Saturday, 16 November 2019 12:09

ሂጅራ ባንክ ከግማ ቢ.ብር በላይ የተከፈለ አክሲዮን ሰበሰበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

      የአክሲዮን ሽያጩን እስከ ህዳር 15 አራዝሟል
                               
              የምስረታ ሂደቱን ከጀመረ አራት ወራትን ብቻ ያስቆጠረው ሂጅራ ባንክ የተከፈለ 527 ሚ.ብር በላይ አክሲዮን መሰብሰቡንና የተፈረመው የገንዘብ ብዛት ከ1.04 ቢ.ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ትላንት አርብ ህዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም ጠዋት በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ የአክሲዮን ሽያጩን እስከ ህዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ማራዘሙንም ገልጿል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ እንቅስቃሴና የአክሲዮን ሽያጭ ስኬት ብሄራዊ ባንክ ካስቀመጠው መመሪያ ሕግ አንጻር ከመቶ ፐርሰንት በላይ ማሳከቱን ነው የባንኩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት የገለፁት፡፡
ሂጅራ ባንክ ለስኬታማነት ያበቃው አካታችና አቃፊ የፋይናንስ ሥርዓትን ለመፍጠር ግቡ አድርጎ ከተነሳ በኋላ የአክሲዮን ሽያጩን ከክልል፣ ወረዳና ቀበሌዎች ድረስ ወርዶ ግንዛቤ በመፍጠርና በመስራት መጀመሩ እንደ ሆነ የሂጅራ ባንክ መስራች፣ የአደራጆች ፀሐፊና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጅብሪል ኡስማን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ ምንም እንኳን 700 ሰው ያህል በተገኘበት ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል የመዝጊያ ፕሮግራም የተከናወነ ቢሆንም በዛን ሰሞን አብዛኛው ነጋዴ በአመታዊ የግብር ክፍያ ሂደት ላይ የተጠመደበትና ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በዚያው ላይ ያደረገበት ወቅት በመሆኑ እንዲሁም ዲያስፖራው ማህበረሰብ በበቂ ሁኔታ አለመሳተፉን ገልፆ የአክሲዮን ሽያጩ እንዲራዘም በስልክ፣ በሶሻል ሚዲያና በአካል በመጠየቃቸው መራዘሙን ተናግረዋል፡፡
ሂጅራ ባንክ የምስረታ ሂደቱን ከጀመረ ጀምሮ ብሄራዊ ባንክ የሚጠይቀውን 500 ሚ. የተከፈለና 1 ቢ ብር የተፈረመ ብር አልፈን 527 ሚ የተከፈለና 1.04 ቢሊዮን የተፈረመ ገንዘብ ሰብስበናል ይህም ስኬታችን ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነው ያሉት ሀላፊው እስከ ህዳር 15 ቀን ደግሞ በርካታ አክሲዮን ይሸጣል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡
ሂጅራ ባንክ አክሲዮን ማህበር መደራጀት ሲጀምር በርካታ ባንኮች በተለያየ ስም መጥተው ሕዝቡ ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ስለነበር ችግሩን ለማጥራት ውይይት መደረጉን የገለፁት ሲሆን የሂጅራን ቢዝነስ ሞዴል የሚከተሉና በዚያ መሰረት አብረው ለመስራት ለሚፈልጉ ጥሪ ማቅረባቸውንና ‹‹ሁዳ››፣ ‹‹ሰላም››ና ‹‹በረካ›› ብለው ከመጡ ውስጥ ወደ ሂጅራ በመሳብ በ8 አደራጆች የተጀመረው ሂጅራ በአሁኑ ሰዓት ወደ 38 ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ሂጅራ ባንክ በቀጣይ የሸሪአ ህጉን የተከተለ ሁሉን ያካተተ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የስራ እድል ፈጠራና የአገር ልማት ላይ አሻራውን ለማኖር እየሰራ ነው ያሉት ሀላፊው በዚህ ተቋም በተለይ አርብቶ አደሩ፣ አርሶ አደሩ ተማሪና መምህራኑ ዲያስፖራውና የትኛውንም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሆኖ መቀረፁን ተናግረው፣ 38ቱም አደራጆች ከተለያዩ ብሄሮች የተገኙና የተለያየ እውቀትና ልምድ ይዘው የተሰባሰቡ የትኛውንም አካባቢ ሕዝብ ማናገር የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

Read 2990 times