Saturday, 16 November 2019 11:40

ዕድሜህ ሲጨምር ሱስህ እየበረታ ከመጣ፣ የነገ መንገድህን በቅጡ መርምረው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

   በብዙ መከራ የተሰባሰቡ አራዊት፡፡ ጉዳያቸውን ባለማወቅ ለመግባባት ብዙ ሰዓት ፈጀባቸው፡፡
ጦጢት ነገሩ ገብቷታል፡፡ አላግባባ ያላቸው “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” ነው፡፡
አንበሳ፤
“እስከዛሬ እኔን ተቀብላችሁ ስትኖሩ የነበራችሁ የዱር አራዊት፣ ዛሬ ምን ተፈጠረና ነው አዲስ መሪ ካልመረጥን የምትሉት?” አለ፡፡
ነብር፤
“አያ አንበሶ፣ መቼም እርጅናን የመሰለ የዱር አራዊት ጠላት የለም፡፡ እርስዎ ራስዎ ሲተርቱ እንደሰማነው፣ “እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደለም ወይ?” ብለዋል፡፡
ስለዚህ እንደ እርጅና አሳሳቢ ጠላት የለንም ማለት ነው”፡፡
ዝሆን፤
“እኔም አያ ነብሮ ያለውን ነው የምደግፈው”፡፡
ጦጢት ዛፍ ላይ ሆና፣ የሚባለውን ሁሉ እያዳመጠች ናት፡፡
“እኔ ሞት ይሻላል ነው የምለው፡፡
“ያው ሞቱ ይሻላል ቁርጡ የታወቀው” ይል የለ አበሻ” አለች፡፡
“እንዲህ ሞትን ስትመኚ መበላትም እንዳለ አትርሺ!” አላት አያ አንበሶ፡፡
*    *    *
አበሻ መሟረት ይወዳል - ከምኞት ላያልፍ፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሾተላይ አለባት፡፡ መርገምት አለባት፡፡ እያደር ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አትሄድም፡፡ አንዱ መርገምቷ ይሄ ነው፡፡
ሁለተኛው መርገምቷ መሪ እንዲዋጣላት አለመሆኑ ነው፡፡ ከትናንሽ ከንቱ ሰዎች አንስቶ እስከ ትላልቅ ሹማምንት ድረስ፣ በየጊዜው በሚገርም ፍጥነት ይቀያየራሉ፡፡ አንዱ የጀመረውን ሌላው ለመጨረስ ፋታ የለውም፡፡ እንደተዋከበ ጀምሮ እንደተዋከበ ያበቃል፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰሎሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት ራሱ ሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን”
የተለመዱት አባባሎች ላይ ሃሳብ ጨምረን ማዳበር ትልቅ ክህሎት ነው፡፡
አገራችን እንደዚህ ዓይነት ርቀትና ልቀት ያሻታል፡፡ መንገዱ ረዥም ይሁን እንጂ ፍፃሜው ጣፋጭ እንደሚሆን ማመን ትልቅ ችሎታ ነው፡፡
ያለ ድካም ፍሬ አይገኝምና!
አለ በውስጣችን ደግ ደግ ፈለግ
ደሞም ዕውቀት ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ
ዕድሜህ እየጨመረ ሲመጣ ሱስህ እየበረታ ከመጣ፣ የነገ መንገድህን በቅጡ መርምረው! ይላሉ ፈላስፎች፡፡

Read 13274 times