Saturday, 16 November 2019 11:37

የህወኃት ዕጣ ፈንታ ዛሬ ይታወቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

     የአዲሱ ውህድ ፓርቲ እውን መሆን አይቀሬ ነው ተብሏል

          የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ዛሬ በሚያደርገው ስብሰባ፤ የግንባሩና የአጋሮቹ ውህደት ጉዳይ ላይ በመምከር አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ የግንባሩ ስራ አስፈጻሚዎች ዛሬ በሚያደርጉት ስብሰባ በውህደቱ የሚሳተፉና የማይሳተፉ አካላትም ተለይተው ይታወቃሉ ተብሏል፡፡
የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ካሣሁን ጐሬ፣ በውህደቱ ዙሪያ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ የውህደቱ አካል ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶችን ጨምሮ አምስቱ አጋር ድርጅተች ናቸው ብለዋል፡፡
ሌሎች ተቃዋሚዎችም ሆኑ ከኦዴፓ ጋር ትብብር የፈጠሩ ሃይሎች የውህደቱ አካል ለመሆን ሂደት እንዳልጀመሩ ታውቋል፡፡
እስካሁን አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን በየስራ አስፈፃሚዎቻቸው ውህደቱን ደግፈው አቋም የወሰዱ ሲሆን ህወሓት እስካሁን ግልጽ አቋሙን አላሳወቀም ተብሏል፡፡ ምናልባት የህወት የመጨረሻ አቋም በዛሬው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዛሬው ጉባኤ ውህደቱ እንዴትና መቼ ይፈፀም የሚለውን አቅጣጫ የሚያስዝ ይሆናል ያሉት አቶ ካሣሁን፤ ለቀጣዩ ምርጫ የሚወዳደረውም ይኸው ውህድ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡ አዲሱ ፓርቲ  የመደመር እሣቤን የፖለቲካ መርሁ እንሚያደርግ ቢገመትም፤ በቀጣይ ውይይት ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ እንደሚሆን አቶ ካሣሁን አስረድተዋል፡፡
ሃዋሣ ላይ በተደረገው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ በውህደቱ ጉዳይ እንዲወስን ለኢህአዴግ ም/ቤት በተሰጠው ስልጣን መሠረት፤ የውህደቱ የመጨረሻ ውሣኔ በም/ቤቱ የሚተላለፍ ይሆናል ተብለዋል፡፡
በአዲሱ ውህድ ፓርቲ መቀላቀል የማይፈልግ የኢህአዴግ አባል ወይም አጋር ፓርቲ ካለ ይቀራል እንጂ ውህደቱ ይካሄድ አይካሄድ የሚለው በድምጽ ብልጫ የሚወሰን እንደማይሆንም ተገልጿል፡፡
የኢህአዴግ ውህደት ጉዳይ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 21 አመታት ሲታሰብበትና ሲመከርበት የቆየ ሲሆን፤ በቅርቡ ውህደቱ እንደሚተገበርና አዲሱ ፓርቲ እንደሚመሰረት የጠቆሙት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር፤ አዲሱ ፓርቲ ነባሩን የኢህአዴግ ቅርጽ፣ አደረጃጀትና የፖለቲካ እሣቤ የራሱን አዲስ ቅርጽ፣ አደረጃጀትና እሣቤ እንደሚከተል አስረድተዋል::
ውህደቱ ዜጐች በመረጡት እንዲተዳደሩ በማስቻል፣ የሀገሪቱን የፌደራል ስርአት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሚሆን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ፖለቲከኞች ይናገራሉ፡፡
የዚህ ውህድ ፓርቲ መስራቾች ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (እስካሁን አቋሙ ባይታወቅም) የሀረሪ ብሔራዊ ሊግ፣ የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የአፋር ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆናቸው ታውቋል፡፡

Read 13851 times