Saturday, 16 November 2019 13:04

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

    አዲስ ፀሐይ ስትወጣ
              ነግቶ “ዛሬ” ሲወለድ
              በ”ነገ” የሳቀው “ትናንት”
             ሄደ---ፊቱን አዙሮ
              ማልዶ ሳይሰናበት …
 አንድ ጊዜ፣ አንድ የውጭ አገር መጽሔት (New week) አንድ የካርቱን ቀልድ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ በካርቱኑ ላይ እግዜር አንድ የቴሌቪዥን ሾው ላይ አተኩሮ ይታያል፡፡ አጠገቡ የተከመሩትን ፋይሎች፣ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚጎርፉለትን --- (ኢ-ፍትሃዊነት ከነገሠባቸው ጭምር) ፖስታዎች፣ የስልክ ጥሪዎች፣ ፋክሶች፣ ኢ-ሜይሎች፣ ቴሌግራሞች፣ ለቅሶዎችና አቤቱታዎች----ዞር ብሎ አላያቸውም፡፡ ይህን ጉዳይ የሰማ አንድ ጉብል ተበሳጭቶ ጓደኛውን፡-
“ለመሆኑ አቤልና ቃየል ሲጋደሉ፣ እግዜር ምን እየሰራ ነበር?” በማለት ጠየቀው፡፡
ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው?  መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
***
በጥንት ዘመን አንድ የሊባኖስ ካሊፌት ነበር፤ ከብዙ ሚስቶቹ በጣም ብዙ ልጆችን ያፈራ፡፡ ከተለዩት ሚስቶቹ ከአንደኛዋ፣ ሁለት መንትያ ልጆች ነበሩት፡፡ ካሊድና ሙሴ የሚባሉ፡፡ አንደኛው ከሱ ጋር ሲያድግ፣ ሌላኛው የሌላ ግዛት ባለቤቶች ከነበሩት የእናቱ ቤተሰቦች ጋር ቤተ መንግስት ውስጥ አደገ፡፡
በተለያየ እምነት ታንፀው ያደጉት ሁለቱ መሳፍንት፣ በህፃንነት ጊዜ እንደተለያዩ፣ ከስማቸው በስተቀር ትዝታ ሳይኖራቸው ኖሩ፡፡ ለአቅመ አዳም ሲደርሱም ወግ ማዕረግ አይተው ለየግዛቶቻቸው የጦር አበጋዝ ለመሆን በቁ:: ሁለቱ መንታዎች በያሉበት ሆነው፣ አንዳንዴ በእንቅልፍ ልባቸው የሚሰሙት ድምጽ ነበር- “ይህንን ድምጽ አትዘንጋ! የሚጠብቅህ እሱ ነው” የሚል፡፡ ለዘመዶቻቸው ቢናገሩም “ቅዠት ይሆናል” ነበር ያሏቸው፡፡
በዚያን ጊዜ እኛን ጨምሮ በየትኛውም ኋላቀር አገር እንደነበረው፣ የመሳፍንቶች “እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ” ፉክክር ሳቢያ በሁለቱ ግዛቶች መሃል የድንበር ግጭት ተነሳ፡፡ በዘመኑ ልማድ፣ ከዘመቻ በፊት ሁለት ነገሮችን ማስቀደም የግድ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ወደ ቤተ እምነት መሄድና አማልክቶቹ እንዲያግዟቸው መለማመን ሲሆን ሁለተኛው ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ቤተ እምነት በጭለማ አቅንቶ፣ መቅደሱን ማቃጠል ነው:: ይህም የጠላቶቻቸው አማልክት በጦርነቱ እንዳይሳተፉና እንዳያሸንፉ ለማድረግ በሚተኙበት ሰዓት እንዲወድሙ ነበር፡፡
ሁለቱ ጦረኞች (the two rivals) ዝግጅታቸውን ጨርሰው ወደ ፍልሚያ ለመግባት ሲቃረቡ፣ በየፊናቸው የተቃራኒዎቻቸውን አማልክት ለማውደም፣ በሌሊት ወደ ቤተ እምነቶቻቸው ገሠገሱ፡፡
ሙሴ በእነ ካሊድ መቅደስ ደጅ ችቦውን ይዞ ሲጠጋ፤
“ቁም!” የሚል ነጎድጓዳማ ድምጽ ቀጥ አደረገው፡፡
“ማነህ?” ብሎ አልጠየቀም፡፡ አብሮት የኖረው ድምጽ ነው፡፡
“አንተ የኔ አምላክ አይደለህምን?”
“አትጠራጠር”
“እዚህ ምን ታደርጋለህ?”
“እዚህም “እኔ”፣ እዛም “እኔ” ነኝ”
“የምጠብቀው አንተን ነው፤ ትለኝ አልነበረምን?”
“ለካሊድም ይህንኑ እያልኩ ነው ያደገው”
ሙሴ ጦርነቱ ከወንድሙ ጋር መሆኑን ሲያውቅ ፈረሱን አዙሮ ተመለሰ፡፡
ካሊድም በዘመተበት መቅደስ ደጀፍ ባጋጠመውና በሰማው ነገር እያለቀሰ፣ ወደ ግዛቱ ሲመለስ ተገናኙ፡፡ እንዳሉት ሆነ፡፡ “ያመጣል መንገድ፣ ይወስዳል መንገድ”…
ወዳጄ፡- ህይወት የተፈጥሮ ስጦታ ናት:: መልካም ሆኖ ለመኖር ግን የያንዳንዱን ሰው ውስጣዊ ሰላምና ቅን ልቦና ይፈልጋል፡፡ ውስጣዊ ሰላም ራስን የመፈለጊያና የማወቂያ ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ ራስን ማወቅና መረዳት ደግሞ ሌሎችን እንድናውቅ ያግዘናል:: ሊቃውንቱ እንደሚሉት፤ “ራሱን የማያውቅ ሌሎችን አያውቅም”፡፡
ወዳጄ፡- የአንድን ሰው አእምሮ ለመክፈትና እውነተኛ ማንነቱን ለመረዳት ሲበሳጭ ወይም ሲመቸው የሚናገረውን በመስማት ወይም በፍቅርና በደግነት የሚፈልገውን ስናደርግለት በሚያሳየን “እሱነት” ብቻ መገመት፣ ሙሉነቱንና ጐደሎነቱን አያሳይም፡፡ ሌሎች ጊዜያዊና ተለዋዋጭ ነገሮች፣ ሰውየው ከሚገኝበት ሁኔታ ጋር ተደማምረው መጠናት አለባቸው፡፡ “እኔ ማን ነኝ?” የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ፣ “እኛ ማን ነን?” ፣ “አነሱ እነማን ናቸው?” የሚባሉ ጥያቄዎች አይመለሱም፡፡
በጋራ የሚነሱ ጥያቄዎችና የጋራ መልሶች፣ ለሁሉም ልክ የማይሆኑት ወይም ሁሉንም የማያስደስቱት በነዚህ ባህሪያት ምክንያት ነው:: እንደ ጥሩ ማህበረሰብ “ማሰብ” ከመቻል አስቀድሞ፣ እንደ “ብቁ” ግለሰብ (Integrated personality) በቦታችን መገኘት ወይም በትክክል ማሰብ ይኖርብናል፡፡ መልካም ባህልና ስልጣኔ፣ ዘመን ተሻጋሪ ወግና ልማድ የሚገነባው አስተዋይ አእምሮ ከተገነባ በኋላ ነው፡፡ አለበለዚያ በድቡሽት ላይ እንደታነፀ ቤት፣ ሲነጋ እንደሚናድ የሆያሆዬ ዳስ---ስልጣኔ ደብዛውን ያጠፋዋል፡፡ እንደ ባከነ ዕድሜ የጊዜ ቁጥር እንጂ በአንድ ወቅት “ስለመኖሩ” የሚመሰክር ውል አይገኝም፡፡
እንዳኮረፈ ትናንትና ትዝታው ይሟሽሻል፡፡ ገጣሚው፡-
አዲስ ፀሐይ ስትወጣ
ነግቶ “ዛሬ” ሲወለድ
በ”ነገ” የሳቀው “ትናንት”
ሄደ---ፊቱን አዙሮ
ማልዶ ሳይሰናበት … እንዳለው፡፡
ወዳጄ፡- ዘርተን ባላጨድንበት፣ ላልኖርንበትና ለማናውቀው ጊዜ ሐውልት ማቆም፤ “ላለፈ ክረምት ቤት እንደ መስራት” የሚቆጠር የዋህነት ነው፡፡ ሰው በህይወት የሚንቀሳቀሰው በሚመገበው ምግብ ነው፡፡ ከሚመገበው ውስጥ ሰውነታችን የሚጠቅመውን እየተገነባበት፣ የማይጠቅመውን ያስወግዳል፡፡ እኛና ትናንትና የተሳሰርነው በሚጠቅም ንጥረ ነገር ነው --- “ዛሬ” በተሰራበት፡፡ ታሪክና ሃውልትም እንዲሁ ነው፡፡ ጠቃሚው በስልጣኔ እየታደሰ የአገር መኩሪያ ይሆናል፡፡ አክሱምና ላሊበላን፣ የሀረር ግንብና የአባጅፋር ቤተ መንግስትን ጨምሮ የዓለማችን ትንግርቶች (Wonders of the world) የዚሁ ምሳሌ ናቸው፡፡ የማይጠቅሙና የስልጣኔ ግብዓት የማይሆኑት ደግሞ (ሰውነታችን የሚጠቅመውን ወስዶ የማይጠቅመውን እንዳስወገደው) ፍሬከርስኪ ወሬዎችና ጊዜ ያለፈባቸው፣ በተረት መሰረት ላይ የተገነቡ ሃውልቶችም ዛሬን ያቆሽሻሉ እንጂ ነገ ላይ የሉም፡፡ ያሳፍራሉዋ!!
***
ወደ ካርቱናችን ስንመለስ፡- የኛ ጆቢራ ---
“አቤልና ቃየል ሲጋደሉ፣ እግዜር ምን እየሰራ ነበር?” በማለት ጓደኛውን ሲጠይቀው
“አሁን እንኳ ተኝቶ ነው፤ ቅድም የጄ. ሲምፕሰንን ጉዳይ ሲከታተል ነበር” አለው -- በሰማይ አቆጣጠር፡፡
በነገራችን ላይ “When you learn your worth, you will stop giving people discounts” ያለው ማን ነበር?
አንድ የመጨረሻ ጥያቄ፡- እግዜር መንታዎቹ ወንድማማቾች እንዳይዋጉ ሲያደርግ፣ አቤልና ቃየል ላይ ለምን የጨከነ ይመስልሃል?
ሠላም!!  


Read 1247 times