Print this page
Saturday, 16 November 2019 13:02

የአውስትራሊያን ከፍተኛውን ሽልማት ያሸነፈችው ሶስና ወጋየሁ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

      ሰርከስ ኢትዮጵያን ከመሰረቱት ታዳጊዎች አንዷ ነበረች። ሰርከስ ለማሳየት ወደ አውስትራሊያ ብዙ ጊዜ ተመላልሳለች:: በመጨረሻም ዜግነት ተሰጣትና ኑሮዋን በአውስትራሊያ አድርጋ ለረጅም ጊዜ ቆይታለች፡፡
ላለፉት 16 ዓመታት በአገረ አውስትራሊያ የኖረችው ወ/ሮ ሶስና ወጋየሁ፤ በተለያዩ ሥራዎቿ ከአውስትራሊያ መንግስት በርካታ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ ዘንድሮ የተሸለመችው ግን ይለያል፡፡ “Order of Australia” የተሰኘውን የአገሪቱን ከፍተኛ ሽልማት ማሸነፏን ወ/ሮ ሶስና ትናገራለች፡፡ የአውስትራሊያ መንግስት ይህንን ትልቅ ሽልማት የሚሰጠው የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥና ችግር ፈቺ የሆኑ ትልልቅ ሥራዎችን ለሰሩ የአውስትራሊያ ዜግነት ያላቸው ነገር ግን የትኛውም አህጉር ለተወለዱ ግለሰቦች ነው፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ሶስና ወጋየሁም ሴፕቴምበር 19 ቀን 2019 ዓ.ም ይሄ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡ ‹‹ሽልማቱ የሚሰጠው በሰዎች ጥቆማ ነው ጠቋሚውም አይለገፅም ‹‹እስካሁን ማን እንደጠቆመኝም የማውቀው ነገር የለም፤ ግን ከዚህ በፊት ከተሸለምኳቸው አራት ሽልማቶች የሚበልጠውንና የአገሪቱ ትልቁን ሽልማት ሰጥተውኛል›› ብላለች፡፡ ይሄንን ያለችው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ አዲስ አበባ በሚገኘው የአውስትራሊያ ኤምባሲ ሽልማቱን አስመልክታ ባዘጋጀችው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነበር፡፡
ብሄራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ለሰርከስ ትርዒት ስትወጣም የ8 ዓመት ሕጻን ነበረች። የ9 እና የ11 ዓመት ታዳጊ እያለች ደግሞ የጂምናዚየም ሻምፒዮን እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼ ከሰጡኝ ስጦታ አንዱና ትልቁ በምፈልገው ሙያ ላይ እንድሰማራ መፍቀዳቸው ነው›› ትላለች - ወ/ሮ ሶስና፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ከልጅነቴ ጀምሮ በሰርከስ ስራ ብታወቅም የአውስትራሊያ ወጣትና ታዳጊዎች፤ ከአደንዛዥ እፅና ከአልኮል ነፃ እንዲሆኑ ሰፊ ስራ ስሰራ ቆይቻለሁ›› የምትለው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ፤ ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ወደ አውስትራሊያ ለሚገቡ ስደተኞች ሥልጠና በመስጠትና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሥራ ላይ መሳተፏንም ትገልጻለች፡፡ በአውስትራሊያ ‹‹ሊደንግ›› በተባለው ኩባንያ ስር በሚገኘው ‹‹ሰርከስወዝ›› ውስጥ ለዘጠኝ አመት በማገልገልና በቦርድ ደረጃም ድርጅቱን በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን የምትናገረው ወ/ሮ ሶስና፤ ሦስት ፊልሞችን እንደሰራችና መፃሕፍት ማዘጋጀቷንም አብራርታለች፡፡  እነዚህ ሁሉ ተደምረው ነው እንግዲህ “Order of Australia” ለተሰኘው የአውስትራሊያ ከፍተኛ ሽልማት የበቃችው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ‹‹ጋሞ ሰርከስ ስኩል ኦፍ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ተቋም በአዲስ አበባ በመክፈት ከአራት የመንግስት ት/ቤት የተውጣጡ ተማሪዎችን ሰርከስ በነፃ በማሰልጠን ላይ ትገኛለች፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊያን ወጣት የሰርከስ ባለሙያዎች በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉና እንዲያሸንፉ እገዛም ታደርጋለች፡፡ ‹‹ለሽልማቱ ከተጠቆምኩ በኋላ የሽልማቱ ድርጅቱ ባደረገው የሁለት ዓመት ጥናት፣ እንደ አውስትራሊያዊ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊትም ለወገኔ የማደርገውን አስተዋጽኦም ገምግመዋል›› ስትል አስረድታለች - ወ/ሮ ሶስና፡፡
የ10 እና የ6 ዓመት ልጆች ያሏት ወ/ሮ ሶስና፤ ኢትዮጵያ እንደሌላው ዓለም አገር አቀፍ የሰርከስ ት/ቤት በመንግስት ደረጃ እንዲቋቋም ትፈልጋለች፡፡ ምክንያቷንም ስትገልጽ፤ ሰርከስ ልጆችን በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ ለማድረግ የሚረዳ የስፖርት ሳይንስ ነው ትላለች፡፡
ወ/ሮ ሶስና ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሽልማቶችን በአውስትራሊያ አሸንፋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም ‹‹People Choice Award›› የተሰኘውን የመጀመሪያዋን ሽልማት ከሲድኒዋ ልዕልት እጅ ተቀብላለች፡፡ በ2004 ዓ.ም ደግሞ “Young Australian of the Year” የተሰኘውን ወጣቶችን የሚያበረታታ ሽልማት ተቀብላለች - ምርጥ አራቶች ውስጥ በመግባት፡፡ በ2007 ዓ.ም  “Australian of the Year” ለተሰኘው የአገሪቱ ሽልማት ለመታጨት የበቃች ሲሆን በ2013 ዓ.ም ደግሞ “The most Influencial African Australian of the year” የተባለውን ሽልማት ከአውስትራሊያ ፓርላማ ተቀብላለች፡፡ እነሆ ዘንድሮ ደግሞ “Order of Australia” በሚል የሚታወቀውን የአውስትራሊያ ከፍተኛውን ሽልማት  ለመሸለም በቅታለች፡፡ ይሄንን ከፍተኛ የክብር ሽልማት ሀይለልዑል የተባለ ሌላም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ማግኘቱ ታውቋል፡፡


Read 1207 times