Print this page
Saturday, 16 November 2019 12:33

ፌስቡክ 3.2 ቢሊዮን ሃሰተኛ አካውንቶችን መዝጋቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሁዋዌ ለሰራተኞቹ የ285 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ሰጠ

            የአለማችን ቁጥር አንድ ማህበራዊ ድረገጽ፣ ፌስቡክ እስካለፈው መስከረም በነበሩት የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ3.2 ቢሊዮን በላይ የፌስቡክና የኢንስታግራም ሃሰተኛ አካውንቶችን መዝጋቱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፤ ፌስቡክ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በመላው አለም የሚገኙ ተጠቃሚዎች ያሰራጯቸውን 11.4 ሚሊዮን ያህል የጥላቻ ንግግሮችና መልዕክቶች ከድረገጹ ላይ ማጥፋቱን ጠቁሟል፡፡ በዚሁ የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢንስታግራም በተሰኘውና ተጠቃሚዎች ፎቶግራፎችን በሚያሰራጩበት አፕሊኬሽኑ የተለቀቁ 1.2 ሚሊዮን የሚደርሱ የህጻናት ርቃንና የወሲብ ምስሎችን ማጥፋቱን የገለጸው ፌስቡክ፤ የተለያዩ አሸባሪ ቡድኖችና ደጋፊዎቻቸው ካሰራጯቸው የሽብር ፕሮፖጋንዳ መልዕክቶች መካከል 98 በመቶ ያህሉን ማስወገዱንም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የሞባይል አምራችን ኩባንያ የሆነው የቻይናው ሁዋዌ፣ ሰራተኞቹ ከአሜሪካ መንግስት የተጣለበትን ማዕቀብ ተቋቁመው፣ ለተሻለ ስኬት እንዲነቃቁ ለማትጋት በድምሩ 285 ሚሊዮን ዶላር በጉርሻ መልክ መስጠቱ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው የማትጊያ ጉርሻውን የሰጣቸው በማይክሮ ቺፕስ ምርት፣ በምርምርና ልማት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ለሚሰሩ 90 ሺህ ያህል ሰራተኞቹ መሆኑን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ እያንዳንዱ ሰራተኛ በአማካይ 3 ሺህ 100 ዶላር ገደማ  እንደሚደርሰው አመልክቷል፡፡
ሁዋዌ፤ ከዚህ በተጨማሪም 180 ሺህ ለሚደርሱት ሁሉም ሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ሰራተኞቹ ለስኬቱ ቁልፍ ሚና በመጫወታቸው ምስጋና ለመስጠትና ለወደፊቱም ተግተው እንዲሰሩ ለማበረታታት በማሰብ ውሳኔውን ማሳለፉን እንደገለጸ አመልክቷል፡፡

Read 2003 times
Administrator

Latest from Administrator