Print this page
Saturday, 16 November 2019 13:06

“ለዛ የአድማጮች ሽልማት” - በእኔ እይታ

Written by  በኤርምያስ ሥሜ
Rate this item
(0 votes)

  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሃገራችን የተለያዩ የሽልማት ድርጅቶች እያቆጠቆጡ መጥተዋል፡፡ ምንም እንኳ በርካታ በውጥን የቀሩና ተጀምረው የተቋረጡ የሽልማት ድርጅቶች ቢኖሩም፣ በጣት የሚቆጠሩት ለዓመታት መዝለቅ ችለዋል፡፡ በዚህ ረገድ በሃገራችን የመጀመሪያው የሆነውና ላለፉት 13 ዓመታት ያለመቋረጥ የተዘጋጀው ‹የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል› በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ‹ጉማ› እና ‹ለዛ› የተሰኙ የሽልማት ድርጅቶች ደግሞ ይከተላሉ፡፡ እነዚህን መሰል የሽልማት ድርጅቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በመወያየትና በመተራረም ማሻሻልና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡
ዛሬ የማተኩረው ‹ለዛ የአድማጮች ሽልማት› ላይ ይሆናል፡፡ የጽሁፌ ሃሳብ የሚያጠነጥነው በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ ሳይሆን በሸላሚው ድርጅት የአሰራር እንከኖች ላይ ነው፡፡ ዓላማዬ ደግሞ እኒህን መሰል የሽልማት ድርጅቶች አድገውና ጠንክረው፣ ለዓመታት የሚዘልቁ ይሆኑ ዘንድ ገንቢ አስተያየቶችን መሰንዘር ነው::
‹ለዛ› የአድማጮች ሽልማት የሚዘጋጀው በብርሀኑ ድጋፌ የማስታወቂያ ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡ ስያሜውን ያገኘው ‹ለዛ› በሚል መጠሪያ በሸገር ሬዲዮ ከሚቀርበው የመዝናኛ ፕሮግራም ነው፡፡ ድርጅቱ ትኩረት ያደረገባቸው የሽልማት ዘርፎች 12 ሲሆኑ የሽልማት ሥነሥርዓቱ፣ የዘንድሮውን ጨምሮ ለ9ኛ ጊዜ ተዘጋጅቷል፡፡ ስያሜው እንደሚያመለክተው፣ ለሽልማት የሚበቁት አሸናፊዎች የሚመረጡት አድማጮች በሚሰጡት ድምጽ ነው፡፡ ድርጅቱ ለሽልማት የሚያወዳድረው በድፍን ሀገሪቱ የወጡ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ሲሆን መራጩም በድፍን ሀገሪቱ ያለ አድማጭ ነው፡፡ የአድማጮች ምርጫ የሚሰበሰበውም በኢንተርኔት አማካኝነት በሚሰጥ ድምጽ ነው፡፡
የሽልማት ድርጅቱ መሰረታዊ የአሰራር ግድፈት ከዚህ ሂደት ይጀምራል፡፡ ለመሆኑ መራጭና ተመራጮች እነማናቸው? የሚያገናኛቸውስ ምንድነው? ከሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ስንነሳ፣ መራጭና ተመራጭ በሁለት የተለያየ ሜዳ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ሊገናኙ የሚችሉበት መንገድም አለመኖሩን  እንገነዘባለን፡፡ በድርጅቱ አሰራር መሰረት፤ በድፍን ሀገሪቱ ያሉ የጥበብ ስራዎች ለሽልማት  የሚመረጡት በ‹ለዛ› ፕሮግራም አድማጮች  ነው፡፡ የ‹ለዛ› ፕሮግራም አድማጮች ደግሞ ከድፍን የሃገሪቱ ህዝብ አንጻር፣ ኢምንት እንደሚሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ አድማጮች የሚሰጡት ድምፅ እንዴት ድፍን ሀገሪቱን ሊወክል ይችላል? “የዓመቱ ምርጥ” የሚል ስያሜንስ እንዴት መስጠት ይቻላል?
እንደሚታወቀው በዓመት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ የኪነ ጥበብ ስራዎች ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች ደግሞ በስርጭታቸው፣ በጥበባዊ ዋጋቸው፣ በትኩረት አቅጣጫቸው (Target Audience) እንዲሁም በአላማቸው የተለያዩ ናቸው፡፡ አድማጭ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍልም እንዲሁ  በፍላጎት፣ ለጥበቡ ባለው ቅርበትና ርቀት፣ እንዲሁም በዕውቀት ደረጃው የተለያየ ነው፡፡  እነዚህን ሁለት የተለያዩ አካላት (መራጭና ተመራጭ) የሚያገናኝ መስፈርት ያበጀ፣ በተወሰኑ አድማጮችና የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ የሚያተኩር አሰራር መከተል የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በየዓመቱ የድፍን ሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ስራዎች በጅምላ ለውድድር ይቀርባሉ፡፡ አሸናፊዎችም፣ የ‹ለዛ አድማጮች› በሚሰጡት ድምጽ  ይመረጣሉ፡፡
ለመሆኑ ‹ለዛ› የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ምን ያህል ህዝብ ጋ ይደርሳል? ሸገር ሬዲዮ ተደራሽነቱ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ‹ለዛ› ምን ያህል አድማጮች አሉት? የፕሮግራሙ አድማጮች ምን አይነት ናቸው? የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪ፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 15% በመቶ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ስሌት፣ ጣቢያው የሚደርሰው ከሀገሪቱ 15 በመቶ ያህሉን ህዝብ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ምን ያህሉ ሬዲዮ ያዳምጣል? ምን ያህሉስ የሸገር አድማጭ ነው? ስንቱ የለዛ ፕሮግራምን ያዳምጣል? --- የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳትና መፈተሽ የግድ ይላል፡፡
ወደ መራጩ እንምጣ፡፡ መራጩ ድምጽ እንዲሰጥ ጥሪ የሚደረግለት ለውድድር በቀረቡ የተወሰኑ (አይነትና ደረጃ በወጣላቸው ወይም ለዚህ ውድድር በሚል በተመዘገቡ) የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ሳይሆን በድፍን ሀገሪቱ በወጡ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ላይ ነው፡፡ ድምጽ የሚሰጠውም በኢንተርኔት አማካኝነት ነው:: ምን ያህል ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው? ባለፈው አመት በወጣው የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት፤ በመላው ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ 18 በመቶ ያህሉ ህዝብ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን በኢንተርኔት አማካኝነት ድምጽ ሊሰጥ የሚችለውን የለዛ አድማጭ፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር  መገመት አያዳግትም፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት የዳኝነት ጉዳይ ነው:: የ‹ለዛ› ሽልማት፣ ዳኝነቱን የሚያከናውነው እንዴትና በማን ነው? ጥያቄውን ያነሳሁት ዳኝነቱ የሚከናወነው በህዝብም በባለሙያም እንደሆነ ስለሰማሁ ነው፡፡ የዳኝነት ጉዳይ ግን ፍፁም ግልፅነትን የሚሻ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ያለበለዚያ የሽልማት ተቋሙ የተዓማኒነት ችግር ይገጥመዋል፡፡ በጊዜ ሂደትም የሽልማቱን ክብርና ተቀባይነት እየሸረሸረው መሄዱ አይቀርም:: ዓመታዊ የሽልማት ሥነሥርዓት ከተከናወነ በኋላ እዚህም እዚያም የሚሰሙ የአርቲስቶች (የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች) ቅሬታና ውዝግብ ምንጩ፣ በአሸናፊዎች አመራረጥ ላይ ግልጽነት አለመኖሩ ይመስለኛል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ‹ለዛ የአድማጮች ሽልማት› ላለፉት ዓመታት ሳይቋረጥ መዝለቁ በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡ የሽልማቱ መሥራችና አዘጋጅ ብርሃኑ ድጋፌም ምስጋና ይገባዋል፡፡

Read 1187 times