Saturday, 16 November 2019 11:36

የአማራና የኦሮሞ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

  ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በአማራና በኦሮሚያ ክልል እያጋጠሙ ስላሉ የፀጥታ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ አዴፓና ኦዴፓን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር ካደረጉ በኋላ በጋራ አብሮ የመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) እና የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ግንባር ናቸው አብሮ የመስራት ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡
ፓርቲዎቹ ቀደም ብለው በሁለቱ ክልል ህዝቦች አብሮነትና የወደፊት ጉዞ ላይ እንዲሁም ችግሮች ሲፈጠሩ በምን መልኩ መፍታት ይገባል በሚሉ ጉዳዮች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋባዥነት በጽ/ቤታቸው ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በአማራና በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በዚህች ሀገር የፖለቲካ አካሄድ ላይ አሉታዊ ሚናቸው የጐላ መሆኑን በስብሰባው ላይ የገለፁት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ይህ እንዳይሆን በሁለቱ ህዝቦች መሃል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ኃላፊነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የሁለቱን ህዝቦች አብሮነትና ህብረት በማጠናከር በኩል የጐላ ሚና እንዳላቸው ያስገዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ፓርቲዎቹ በጋራ ለሀገር ሠላም ህልውናና ለህዝቦች አብሮነት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
ሁሉም ፓርቲዎች ትግላቸውን የሃሳብ ፖለቲካ ላይ እንዲያደርጉና ከሃይልና ብጥብጥን ከሚያነሳሱ ድርጊቶች በመቆጠብ ችግሮች ሲፈጠሩ ማረቅ በሚቻልባቸውና ከሴራ የራቀ የፖለቲካ መንገድ መከተል እንደሚገባ የተወያዩ ሲሆን በኢትዮጵያ አንድነት፣ ለማምጣት ለመስራትም ተስማምተዋል፡፡ የሀገሪቱን ሠላምና የዲሞክራሲ ሂደት እየጐዱ ባሉ የፖለቲካ አካሄዶች ላይም ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ውይይቱን ተከትሎም ፓርቲዎቹ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ፤ በሁለቱ ክልል ህዝቦች ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራትና በሀገሪቱ አንድነት ላይም በጋራ ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በስምምነታቸው ያለፋ የታሪክ ቁስሎችን በመቆስቆስ ሁለቱን ህዝቦች ወደ ግጭት ከሚከቱ ነገሮች ለመታቀብ እንዲሁም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍም ቃል ተግባብተዋል፡፡
በቀጣይም ችግሮች ሲያጋጥሙም ሆነ የሁለቱ ህዝቦች ጉዳይ ላይ በዘላቂነት እየተገናኙ ምክክር ለማድረግም ተስማምተዋል ተብሏል፡፡
ከፖለቲከኞቹ ባሻገርም የአማራ እና ኦሮሞ ባለሃብቶች ውይይት ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ የሁለቱ ህዝቦች የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተመሳሳይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል::
መሰል የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነት በአማራና በትግራይ፣ በኦሮሚያና በትግራይ፣ በኦሮሚያና  በሶማሌ፣ በአማራና በሶማሌ እንዲሁም በሌሎቹ መካከል እንዲኖር መድረኮች እንደሚፈጠሩ ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡


Read 11666 times