Saturday, 23 November 2019 11:41

በዩኒቨርሲቲ አመፅ ለመቀስቀስ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ውስጥ አመጽ ለመቀስቀስ ሙከራ አድርገዋል ያላቸውን ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡
ከትናንት በስቲያ በዩኒቨርስቲው ዋና ግቢ ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱ በአግባቡ እንዳይከናወን በማደናቀፍ፣ ተማሪዎችን ለአመፅ ለማነሳሳት ሙከራ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በግቢው ውስጥ ሊነሳ የነበረውን ረብሻ ለማስታገስ መቻላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ከትናንት በስቲያ ማለዳ ላይ፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ናቸው በተባሉ ወጣቶች አነሳሽነት ሊቀሰቀስ የተሞከረውን አመጽና የፀጥታ ችግር ፖሊስ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉን እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በዕለቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጥያቄዎች አሉን›› በማለት ለአመጽ የተንቀሳቀሱትን ቁጥራቸው 200 ገደማ ይሆናሉ የተባሉትን ተማሪዎች ለማነጋገርና ችግሮች ካሉ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሙከራ ማድረጋቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ ለአመጽ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት ተማሪዎች ያቀረቡት ጥያቄ በሌሎች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመማር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ብሔር ተማሪዎች እየሞቱ ባሉበት ሁኔታ እኛ እዚህ ትምህርታችንን መማር ስለማይገባን ድምፃችንን ማሰማት እንፈልጋለንና የሚመለከተው አካል መጥቶ ያነጋግረን የሚል ሲሆን ጥያቄው ከዩኒቨርሲቲው አቅም በላይ መሆኑን በመግለፃቸው ዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ኃይል ወደ ግቢው እንዲገባና የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር እንዲያረጋጋ ጥያቄ አቅርቧል ብለዋል፡፡ በዚሁ ጥያቄ መሰረትም ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የዘለቀው የፀጥታ ኃይል ግቢውን በማረጋጋት በአመጽ ቅስቀሳው ላይ ተሳትፈዋል፣ ተማሪዎች ለአመፁ እንዲነሳሱ ቀስቅሰዋል ያላቸውን ተማሪዎች በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ተማሪዎች መካከል የባለአደራው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ተማሪዎች መሪ ነው የተባለው ወጣት ኦብሳ እንደሚገኝበትም እነዚሁ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  

Read 1304 times