Print this page
Saturday, 16 November 2019 12:28

የእናቶች ሰቀቀን…!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

      እናቴ ከምትለው ሳይሆን ሚስቴ ከምታስበው አውለኝ ይባላል፡፡ ሚስት በባሏ ላይ ክፉ ነገር ይደርስ ይሆን ብላ አታስብም ባይባልም፣ የቅናት ስሜት ሊፈጠርባት ስለሚችል፣ ባሏ ከቤት በራቀ ጊዜ “በየመጠጥ ቤቱ ሲዞር፣ ከኮረዳዎች ጋር ሲላፋ ይሆናል” ብላ ልትገምት ትችላለች፡፡ እናት ግን የምታስበው አንዱን ልጇን ብዙ ሆነው ሊያጠቁት ሲዘጋጁ ሊሆን ይችላል፡፡ እናት የልጇ ትንሹም ትልቁም ጉዳይ ያሳስባታል - ያስጨንቃታል፡፡ ዘጠኝ ወር አርግዛ፣ ብዙ ፈተና አልፋ ያሳደገችው ልጇ በመሆኑ፣ መንሰፍሰፏ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
የፖለቲካ ትግል የሚካሄድባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ ጥቂት ሰዎች እራሳቸውን በቡድን አደራጅተውና ኩዴታ ፈጽመው፣ የመንግሥት ሥልጣን ሊጨብጡ ይችላሉ፡፡
መሣሪያ አንስተው ጫካ የሚገቡት ደግሞ ትግሉ የወሰደውን ጊዜ ያህል ወስዶ በእነሱ አሸናፊነት እንዲደመደም ለማድረግ፣ በደፈጣ ወይም በፊት ለፊት ውጊያ ይገድላሉ፣  ይገደላሉ፤ ይማርካሉ፣ ይማረካሉ፤ ንብረት ያወድማሉ፤ ይዘርፋሉ…የማታ ማታ ከተሳካላቸው፣ እንደ ሕወሓት ኢህአዴግ አሸንፈው፣ የመንግሥት ሥልጣን ይይዛሉ፡፡
መግደልና መሞት የማይፈልጉት፣ መሣሪያ ማንሳትን ምርጫቸው ያላደረጉት ደግሞ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመንግሥትን ድክመቶች በመግለጥ፣ ራሳቸውን ለሕዝብ ተቆርቋሪ አድርገው በመሳልና በማሳየት፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ድጋፍ እንዲያጣ፤ እንዳይታመን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በምርጫ ወቅት ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረብም፣ ከሌሎች ተቀናቃኞቻቸው አንፃር፣ የተሻለ ድጋፍ በማግኘት ተመርጠው፣ ለመንግሥት ሥልጣን ይበቃሉ፡፡
በሀገራችን መሣሪያ አንስተው የሚፋለሙ ብዙ ድርጅቶች የነበሩ ቢሆንም፣ ባለፈው የአንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሁሉም ትጥቃቸውን ፈታው፣ ወደ ሰላማዊ ትግል እንደገቡ ይታመናል:: እኔ እስከማውቀው፣ አሁን መሣሪያ አንስቶ ከመንግሥት ኃይል ጋር እየተዋጋ ያለው የኦነግ አካል “የነበረው”፤ ጃልሞሮ የሚመራው “ኦነግ ሸኔ” ብቻ ነው፡፡  
ከአንድ ዓመት ወዲህ በየቦታው ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ ሰው የሚገድሉና የሚያጋድሉ፣ ንብረት የሚዘርፉና የሚያዘርፉ፣ ሰዎች ከቤታቸው በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይመለሱ የሚያውኩ ሌሎች አዲስ “ታጋዮች” ተፈጥረዋል፡፡ እነሱ ወደ ፈለጉት ግብ ለመድረስ ንፁሃንን ያለ ምክንያት ይደበድባሉ፤ አካላቸውን ያጎድላሉ፤ ንብረታቸውን ያወድማሉ፡፡ በዚህ ብቻ አይመለሱም፡፡ ሕይወታቸውንም  ያጠፋሉ፡፡
ከአመታት በፊት አውሮፕላን ጠልፈው ወይም ሰዎችን አፍነው መያዣ በማድረግ፣ ድርድር የሚጠይቁ የፖለቲካ ኃይሎች ነበሩ፡፡ በእኛ አገር ብዙም ባይታወቅ፣ በሌሎች አገራት የተለመደ አሠራር ነበር፡፡ ህገወጥ ቢሆንም፡፡እነሱ አውሮፕላን ሲጠልፉ ወይም ሰው ሲያግቱ፣ ማንነታቸውን ገልጠው የሚፈልጉትን ጉዳይ በይፋ ዘርዝረው፣ “ጥያቄ አለን” በማለት ለመንግሥት ያቀርባሉ፡፡
እኛ ዘንድ አሁን እየታየ ያለው ነገር ግን ቅጥ አምባሩ የጠፋ ነው፡፡ በየዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቻችን በግጭት እንደ ዘበት እየሞቱ ነው:: ይህን የሚያደርጉ - ቡድኖች እንደዚህ አይነት ግብ ለመጨበጥ ነው አይሉም፡፡ ግን ይገድላሉ፣ ያስገድላሉ፡፡
እንዲህ የምታደርጉ ወገኖች እባካችሁ፣ ጥያቄያችሁን ይዛችሁ ወደ አደባባይ ውጡ:: ሀገር ውስጥ ካልሆነላችሁ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ተጠቅማችሁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያደርግላችሁ የምትፈልጉትን በግልፅ ጠይቁ፡፡ መደራደር የምትፈልጉ ከሆነም ጊዜና ቦታ ቆርጣችሁ፣ መንግሥትን እዚህ ቦታ እንገናኝ በሉት፡፡ በዚህ በኩል ግልጽነቱ፣ ድፍረቱና ቁርጠኝነቱ ሊኖራችሁ ይገባል፡፡
መንግሥት ለማንበርከክ ብላችሁ… በየጊዜው የነገ ፍሬዎችን የዛሬ አበባዎችን” - ልጆቻችንን መቅጠፋችሁን አቁሙ!! በወጣቶቻችን ነፍስና ደም አትቆምሩ፡፡
በግብግቡ ውስጥ ምንም ሚና የሌላቸውን ምስኪን የኢትዮጵያ እናቶች አታሰቃዩ፡፡ “ወይኔ ልጄን!” የሚለው የእናቶች የሰቀቀን ጩኸት ይሰማችሁ - “ኧረ ልጄን ተውልኝ” እያሏችሁ ነው፡፡ እባካችሁ ሰላም ስጧቸው!!  

Read 9971 times