Saturday, 16 November 2019 13:01

‹‹Gold G ቴሌኮም›› ዝነኞችንና አድናቂዎቻቸውን በመረጃ ማገናኘት ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ጎልድ ጂ ቴሌኮም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ስለ ታዋቂ፣ ተወዳጅ፣ ዝነኛና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ማንኛውንም አይነት መረጃ የሚያቀርብ አሰራር ዘረጋ። አንድ ሰው ስለአንድ ተዋናይ ማንነት፣ ሥራ፣ ስለሕይወት ዘይቤው፣ ስለሚወደው ነገርና ስለማንኛውም ጉዳይ ወደ 8622 B ብሎ በመላክ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት የሚችል ሲሆን ያ ሰው ወደ 8622 B ልኮ ላገኘው መረጃ ወይም ለአንድ መልዕክት 1 ብር ብቻ እንደሚከፍል ‹‹የጎልድ ጂ›› ሀላፊዎች ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በሚገኘው WA ሕንጻ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ እንደ ሀላፊዎቹ ገለጻ ማንኛውም ሰው ስለ አርቲስቶች ማወቅ የሚፈልገውን መረጃ በተቀመጠው ካታጎሪ ገብቶ በማየት ማግኘት የሚችል ሲሆን ከተሳሳተና ከተዛባ መረጃ ከመዳኑም በላይ አርቲስቶቹም ላበረከቱት አስተዋጽኦ እግረ መንገዱን አንድ ብር በማውጣት ክፍያ በመፈፀም ተጠቃሚ የሚያደርግበት አሰራር ነው ተብሏል:: እያንዳንዱ አርቲስት፣ አትሌት፣ ሰዓሊና ማንኛውም ተፅዕኖ ፈጣሪ ወደዚህ ሲስተም ሲገባ ጎልድ ጂ የሚያቀርብለትን 625 ጥያቄ በትክክል መሙላትና መፈረም ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡ እስካሁንም ከ200 በላይ የአገራችን አርቲስቶች በዚህ ስምምነት ውስጥ ገብተው የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ሞልተው ለጎልድ ጂ መመለሳቸውና ስምምነቱን መፈፀማቸውም በመግለጫው ላይ ተብራርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ 8566 Ok ብሎ በመላክና አንድ ብር በመክፈል ተወዳጅ የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ አዝናኝ ቀልዶችና የአጭር መልዕክት አገልግሎት መምረጫ ማግኘት እንደሚችሉም ተገልጿል:: ጎልድ ጂ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በዚህ አሰራር ሲስማማ ኢትዮ ቴሌኮም ከአጠቃላይ ገቢው 40 በመቶ ድርሻ ሲኖረው ቀሪው 60 በመቶ ደግሞ ጎልድጂ እና አርቲስቶቹ እኩል የሚከፋፈሉ ይሆናል ተብሏል፡፡ በዚህ አሰራር እስከ ዛሬ ያለብዙ ጥቅም ሕዝብ ሲያገለግሉ የቆዩ በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎች በሕዝባቸው የሚጠቀሙበት ዕድል መመቻቸቱ ትልቅ ነገር ነው ብለዋል የጎልድ ጂ ሀላፊዎች፡፡ ጎልድ ጂ ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በርካታ ፕላት ፎርሞችን ለመስራት ማቀዱን ገልፆ፣ ለምሳሌ በጤና፣ በመዝናኛ፣ በክፍያ ሥርዓትና በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ከ62 በላይ ፕላት ፎርሞችን እየሰራ ስለመሆኑም ታውቋል፡፡ ይህንን ሥራ ለመስራት የ11 ዓመት ጥናትና የ3 ዓመት ሲስተም ዝርጋታ ጊዜ የወሰደ ሲሆን ይህ እውን እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ባለሀብቱን አቶ ወርቁ አይተነውንና ኢ/ር ምስራቅን ሀላፊዎቹ አመስግነዋል፡፡ በዚህ ሲስተም ብዙ ተከታይ ያለው ፖለቲከኛ፣ በጎ አድራጊ፣ ኢኮኖሚስት፣ ጋዜጠኛና ሌላውም ተሳትፎ ተጠቃሚ መሆን የሚችል ሲሆን ተዓሚኒነትን በተመለከተም አንድ አርቲስት ወይም በዚህ ሲስተም የተመዘገበ ታዋቂ ሰው ስለእርሱ ምን ያህል ሰው በ8622 B መልዕክት እንደላከና ምን ያህል ገንዘብ እንደገባ ‹‹ማያ›› በተሰኘው አፕሊኬሽን ገብቶ መመልከትና መከታተል እንደሚችል የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሐይለ ልዑል ታምሩ፣ የጎልድ ጂ ም/ስራ አስኪያጁ አቶ ፋሲል ሰለሞንና የኤጀንት ሀላፊው አቶ አንድነት አያሌው በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

Read 539 times
More in this category: « የቴክኖሎጂ ጥግ