Saturday, 16 November 2019 12:22

መለወጥ ወይስ ‹‹መደፍጠጥ?›› - ለኢሕአዴግ የቀረበ ምርጫ!

Written by  ከሙሼሰሙ
Rate this item
(2 votes)


            ኢህአዴግ ለለውጥ የተጋውን ያህል፤ መገለጫዎቹ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትና አፋኝነት እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አማራጭ መሆን የሚችሉ ጠንካራ ፓርቲዎች፣ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች፣ ነጻ ጋዜጦችና ማህበረሰባዊ ተቋማት በሃገራችን እንዳይኖሩ ጠንክሮ መስራቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ  በዚህ ድርጊቱ ከ27 ዓመት በኋላም ቢሆን፣ ዜጎች የሚተማመኑበት የተደራጀ አማራጭ ሃይልና ሃሳብ እንዳይኖራቸው ወሳኝ ሚና መጫወቱ ከጥፋቶች ሁሉ የላቀው ጥፋት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ዛሬ ላይ ሃገራችንም ሆነች ሕዝቦቿ ሉዕላዊነታቸው ተገሶ፣ የኢህአዴግ ጥገኛና ምርኮኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ተፈርዶባቸዋል፡፡ የኢህአዴግ ነገርም የማይታረቁትና የማይፋቱት ተቃርኖ ሆኖ አሁንም ስለቀጠለ፣ ልክ እንደ ቀን ቅዠት አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር፣ ዜጎችም ሆኑ ሀገር የሚረበሹበት ጉዳይ መሆኑ ቀጥሏል፡፡  
ኢህአዴግ  የፈጠረውን ይህንኑ የስጋትና የተሳከረ ነባራዊ ሁኔታ መጠቀሚያ በማድረግ፣ እራሱን ከሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም አኳያ ከማደስና ከማረም ይልቅ በአየር ላይ ሕልውናውን ለማስቀጠል ሲል፤ አንዴ ‹‹ሃገር ትፈርሳለች›› ሌላ ጊዜ ‹‹ሕዝብ ይበተናል›› የሚለውን ትርክት በገሃድ በማሰራጨት፣ ዜጎችን በማሸማቀቅና በማስፈራራት አማራጭ ሃሳብ እንዳይኖር፣ ሕገ መንግስታዊነትና ተቋማዊነት እንዳይዳብር ከማድረግ ቦዝኖ አያውቅም፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ኢህአዴግ የፈጠረውን የስጋት ድባብ በመንተራስ፣ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል በመወሰን ሂደት ላይ “ተወደደም ተጠላ” የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ግንባር እራሱ ብቻ መሆኑን ደጋግሞ አስመስክሮበታል:: በተለይ ደግሞ የምርጫ ወቅት እየተቃረበ በመጣ ጊዜ፤ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ እየቆሰቆሰ መጠቀሚያው በማድረጉ ዜጎች በስጋት ውስጥ ሆነው መቶ ፐርሰንት እስኪመርጡት ድረስ ሲያዋክባቸውና ጫና ሲያሳድርባቸው እንደነበር የቅርበ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ሃገራችን በዚህ መንገድ በመቃኘቷ ይመስለኛል፤ ላለፉት 27 ዓመታት እንደ ሕዝብ ኢህአዴግን ደገፍነውም አልደገፍነው፣ መረጥነውም አልመረጥነው፣ ወደድነውም ጠላነው፣ አነሰም በዛም እለት ከእለት በስልጣን ላይ መቀጠሉና አለመቀጠል ወይም እንደ ግንባር መሞቱና መሰንበቱ የሚያሳስበን አጀንዳ ሆኖ እንዲዘልቅ ማድረግ የተቻለው፡፡ ውጤቱ ግን ዘለቄታ አልነበረውም፡፡ ሕዝብን በሉዕላዊነትና በሕግ የበላይነት ከመምራት ይልቅ አስፈሪ የስጋት ድባብ በመፍጠር በዛ ድባብ ውስጥ በተጽእኖ፣ በእቀባና በስጋት እንዲኖሩ በማድረግ ነጻነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ሲነጠቁ፣ ከስጋታቸው የተነሳ የአንድ ፓርቲ ምርኮኛነታቸው የማይቀር መራራ እውነታ የሚሆነው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ነጻነትና ሉዓላዊነትን በዚህ መልክ ሲደፈጠጥ በአመጽ፣ በጉልበትና በጫካ ሕግ ነጻነትንና ሉዓላዊነትን መቀዳጀት ያስከትላል፡፡ የኛ ጦርነት ስላለቀና ስለተጠናቀቀ፤ ሌላው “ደፍሮ” ጦርነት ውስጥ አይገባም የሚለው ትርክት የትም አያደርስም፡፡
ኢህአዴግ በጎ ጎኖቹ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ላለፉት 27 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ ጠላት እየፈበረከ፣ ተቃዋሚዎችን እያዳከመ፤ ለዜጎች፣ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አዳዲስ ትርክቶችን እየፈጠረና እያጋጨ በመጣበት መንገድ፣ በስልጣን ላይ ለመቀጠል እንደማይችል ያለፉት ሶስት ዓመታት ግልጽ አድርገውለታል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ እውነታው ግን አሁንም የጠራ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በነበረውና በለመደው መንገድ የመጓዝ አባዜ ዛሬም ላይ በገሃድ ይታያል፡፡ ኢህአዴግ በለመደው መንገድ፣ በታሪክ አጋጣሚና በደረሰበት ቦታ ሁሉ ከጦር ምርኮኛና ከየፓርቲው በሚያውጣጣቸው አባላት አማካኝነት የብሔርም ሆነ ሌላ ዓይነት ፓርቲዎችን ዛሬ መቀፍቀፍ እንደማይችልና ያኔ የቀፈቀፋቸው ፓርቲዎች አባላትም ቢሆኑ፣ ዛሬ ላይ  ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በአዲሱ ትውልድ አባላት የተተኩ ስለሆነ፣ በኢህአዴግ ውስጥ የአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን የበላይነትን ማስፈን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ መሰናበቱ ግልጽ የሆነለት ይመስላል፡፡ ኢህአዴግ ዛሬ ላይ ሁሉም ሕዝብ እንደየምርጫውና አሰላላፉ ለዜግነቱ፣ ለማንነቱና ለአንድነቱ ተቆርቋሪነትን ያዳበረ ከመሆኑም በላይ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ይዋል ይደር እንጂ የማይጋፉት ብቸኛው መንገድና አማራጭ መሆኑ በገሃድ ፍንትው ብሎ የሚታይ ቢሆንም ግንባሩ ግን እውነታውን ለመጨበጥ ያዳገተው ይመስላል፡፡
የትንናቱ ኢህአዴግ ዓለምን ያስደመመ የሚባልለት ርዕየተ ዓለሙም ሆነ የልማት እቅዱ፣ ድራማውም ሆነ ዶክመንትሪው፣ ከ27 ዓመት በኋላ በተለይም ከመጨረሻዎቹ ሦስት ዓመታት ወዲህ ብዙ ርቀት ሊያራምደው እንዳልቻለ አብረን ታዝበናል፡፡ በመጨረሻዎቹ ሦስት ዓመታት ከነበረው ሁነት በጥቅሉ እንደተረዳነው፤ የግንባሩ ነዳጅ ተሟጦ በማለቁ ምክንያት የዜጎችን ጥያቄ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በጥይት ለመፍታት ሲሞክር ከርሞ፣ በመጨረሻ ላይ በመረጠው መንገድ በተባበረ የሕዝብ አመጽና ቁጣ ሊንበረከክ ችሏል፡፡ ዛሬ ላይ በደመ-ነብስ ቢውተረተርም፣ በለመደው መንገድ ለመራመድ አቅም ያጠረውና በስጋም ሆነ በመንፈስ ያበቃለት፣ በቅርጽና በስም ብቻ ካልሆነ በስተቀር በተግባር መቀጠል ያልቻለ ድርጅት ስለመሆኑ ከሚያፈራው ፍሬ እያስመሰከረ ነው፡፡
ከዚህ ተነስተን ስንፈትሸው፤ ኢህአዴግ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው የውስጠ ፓርቲ ሽኩቻም ሆነ በሃገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው ቁጣና አመጽ አንዱ መንስኤ “ግንባሩ በመጣበት መንገድ፣ አደረጃጀት፣ አሰራርና ርዕዮተ ዓለም መቀጠል ይችላል ወይስ አይችልም?” በሚለው ወሳኝና ፈታኝ ጥያቄ እንዲሁም “ባለበት መቀጠል አለበት” በሚለው ሃይል መካከል መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በተግባርም እየታያ ያለው የድርጅታዊ አቅም መላሸቅ፣ በክልል ደረጃ መጥበብ፣ በጊዜያዊ ጉዳይ መደናበርና ችግር የመፍታት አቅም ማጣት፣ ሃገርና ሕዝብን እያነጋገረና እያተራመሰ መሆኑም ሌላው በግንባሩ ውስጥ ለለውጥ መንስኤነት ግፊት እያደረገ ያለ ፈታኝ ጥያቄ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ፣ ለዘመናት እራስን አድራጊና ፈጣሪ እንዲሁም ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የማቅረብ አባዜ ባስከተለው መዘዝ ምክንያት ቁጣ የቀሰቀሰው ሕዝባዊ ትግል ለኢህአዴግ “መለወጥ” ወይም “መዳመጥ” የሚል አስገዳጅ ምርጫ የቀረበለት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግ በመጣበት መንገድ መቀጠል እንደማይችልም ላለፉት ሶስት ዓመታት ያለማቋረጥ… በተለየ ሁኔታ በኦሮሚያና በአማራ፣ አልፎ አልፎም በተባራሪ መንገድ በተለያዩ ክልሎች የተቀጣጠሉት ዓመፆች አመላካች ናቸው፡፡ የዓመፆቹ ምክንያቶች ውስብስብና አንዳንዴም ብሔር፣ ሃይማኖትና ጎጥ ተኮር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከበስተጀርባ ሆነው በሚዶልቱ ሃይሎች ግፊትና ተጽእኖ የሚከሰቱ ቢሆኑም ዋነኛ መገለጫቸው ግን ሕዝብ በኢህአዴግ ስራ አለመርካቱ፣ መሰላቸቱና ከኢህአዴግ ጋር ለመፋታት መፈለጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ኢህአዴግ ውስጠ ፓርቲ መናጥ (ዳይናሚክስ) እንደሚታይበት ድርጅት፤ ይህንን ተጨባጭ ሁኔታ ተረድቶና መዝኖ ለመለወጥ ማሰቡ እሰየው የሚያሰኝ እርምጃ ነው፡፡ ግንባሩ ሃገሪቱን ገደል አፋፍ አድርሶ፣ እራሱንም ገደል ውስጥ ጨምሮ ሃገሪቱንና ሕዝቦቿን ለእልቂትና ለውድቀት ከመዳረጉ በፊት ከደነዘዘበት በመንቃት በጭላንጭልም ውስጥ ቢሆን ማሰብ መጀመሩ፣ “አማራጭ የሌለው ድርጅታዊ ጉዞ” ነው የሚል ግምገማ አለኝ፡፡ ሁሉም ነገር ጊዜና ሂደት የሚያጠራው ጉዳይ ሲሆን በዚህ መሃል መንጠላጠል፣ መውረድና መፋታትም የሚጠበቅ ነው፡፡ በጥቅሉ፤ የአዲሱን ፓርቲ ሰነድ የማንበብ እድል ባይገጥመኝም፣ በአንድ በኩል ዛሬ ላይ ሆኜ ስመለከት፣ ሽግግሩ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ስለ አዲሱ ፓርቲ በየመድረኩ ከሚነገርለት በመነሳት፣ ከስጋት አኳያ ጥቂት ነገሮችን ብቻ ለማለት እወዳለሁ፡፡
አንደኛ፤ የአዲሱ ፓርቲ የአባላት አደረጃጀት ጥልፍልፍና ውትፍትፍነት የሚስተዋልበት ፓርቲ ሊሆን እንደሚችል ከአመራሮቹ በተለያየ ጊዜ በተናጠል ከሚነሱት ሃሳቦች መገመት ይቻላል፡፡ የአዲሱ ፓርቲ አባላት ዜጎች፣ ብሔሮች፣ ቡድኖች ወይም የብሔር አሊያም ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይነገራል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ፓርቲ ውስጥ ምን ዓይነት “ፕሮፖርሽናል ሪፕረዘንቴሽን” ሊኖር እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ለኦዴፓ ድል እንደሆነ መገለጹ፤ ኦዴፓ እንደ ሕወሃት “በአዲሱ ኢህአዴግ” ውስጥ የበላይነቱን ለመውሰድ ጡንቻውን በማሟሟቅ ላይ መሆኑን ሊያመላክት ስለሚችል፣ በሌሎች ዘንድ ስጋት መደቀኑ አይቀርም፡፡ ትናንት ዜጎችን ወደ አመጽ የወሰደ የአንድ ፓርቲ የበላይነትን፣ በሌላ ቅርጽና ይዘት ዛሬ ላይ በመድገም ፓርቲው ዜጎችን፣ ብሔር-ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ምርኮኛ ለማድረግ እየተመቻቸ ከሆነ፣ መቼስ ከሂደት ያለ መማር ዓይነተኛው መገለጫ ሆኖ እንደሚጠናቀቅ መገመት ነብይነትን አይጠይቅም፡፡ እኩልነትን፣ መከባበርንና መቻቻልን እንጂ ማናቸውንም ዓይነት የቁጥር፣ የብዝሃነትም ሆነ የብዙነት አሊያም የርዕዮተ ዓለምም ሆነ የአደረጃጀት የበላይነትን የሚቀበል ጫንቃ ያለው ሕዝብ እንደማይኖር ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ሁለተኛ፤ ነባሩ ኢህአዴግ በአዲስ መልክ ሲደራጅ አባል ድርጅቶችና የተናጠል ግለሰብ አባላቱን ጨምሮ በፓርቲው በሚፈጠረው ውስጠ ፓርቲ ትግል አቋመ ቢስ ሆነው የሚንጠላጠሉ፣ ከተለመደው መለኮታዊ ክብርና ሞገስ በመውረድ “ሰው መሆን” እና እስከነ አካቴውም መፋታት የሚመርጡ ሊኖሩ እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህንን የውስጥ ፓርቲ ትግል ልክ በሃገር ህልውና ላይ የተደቀነ ፈተና አስመስሎ በማቅረብ፣ ሃገራችንን ለውድቀትና ለአደጋ የምትጋለጥ አድርጎ ማቅረብና፤ ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ መግለጽ አስተዛዛቢ ድርጊት ነው፡፡ ሀገሪቷ አስቸጋሪ በሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ብትገኝም እንኳን፣ የፓርቲዎች መምጣትና መሄድ ወትሮም የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን ከእነውጥንቅጣችንም ቢሆን፣ ኢህአዴግ ኖረም አልኖረም ሃገርን የማስቀጠል ጉዳይ እንደ ሕዝብ ቃል ኪዳን የገባንበትና የመጭው ትውልድ አደራም ጭምር ስለሆነ፣ ሁላችንም ለኢትዮጵያ ዘብ ልንቆምላት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሦስተኛ፤ የኢህአዴግ አባል ያልነበሩና ያልሆኑ ሃይሎችም ሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች፤ ኢህአዴግ ለምን ይለወጥብናል በሚል የአዞ እንባ በማንባት፣ ሕዝብን ከሕዝብ ከማጋጨትና ከማጨራረስ ይልቅ የራሳቸውን ፓርቲ አቋቁመው የተሻለ የሚሉትን አማራጭ ሃሳብ ቀርጸው በፓርቲ በመደራጀት፣ የሃሳብ የበላይነታቸውን በአዲሱ አማራጭ ላይ ማሳየት ጨዋነት ያለበት አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አባል ያልሆኑበት ፓርቲ የቅርጽም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ማድረጉን በመቃወም፣ የጋራ ሃገራችንንና ሕዝባችንን የሁከት ምርኮኛ ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው፡፡ በጎንዮሽ አጀንዳ ሃገርን በማመስ፤ ወላጆችን፣ ሕጻናትን፣ አረጋውያንንና በአጠቃላይ ሕዝብን ከማስለቀስ ውጭ ፖለቲካዊ ትርፍ አይገኝም፡፡ በዚህ የተንኮል መንገድ አሸናፊ ኃይል መሆንም አይቻልም፡፡
በመጨረሻም አንድ ነገር ልጨምር፡፡ ኢህአዴግ ለመዋሃድም ሆነ እንደ ኢህአዴግ ለመቀጠል ሲወስን፣ ጉዳዩ ውስጠ ፓርቲ ትግል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአዲሱ ውህድ ፓርቲ ውስጥ መቀጠል የማይፈልጉ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ላይ ‹‹እኛ በፈቀድነው መንገድ ካልሄደ አይሆንልንም›› ከሚሉ፣ ምርጫ ቦርድ ቀርበው አዲስ ግንባር በመመስረት ወይም ያላቸውን ፓርቲ በተናጠል እንደ ፓርቲ በማስቀጠል ትግላቸውን ማጧጧፍ ወይም ደግሞ ድሮ ከምናውቀው ኢህአዴግ ውጭ ትግል አልሆንልህ ካላቸው ትግሉን እርግፍ አድርገው በመተው፣ ለሕዝባቸውና ለጋራ ሃገራችን የሰላም አማራጭ ሆነው መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ የግንባራቸው የውስጥ ጉዳይ በሆነው ውህደት፣ ጥምረት ወይም መበተን ምክንያት ጫካ መግባትም ሆነ የጋራ ሃገራችንን ማፍረስ አሊያም ኮንፌዴሬሽን ለመመስረት መማጸን፣ አልፎ ተርፎም ሃገራችንን ማገቻ ለማድረግ መዶለት መጣንበት ከሚሉትም ተሞክሮ አኳያ የሚመጥናቸው  ድርጊት አለመሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በአጠቃላይ፤ ቀደም ባሉት ሦስት አሰርት ዓመታት እንደታዘብነው፤ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ከሚያጠቃበት ዘዴዎች መካከል አንዱ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውስጣቸው ገብቶ ይከፋፍላቸውና ዘወር ብሎ “ተቃዋሚዎች ውስጠ ፓርቲ ልዩነቶቻቸውን የሚያስተናግዱበት አቅማቸው እጅግ በጣም ደካም ነው፡፡ የቅራኔ መፍቻ ስርዓት የላቸውም” በማለት ለሕዝብ ያሳጣቸው ነበር፡፡ በርግጥ የተቃዋሚዎች ደካማነት ስህተት አልበረም:: ዛሬ ላይ ግን ኢህአዴግ በዚሁ ሲመጻደቅበት በነበረው ቅራኔን በአግባቡ የመፍታት ወይም የማስተናገድ አጀንዳ ተጠምዶ እራሱን የሚፈተሽበት ወቅት ላይ መድረሱ ግልጽ ሆኗል:: ታድያ፣ ልዩነትን በጨዋ ደንብ ይፈታዋል ወይስ ተቃዋሚዎችን ሲያማ በነበረት መንገድ ጸጉር እየተነጫጨና በየመንገዱ እርስ በርስ እየተፈነካከተ ያጠናቅቀዋል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው:: እውነታውን በቅርቡ የምናየው ይሆናል:: ለማንኛውም ግን ኢህአዴጎች ሆይ፣ የጋራ ሃገራችንን ለጊዜውም ቢሆን ለቀቅ አድርጋችሁ አመላችሁንና አተካሯችሁን በጉያችሁ ሸጉጣችሁ፣ ውስጠ ፓርቲ የሽግግር ሂደታችሁን ለሕዝብ ክብር ስትሉ በመደማመጥ፣ በውይይት፣ በመከባበርና በሰላም እንድታጠናቅቁ መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሰላም!!

Read 962 times