣ መንጋው፤ 32ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተዘራ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡ የአንበጣ መንጋው በዋናነት በግጦሽ ሣርና በማሽለ ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ የተጠቆመ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የጉዳቱ አሃዛዊ መረጃ በባለሙያዎች እየተጠና መሆኑን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
ለሁለተኛ ዙር ጥቃት እየተዘጋጀ ነው የተባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ፤ወደ ሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች ይንቀሳቀሳል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ቀደም ብሎ የገባው የአንበጣ መንጋ  በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና አፋር አካባቢዎች በስፋት ጥቃት ማድረሱ ተገልጿል፡፡
በቀጣይ የአንበጣ መንጋው በጫት፣ በቡና፣ በጤፍ በማሽላ፣ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ጥቃቱ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በእጅጉ ሊፈታተን ይችላል ብሏል፡፡
የአንበጣ መንጋው በአብዛኛው ጉዞውን በሌሊት የሚያደርግ ሲሆን በሰአት 150 ኪሎ ሜትር በመጋዝ ጥቃት መሰንዘር እንደሚችል ጥናቶች ይገልፃሉ፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2003 እና 2004 ዓ.ም በአንበጣ መንጋ ተጠቅታ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ነገር ግን በወቅቱ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከአሁኑ በእጅጉ ያነሰ ነው ብሏል፡፡


Read 11130 times