Saturday, 16 November 2019 13:06

“የኢትዮጵያ ችግር ግማሽ እውነት ላይ ነው”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

    በ40 ዓመታችን 18 አልሞላንም

           ገጣሚና ደራሲ ታገል ሰይፉ “ፍቅር”፣ “ቀፎውን አትንኩት”፣ “የሃምሳ አለቃ ገብሩ”፣ “ሌዋታን” “የሰዶም ፍዳ”፣ “በሚመጣው ሰንበት” የተሰኙ መጻሕፍትን ያሳተመ ሲሆን፣ በምስል የተቀነባበሩ አዝናኝ ግጥሞችንም ለሕዝብ አቅርቧል፡፡ በቅርቡም በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሃምሳ አለቃ ገብሩን በምስል እያቀረበ ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አነጋጋሪ በሆነ ርዕስ የወቅቱን ትኩሳት የሚመስል የልቦለድ ስራ ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ የአዲስ አድማሱ ደረጀ በላይነህ ከገጣሚ ታገል ሰይፉ ጋር በአዲሱ መጽሐፉ ዙሪያ በስፋት አነጋግሮታል፡፡ በልብወለዱ ውስጥ የቀረበውን ፖለቲካ ወለድ ታሪክ ከዛሬው ተጨባጭ የአገራችን ፖለቲካዊ እውነታ ጋር እያወዳደሩና እያነፃፀሩ ግሩም አውግተዋል፡፡ ማራኪ ጭውውት እነሆ፡-


             ይህንን አዲሱን መጽሐፍ እንዴት ጀመርከው? አንዳንዴ ፖለቲካ የምታሸት ይመስላል፤  “ሌዋታን” የተሰኘውን መጽሐፍ ያወጣህ ጊዜም ከመንግስት ጋር አጋጭቶህ ጣጣ ውስጥ ገብተህ ነበር፡፡ ይህኛው የሀገር ጉዳይ ይሁን እንጂ ፖለቲካ ቀመስ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር እንዴት ነው? ስስነትም ይታይበታል፡፡
ልቦለድ መጽሐፍን በተመለከተ ከሰዓሊዎች ጋር ነው የማገናኘው፡፡
ሰዓሊ ጓደኞች ነበሩኝ፤ ለምሳሌ መስፍን ሀብተማርያምን ልጠቅስልህ እችላለሁ፡፡ ጐበዝ ሰዓሊ ነው፤ አንዳንዴ ግጥም ይጽፋል:: እንደርሱው አልፎ አልፎ ግጥም የሚጽፉ ሰዓሊዎችን አውቃለሁ፡፡ የእሸቱ ጥሩነህን፤  የበቀለ መኮንን ግጥሞች አንብቤያለሁ፤ እና ጠጋ ያልኳቸው ሰዓሊዎች ጋ ያየሁት፣ በብሩሻቸው ሄደው ሄደው ሊደርሱበት ያልቻሉትን ነገር በግጥም ሊነኩት ነው፡፡ ይህ በግጥም ካልሆነ ሊነካ አይችልም፣ በሚል መቋጫ የሚያደርጉለት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ነው የሰዓልያን ግጥም ለየት የሚልብኝ፡፡ መንገዱ ያ ብቻ ነው፡፡
በኔም ህይወት ውስጥ የሀገራችንን ፖለቲካ በግጥም ልደርስበት ያቅተኛል፣ ይሰፋብኛል፣ ይገዝፍብኛል፤ ነውጡንና ዝብርቅርቁን “እንዴት አድርጌ ስንኞችን ላሸክም?” ስል በዝርው ካልሆነና አደማሱን ካላሰፋሁት ልገልፀው የማልችልበት ደረጃ ስሜቴና ቁጣዬ ሲደርስ በዝርው እጽፋለሁ፡፡ መጽሐፉን የጀመርኩት.. “እፎይታ” መጽሔት ላይ የወጣው “የግንቦት ህልም” የሚለውን አጭር ልቦለዴን ስፅፍ፣ የዚህ ዓይነት አተያይ መጀመሬ ትዝ ይለኛል:: ያኔ ኢህአዴግ ሲገባ የነበረውን ትዕይንት ጽፌው፣ ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር ሸገር ሬዲዮን ጨምሮ ብዙ ሬዲዮ ጣቢያዎች ይተርኩታል:: ከዚያ በኋላ ፋናና የመንግሥት ሚዲያ ላይ በነበርኩበት ጊዜ የማየውን ነገር “ሌዋታን” በሚለው መጽሐፌ ለንባብ አብቅቸዋለሁ፡፡ ያም በግጥም ልገልፀው የማልችለው ዓለም ነበር፡፡
አሁንም “ብሰጦሽቁዋጭ ቁዋጣሽቆር” በሚለው አዲሱ መጽሐፌ ላይ የሚታየውም እሱ ነው፡፡
ርዕሱን አንተ በቀላሉ ትጠራዋለህ፤ ለኔና መሰሎቼ ግን ዳገት ሆኖብናል፤ ከየት ነው ያመጣኸው?
እንግዲህ አንተን ጨምሮ አለማየሁ ገላጋይም ርዕሱ ከበድ ይላል ትላላችሁ፡፡ ከኑሯችን ግን አይከብድም፡፡ ሀገሪቱ እኔ ከሰጡሀት ርዕስ የከበደ ህይወት ውስጥ ናት፡፡ ያንንም መጽሐፉ ውስጥ ታየዋለህ፡፡ እዚያ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆኜ ሳየው፣ የርዕሱ ክብደት ብዙ አይታየኝም፡፡ ብዙ ሰዎች የመፍሐፉን ርዕስ ካነበቡ በኋላ ርዕሱ ከባድ ነው ይሉኛል፡፡ “ውስጡን አንብቡትና የዚህን መጽሐፍ ሃሳብ እዩትና… ከዚህ የቀለለ ርዕስ ካላችሁ ንገሩኝ” ስላቸው “አይ ይሁን” የሚሉኝ ይበዛሉ፡፡ ውስብስብነቱ አሁን መጽሐፉ ውስጥ ከምንኖረው ኑሮ አይብስም:: አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ሞትን በቀላሉ እንኖረውና “ሞት” የሚለውን ስም ስንሰማው ግን “አታንሱብኝ” እንላለን፡፡ “ሞትንስሙን አትጥራብኝ”  ብሎ እሪሪ የሚልብህ ሰው፣ ጠጋ ብለህ ሥታየው ከሞት የከፋ ኑሮ ነው የሚኖረው፡፡    
የስነ ግጥም ሊቃውንት፤ ጥሩ ግጥም ሞትን እንኳ ዘና አድርጐ ያቀርባል ይላሉ፡፡ አንተ ደግሞ በዚህ በዝርው መጽሐፍም የሚያስቁና ዘና አርጌዎች ይታዩበታል፤ መጽሐፉ ውስጥ ያለውን ህመምና ጥያቄ (በአደባባይ አሁን የምናየውን ሰቀቀን) ይዟል፡፡ ኮሚክ ነገርና ስላቅ ትወዳለህ ልበል?
በነገርህ ላይ እማማ ኩንዳሬ የሚባሉትን ገፀ ባህሪ የኮሚኩን ቦታ እንዲጫወቱ የጨመርኳቸው፤ ባለፈው ዓመት ነው ከዚያ ውጭ የነበሩት 2005 ዓ.ም ላይ ነው የተፃፉት:: መራር የህይወት ክፍሎቹ የተፃፉት ቀደም ብለው ነው፡፡
ያኔ የነበረው ነገር እስካሁን አልተለወጠም እያልከኝ ነው? ወይስ ትንቢት መናገር ጀምረህ ነው?
እኔ ከእማማ ኩንዳሬ ውጭ ያለውን ታሪክ ስሰራ መራር ነበር፡፡ 2011 ዓ.ም ላይ አጫዋቹን ክፍል የጨመርኩት ጉዳዩ መራር ስለሆነ፣ ሌላ ገፀ ባህሪ ልጨምርና ለቀቅ ላድርገው ብዬ ነው፡፡ ትንሽ ፈገግ የሚያሰኝ ቅመም ገፀ ባህሪ ያስፈልገዋል ብዬ አሰብኩ፡፡ የመረረውን አንባቢ ሌላ መራራ ነገር ጥሬውን አቀርብለታለሁ በሚል ጣል አደረግሁበት፡፡ ይህን ዘመን ይመስላል ያልከው… ታሪክ የተፃፈው 2005 ዓ.ም ነው፡፡ ስጽፈው አሁን የሚታየው ችግር አልተከሰተም ነበር፡፡ የዚህን መነሻ ሃሳብ ያገኘሁት በአጋጣሚ ደቡብ ሄጄ በሰማሁት አሳዛኝ የብሔር ልዩነት ጉዳይ ውስጤን ተጐትጉቼ ነው፡፡ ወገን ለወገኑ መልካም ሲያደርግ ሊሰጥ የሚገባው አክብሮት ለሽሙጥ በተዳረገበት አጋጣሚ ደርሼ አመመኝ:: መጽሐፌን የጀመርኩት ያኔ ነው፡፡
አንዳንዴ አዲስ አበባ መጥቼ ከጉዳዩ ስርቅ የተወሰኑ ምዕራፎች እሄድና ሌላ ዓለም ሳይ፣ “ይሄ የፃፍኩት ዓለም ኢትዮጵያን አይወክልም”፤ እያልኩ አቆመው ነበር፡፡ እንደገና ደግሞ ሌላ ግጭት ሲነሳ ቱግ ይልብኛል፡፡ ስለዚህ ይህን ሥራ ባለፉት ዓመታት ዞር ብዬም አላየሁትም ነበር፡፡ አሁን ነገሩ እየባሰ ሲመጣ፣ በተለይ አቶ በቀለ ገርባ የሚባሉት ሰውዬ “በክልላችሁ ሰዎች ሲመጡ፣ በቋንቋችሁ ካላናገሯችሁ አታናግሯቸው” ያሉትን ስሰማ ደነገጥኩ:: እኔ ይህንን በ2005 ዓ.ም ጽፌዋለሁ፡፡ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ኑፋንቅ የምትባለው ከተማ፣ “በራሳቸው ቋንቋ ካላናገሯችሁ ዝጓቸው” ብዬ ጽፌው ስለነበር የኒህን ምሁር ንግግር ስሰማ ደነገጥኩ፡፡ “እንዴት አንድ ሊሆን ቻለ?” ብዬ ይህ መጽሐፍ ማለቅ አለበት” አልኩ፡፡ መስከረም ሳይጠባ ማተሚያ ቤት ገብቶ፣ ጳጉሜ ላይ መጽሐፉን ለሰዎች ሁሉ በትኜ ነበር፤…ላንተም ደርሷል፡፡ ሳነበው ይህ ከሆነ በኋላ እንደገና “ጠባቂዎቼ ተነሱብኝ” በሚል ሰበብ ሌላ አሰቃቂ ግጭት ተፈጠረ፡፡
መጽሐፉ ጀርባ ላይ የተፃፈውን ሳነበው፣ አሁን አይቼ የፃፍኩት እስኪመስል ድረስ ተገጣጠመ፤ መጽሐፉን የሰጠኋችሁ ሰዎች ብቻ ናችሁ የምታምኑኝ፤ ግን ይህ ሁሉ የተፃፈው 2005 ላይ ነው፡፡
እኔ የተረዳሁት የብሔር ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች አካባቢ ያለው ችግር፣ የትም ክልል ቢሆን ተመሳሳይ መሆኑን ነው፡፡
የመጽሐፉ የፊት ሽፋን ላይ ያለው ጫማ  ሰሞኑን ያለንበትን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከት የሚያስታውስ ነው፤ ይኸኛውስ ግጥምጥሞሽ እንዴት ነው?
ይህንንም ያሰብኩት እዚያው ሆኜ ነበር:: አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በማይረባ ምክንያት “ይሄ ጠፋብኝ፤ ይሄ ጠፋብኝ” ተባብለው ብዙ ሰዎች ሞቱ፤
/የዩኒቨርስቲውን ስም ብነግርህ ጉዳዩን ከመጽሐፉ ታሪክ ጋር እንዳያይዙት ልለፈው/ ይህን ሳይ በአንድ እግር ጫማ መጥፋት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙ ሰዎች አለቁ፡፡ የሀገሪቱን ችግር ይፈታሉ የተባሉ ወጣቶች፣ የማይረባ ጥፋትና ችግር የሚፈጥሩና የሚጋደሉ ከሆነ ተመርቀው ወጥተውስ ምን ሊሠሩ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያቺን ጫማ ያደረኩት ለዚያ ነው፡፡ ዋናው መልዕክት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ታትሞ ቅዳሜ እየተሰራጨ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች ተገዳደሉ፡፡ ድርጊቱ በትክክሉ የወቅቱ ጉዳይ መሆኑን አሳስቦኛል፡፡
ገፀ ባህሪያት አሳሳል ላይ ወደ ውስጥና ገብተህ… ስነልቦናዊ ቅርፃቸው ላይ አላተኮርክም:: እኔ ሳውቅህ ብዙ ጊዜ የፍሮይድንና የእነ ኤሪክ ኤሪክሰንን ሳይቀር እየተነተንክ መፈተሽ ትወዳለህ፡፡ አሁን ግን ይህን ቸል ያልክበት ምክንያት አልገባኝም፡፡
እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ችግር አጠቃላይ መንስዔው ጅምላ ፍረጃ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
“አሁን ስለምተርክላችሁ ታሪክ ምክትል ዋና ልጅ ለምልሙን ጅባካን ብትጠይቁት ሁሉም ነገር የተጀመረው ቅዳሜ ምሽት ነው” ይላችኋል:: ቅዳሜ ምሽት ስም አይጠሬው ፕሬዚዳንት ካደረጉት ንግግር ነው፣ የዘረኝነቱ ህይወት የጀመረው” ነው የሚለው፡፡
ችግሩ ይህ ከላይ ያነበብከው ያለመሆኑን ለማየት ነው ታሪኩ የሚቀጥለው፡፡ ችግራችን የተጀመረው በዘር መፈረጅ ስንጀምር አይደለም፤ ከዚያም በፊት የነበሩትን የሚዲያ ስራዎች ይጨምራል፡፡ እነ አቶ መለስ ስልጣን ይዘው “ዴሞክራሲያዊ መንግሥት” ካሉ ጀምሮ ያለውን ብታይ፣ በብሔር ውስጥ የማይገለጥ ሌላ ፍረጃ ነበር፡፡ አቶ መለስ የተናገሩት ንግግር በሙሉ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድም ቀን “ጥሩ ነው” ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ መለስ ያሉት በሙሉ ስህተት ነው፡፡ እነ አቶ መለስ ጋ ስትሄድ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎች የተናገሩት “ጥሩ ነው” ብለው አያውቁም፤ ጅምላ ፍረጃው ከዚህ ይጀምራል፡፡ እና የችግራችን ምንጭ ዘረኝነት ሳይሆን ጅምላ ፍረጃ ነው፡፡ ዘረኝነቱ እንኳ ቢቆም ፍረጃውን ካልተውን፣ ቀለምና ስሙን ቀይሮ ብቅ ይላል፡፡ መጀመሪያም ችግሩ ነበረ፤ አሁን ዘረኝነት ሲመጣ ታጅቦ መጣ እንጂ፣ ቀድሞም ነበረ፡፡
ስለ ጅምላ ፍረጃና ልኬት ሳስብ እዚህ ሀገር 18 ዓመት የሞላው ሁሉ ይምረጥ! ሲባል “እኛ 18 ዓመት መቸ ሞላን” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህን ጅምላ ፍረጃ የሚፈጥረው የመለካትና የመተንተን ችሎታ ማነስ ነው፡፡ የኔ ሃሳብ ነገሮችን በቅጡ መለካት አንችልም ነው:: ይህንን ደግሞ “ሌዋታን” የሚለው መጽሐፌ ላይ በሰፊው ሄጄበታለሁ፡፡ “መለካት አንችልም” ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ “መቼ ሰው ሞቶልኝ ድንኳን ተቀምጬ፣ ንፍሮ እየበላሁ ሳስተዛዝን ቀኑ በተገፋልኝ” እያለ የሚያስብ ሥራ ፈት ሰው፣ የዕድር ጥሩንባ ሰምቶ ጧት ወጥቶ ዕቃ አውጥቶ፣ ሶስት ቀን ድንዟን ተቀምጦ፣ ካርታ እየተጫወተ ቢያሳልፍ፤ አንተ ደግሞ በጣም ታታሪ ሆነህ ጊዜ አጥተህ ቀብረህ ብትመለስ፣ ሁለታችሁ ለምርጫ ብትወዳደሩ የሀገራችን ህዝብ የሚመርጠው ያኛውን ሰው ነው… “ቀባሪዬ… ከቀብር የማይጠፋ አስተሳዛኝ” እያለ ያደንቀዋል፤ ችግራችን ከዚህ ይጀምራል፡፡
የሰለጠነው ዓለም “18 ዓመት የሞላው ሰው ይምረጥ” ሲል ያለ ምክንያት አይደለም:: አንድ ዜጋ በዚያ ዕድሜው፣ ምክንያታዊነት ልኬትን፣ ትንታኔን፣ ራስን መቻልን አውቆና ኖሮ ከቤት የሚወጣበት ነው፡፡ ገና በ4 ዓመቱ ክፍል ተለይቶለት፣ የራሱን ክፍል በኃላፊነት መምራት የሚችል ሙሉ ዓለም ያለው ነው፡፡ እኛ በ40 ዓመታችን ከእናታችን ጋር የምንተኛ ነን:: ስለዚህ ሙሉነት የሌለው፣ “እናቱ ከጐረቤት ሲጣሉ፣ ተደርቦ መጣላትን ያልተወ ሰው… “ልክ ነው? ልክ አይደለም?” በማይል መለኪያ ቢስነት አድጐ በዕድሜ ሊመዘን አይገባውም፡፡ በ40 ዓመታችን ገና 18 ዓመት ያልገባን ብዙ ነን:: ጅምላ ፍረጃም የሚፈጠረው ከዚሁ የሚዛን መዛባት ነው እያልኩ ነው፡፡
ዘረኝነት የጅምላ ፍረጃ አንዱ መገለጫ እንጂ ዋናው በሽታ ዘረኝነቱ አይደለም፡፡ መመታት ያለበት ጅምላ ፍረጃ ነው፤ እርሱ ከተመታ ትክክለኛ ሰዎች ሥልጣን ላይ ይወጣሉ፡፡
አዲስ አበባም ውስጥ “ዘረኛ አይደለሁም” ብሎ ገበሬውን የሚታዘበው የአዲስ አበባ ሰው… ብትፈትሽው ፈራጅ ነው፡፡ ገና 18 ዓመት አልሞላውም፡፡ ስለ ዘር ስለማያወራ ብቻ ራሱን “ስልጡን ነኝ” ብሎ ያስባል፡፡ አንዱ ችግራችን ይህ ነው፡፡
ችግራችን ሥነ ልቡናዊ ነው እያልከኝ ነው?
ችግራችን የመለካት ችሎታ ማነስ ነው፡፡ የንቃተ ህሊና ማነስ ነው፡፡
ችግሩ ከምን የመጣ ይመስልሃል?
ከአስተዳደግም ከባህልም የተወራረሰ ይመስለኛል፡፡ በቡድን የማሰብ ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ አንበሳን እናደንቃለን እንጂ ባህሪያችን የሚያደላው ወደ ጅብ መንጋነት ነው፡፡ ስታጠቃም በቡድን ነው፡፡ ብዙ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሳይቀር ቡድን አለ፡፡ ስብሰባ ላይ ተከፋፍለህ ትተጋተጋለህ፡፡ አንዳንዱ ስብሰባ ላይ ገና እጅ ሳያወጣ ደግፎሃል፡፡
ለምሳሌ እኔ ስድስት ጊዜ መጽሐፍ አሳትሜያለሁ፡፡ በዚያ ሂደት የታዘብኩትን ልንገርህ፡፡ አንዴ መንገድ ላይ አንድ ጋዜጠኛ ያገኘኝና፤ “መጽሐፍ አወጣህ አሉ?” አለኝ:: አዎ ስለው “አሪፍ አድርጌ እጽፍልሃለሁ” ይለኛል:: ይህንን ሲለኝ መጽሐፉን አላነበበውም፡፡ ወዳጄ ስለሆነ አሪፍም ባይሆን ይጽፍልኛል:: ይሄ ሰውዬ ቢጠምደኝ ምን ሊያደርግብኝ እንደሚችል አስብ፡፡ “እናቱን እጽፍበታለሁ” ነው የሚለኝ:: ፈርጆ ማሰብ ይህ ነው፡፡ ህዝቡን ሊለውጥ የሚችለው የሚዲያው ዓለም እንዲህ ከሆነ፣ ከህዝቡ ምን ትጠብቃለህ? ገና ነን! ገና ነን!
የመጽሐፉ መቸት አልተገለፀም፤ ገፀ ባህሪያቱና ቦታው አይታወቅም፡፡ አንባቢ ምናልባት ሊገምት ይችላል፤  ለዚያውም ብዙ ቀዳዳ ያለ አይመስልም፤ ይህንን ለምን አደረክ?
ይህን ያደረኩበት ምክንያት ለምሳሌ ጂባካን የተባለውን ገፀባህሪ ያይና “ይሄ አቦይ ስብሀት ነው፣ ይሄ ጀዋር ነው” እንዳይል ነው፡፡ እዚያ ነገር ውስጥ ከገባን ዋና መልዕክቴ አይተላለፍም፡፡ እንዲያውም የባሰ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ህወሓት ውስጥ እንከን ካየህ፣ የትግራይ ህዝብ ሁሉ “እኔን ሰደብከኝ” ሊልህ ነው፣ ፍረጃ ውስጥ ገብተናል፡፡ ህወሓት በዚህና በዚያ ጠንካራ ጐን አለው፤ በዚያ ደካማ ጐን አለው ማለት እንኳን አትችልም፡፡
ላንዱ ቡድን የጀዋር ነገር ሁሉ ወንጀል ነው:: ለሌላው ቡድን ደግሞ የጀዋር ነገር በሙሉ ጽድቅ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ችግር አለ፡፡ ይህን አፃፃፍ የተማርኩት ከአባቶቻችን ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” አለች አህያ ይሉሃል:: አህያ አፍ አውጥታ እንደማታውቅ የታወቀ ነው:: ይህን ሲሉ እገሌና  እገሌ ከሚፋጠጡ፣ በሰበብ መልዕክታቸውን ማስተላለፍ ፈልገው ነው:: እኔም ሌላ ዓለም፣ ሌላ ብሔር የፈጠርኩት ለዚያ ነው፡፡ አለዚያ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግራዋይ… ብለው “እኛን ነው፣ እኛ ነው” የሚለው ውስጥ መግባት ይመጣል፡፡
እኔ የምፈልገው ሁላችንም ከቡድን ወጥተን ወደ ሃሳብና ውይይት እንድናድግ ነው፡፡ የዘረኝነት አስከፊ ባህርይው ወደ ሃሳብ ያለማደጉ ነው፡፡ ወደ ውይይት አታድግም፡፡
የእውነቱን ግማሽ ጐን ነው የተለማመድነው፤ የሁሉ ነገራችን ችግር ይህ ነው፤ ዳገቱን ካየ ቁልቁለቱን አያይም፡፡ ሁሉም ከቆመበት ቦታ አንፃር አንደኛው “ዳገት ነው” ሲል፣ ሌላኛው “የለም ቁልቁለት ነው” ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ያለው ግማሽ እውነት ላይ ነው፡፡
ያጣነው ሙሉ እውነት ነው፤ ግማሽ እውነት ደግሞ የሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን አዳምን ያሳተው በግማሽ እውነት ነው፡፡ “እነ መለስ በዚህ በዚህ ጥሩ ሠርተዋል፤ በዚህ በዚህ ደግሞ አበላሽተዋል፡፡ እነ ዶክተር ዐቢይ በዚህ  ጥሩ ሠርተዋል፤ በዚህ ደግሞ ልክ አይደሉም የሚል ነው የሚያስፈልገን፡፡ ይህም መንግስት ይህን ማድረግ ተስኖታል፡፡ አጠገቡ የሰበሰባቸው ሰዎች እንደዚያው ናቸው፡፡ በዚህ መንግሥት ያሉ ሰዎች “መለስ ጥሩ ሠርቶ ነበር” ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህ? ታዲያ ለውጡ ምንድነው? እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጣ ብዬ የምለው ሚዛናዊነትና ከፍረጃ ነፃ ሆኖ ሳይ ነው፡፡
መጽሐፍህ ውስጥ “ዘመን” የሚል ጋዜጣ አለ፤ እንዴት ነው የሳልከው?
አንዳንድ ሰው ይህ “ዘመን” የሚለው ስያሜ ያሳስተዋል፣ በእውኑ ዓለም “ዘመን” የሚባል ጋዜጣ የለም፤ “አዲስ ዘመን” ነው፡፡ “ዘመን”ን በኔ መጽሐፍ ዐውድ ነው የሰራሁት፡፡ አዲስ ዘመን እኛን ሁሉ ያሳደገ  ጋዜጣ ነው፡፡ “ዘመን” የሚለውን ስያሜ የተጠቀምኩት ጊዜውን ስለሚያሳይ ነው፡፡ “ጊዜ” ልለው አስቤ፣ ጋዜጣና ጋዜጣ አልመስል ሲለኝ ተውኩት፡፡
መጽሐፍህ ውስጥ የጋዜጣው ሚና ምን ነበር?
የመንግስት ፕሬስን ሁኔታ የሚያሳይ ነው:: በዚህ ሁሉ ቀውጢ ውስጥ ያለውን ድርሻ ነው የሚያሳየው፡፡ በሁለት ነው የከፈልኩት፤ ማሳየት የፈለኩትም የመንግስትን ሁለት መልክ ነው፡፡ አንደኛው መልክ አንገብጋቢውን ነገር ቸል ማለት ሲሆን፤ በመጽሐፉ አውድ ዲባካ በተባለው ገፀ ባህሪ የሚካሄደውን የዘረኝነት አደጋ ቸል ማለት ነው፡፡ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የነበረው ሁኔታ ይህ ነው፡፡ ሁለተኛው በዚያው በሃያ ሰባት ዓመት የማይረባውን ጉዳይ ረዥምና ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ፣ ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን ያህል ቀን የፈጀ ጥልቅ ግሣገማ፣ ምናምን የሚለው ረዣዥም ስብሰባዎች ነበሩ:: የውድቀታችን ምልክት ይህ ነው፡፡ ችግሮችን ለማየት ሰዓት የሰጠውን ያህል ትክክለኛ ችግሮቹ ላይ አተኩሮ ቢሠራ ኖሮ፣ አሁን የገባንበት ነገር ውስጥ አንገባም ነበር… የሚል እምነት አለኝ:: ለምሳሌ የሃዋሳውን ግርግር ቀደም ብዬ “ይህ ነገር አደጋ አለው” በማለት የነገርኳቸው ታጋዮች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚያ ሰዎች በድርጅታቸው ፍቅር የታወሩ፣ የድርጅታቸውን መርህ እንደ እግዚአብሔር ቃል አምነው፤ የድርጅታችን መንገድ የጠራ መንገድ ነው፤ አንተ የምትለው ነገር አይደርስም” ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ አሁን እንደሚወራው ሀገር ለመበታተን የተነሱ ብዙ አላየሁም፡፡
ጥቂት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ አብሬያቸው የሠራኋቸው ሰዎች ግን ከድርጅታቸው ጋር በገቡት ፍቅር፣ ዐይናቸው ታውሮ ገደል የገቡ ናቸው፡፡ “ሌዋታን” በሚለው መጽሐፌ ገልጬ ነበር፡፡ ታጋይ ደሜ የዚህ ማሳያ ነው፡፡
ከህዝቡ ጋር ዘይትና ውሃ የሆነ ሰው ነው፡፡ ግን ሃቀኛ ታጋይ ነው፡፡ እኔ አንዳንዴ ህወሓት ተብሎ በጅምላ ሲፈረጅ እሸማቀቃለሁ፡፡ በጣም የማውቃቸው ሙስና ደጃቸው የማይደርስ፣ በህዝብ ፍቅር ያበዱ አሉ፡፡
አሁን ካሉት ዶክተር ዐቢይንና መሠሎቻቸውን እወዳቸዋለሁ፤ ግን “ህወሓት” ብለው በጅምላ ሲናገሩ ይከብደኛል፡፡ እኔ በ1984 ዓ.ም የኢህአዴግ ሚዲያ ላይ ስሰራ አባል አልነበርኩም፡፡ የምሠራው የመዝናኛ ገጽ ላይ ነው፡፡ እዚያ ሳያቸው “ሃያ አራቱም ሰዓት የድርጅቱ ነው፡፡” ብለው የሚያምኑ ነበሩ፡፡ የሚተኙት እንኳ ከድርጅቱ በተቀነሰ ጊዜ ነው ብለው የሚያስቡ፣ ሕዝቡ አይሳሳትም” የሚሉ ሕዝብን እያገለገልኩ ነው ብለው የሚደክሙ ምስኪን ታጋዮች አሉ፡፡ የነዚህን ታጋዮች ናሙና “ሌዋታን” ላይ ታየዋለህ፡፡
ሕወሓት ስል ብዙ ሀቀኞችን አስባለሁ:: ሩቅ ሳትሄድ አርከበ እቁባይን አስባለሁ፡፡ ማዘጋጃ አርከበ በነበረበት ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡ እንዴት ዓይነት ታታሪ ሰው እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ እስካሁን የማወራልህ፡፡ የጅምላ ፍረጃን ጠንቅ ነው፡፡
መጽሐፍህ ውስጥ ስለ እንጀራው ሲጨቃጨቁ እንቅልፍ የወሰዳቸው ልጆች ትዝ አሉኝ?
ሀገራችን ያለችበት ሁኔታና እኛ ያለንበት… ምን ያህል የሰማይና ምድር ያህል እንደሚራራቅ ለማሳየት የሞከርኩበት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“ይህ ሁሉ የሆነው ከተቆነጠጡ በኋላ ጥፋታቸው የማይነገራቸው ህፃናት፣ ልቅሶ ከሚያባራባቸው የሀገራችን ከተሞች በአንዱ ውስጥ ነው” ይላል፡፡ ችግራችን ከዚህ ይጀምራል:: ሕፃናትን እንኳ መትተን ለምን እንደተመቱ አንገራቸውም፡፡
ከዚህ ከተማ ላይ ከአንድ እንጀራ ስንት ግማሽ እንጀራ ይወጣል? እያሉ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሲከራከሩ፣ እንጀራውን ሳይበሉት እንደውም እንቅልፍ የሚወስዳቸው ሕፃናት ይበዛሉ::
እንግዲህ አስበው፤ ይህን ካሳየሁ በኋላ ነው፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ፣ ከአንድ እንጀራ ውስጥ ግማሽ እንጀራ ወጥቶ ስንት ስንት ይደርሰናል? እያሉ የሚጨነቁ ሕፃናት በበዙበት ዓለም ውስጥ... የሚቀድመው ለነርሱ እንጀራ ማቅረብ ነው? ወይስ በዘርና በጐሣ መከራ ማየት? የሚለውን ለንጽጽር ብዬ ነው የመጀመሪያውን ምዕራፍ በዚህ የጀመርኩት፡፡

Read 685 times