Saturday, 23 November 2019 11:40

የኢህአዴግ ም/ቤት የብልጽግና ፓርቲ መመስረትን አፀደቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

         - በውጭ ሀገራት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ይኖሩታል
                - ፓርቲው “ብልፅግና” የተሰኘ ልሣን ይኖረዋል


           የኢህአዴግ ም/ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የብልጽግና ፓርቲ መመስረትን በሙሉ ድምጽ ያፀደቀ ሲሆን የፓርቲው ፕሮግራም “መደመር” እንዲሆን ወስኗል፡፡
ሐሙስ ባካሄደው ስብሰባው የብልጽግና ፓርቲ ሊከተለው ባቀደው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ዝርዝር ውይይት መካሄዱ ታውቋል፡፡
ስምንት የገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የመሠረቱት ፓርቲ በ37 ገፆች 54 አንቀፆችን የያዘ መተዳደሪያ ደንብም አጽድቋል::
አዲሱን ፓርቲ ለመመስረት ውህደት ለማካሄድ የወሰኑት አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢህዴን እንዲሁም የአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሃረሪና የሱማሌ ገዥ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ ኢህአዴግን የመሰረተው ህወኃት ከውህደቱ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡
በቀጣይ ውህደቱን የሚፈጽሙት ፓርቲዎች በየራሳቸው የውህደት መሸጋገሪያ ጉባዔ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ይህን የመሸጋገሪያ ጉባኤ በአስቸኳይ ለማከናወን ከወሰኑ ፓርቲዎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ተጠቃሽ ሲሆን ከነገ በስቲያ ሰኞ ህዳር 15 ቀን 2012 የመሸጋገሪያ ጉባኤውን እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎችም በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ የመሸጋገሪያ ጉባኤያቸውን ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከፓርቲዎቹ የመሸጋገሪያ ጉባኤ በኋላም አዲሱ ውህድ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ ውህደቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ለውህደቱ ሂደት ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡
የፓርቲ ውህደቱን በተመለከተ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለፁት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ “ውህደቱ የኢትዮጵያን የፌደራል ስርአት ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ተሠሚነት ላልነበራቸው አጋር ድርጅቶች እኩል ድምጽ የሚሰጥ ህብረ ብሔራዊነትን የሚያፀና፣ አካታችነትንና ፍትሃዊ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሁነኛ አቅጣጫ ነው” ብለዋል፡፡ የፓርቲው ውህደት ሀገራዊ አንድነትን ከህብረ ብሔራዊነት ጋር አስተሳስሮ ለመጓዝ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ሊቀ መንበሩ ጠቁመዋል፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ኢሕአዴግ መዋሃዱ ለአገሪቱ ብሔራዊ መግባባትና ሰላም እንዲሁም የተጠናከረ ፌዴራሊዝም ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢሕአዴግን ውህደት ከደገፉት መካከል ኢዜማ እና የአረና መሪዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ውህደቱ የፌደራል ሥርዓቱን ያጠናክራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
45 የህወኃት ተወካዮች ባልተገኙበት በተካሄደው የኢህአዴግ ም/ቤት ስብሰባም የፓርቲው ፕሮግራምና ህገ ደንብ በጥልቀት ተገምግመው በሙሉ ድምፅ መጽደቃቸው ታውቋል፡፡
የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራም የመደመር እሣቤ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን ዝርዝር መተዳደሪያ ደንቡም በህግ ባለሙያዎችና ምሁራን ሰፊ ጥናት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ ላይ ፓርቲው ሊያሳካቸው ያለማቸው ግቦች የተቀመጡ ሲሆን  አዲስ ራዕይና አዲስ ሀገራዊ ትርክትን በመያዝ የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ የሠፈነባት፤ የግለሰብና የቡድን መብቶች በሚዛኑ የሚከበሩባት፣ የበለፀገች፣ ህብረ ብሔራዊ ማንነቷ የዳበረና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን የመገንባት አላማ እንዳለው አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው ለሁሉም የሀገሪቱ ቋንቋዎች ሙሉ እውቅና እንደሚሰጥ ነገር ግን አሁን የፓርቲው የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግርኛና አፋርኛ የተመረጡ ሲሆን ክልሎችና የአካባቢ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የየራሳቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ታሣቢ በማድረግ ቢያንስ አንድ የፓርቲውን የስራ ቋንቋ በተጨማሪነት መጠቀም እንዳለባቸው በህገ ደንቡ ተደንግጓል፡፡
አዲሱ ፓርቲ “ብልጽግና” የተሰኘ የራሱ ልሣን የሚኖረው ሲሆን ልሣኑም በፓርቲው ሁሉም የስራ ቋንቋዎች ይዘጋጃል ይላል፡፡ የቀድሞ የኢህአዴግ ልሣን “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” እንደነበር ይታወሳል፡፡
የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አዲስ አበባ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በየክልሎቹ ዋና ከተማዎች እንዲሁም በዞንና በወረዳ የሚኖሩ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በውጭ ሀገራትም እንደሚኖሩት ደንቡ ይደነግጋል፡፡
ማንኛውም ፍላጐቱ ያለው ግለሰብ የፓርቲው አባል መሆን እንደሚችል የሚደነግገው መተዳደሪያ ደንቡ፤ በህብረ ብሔራዊነትና በሀገራዊ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም ያለውና ዋልታ ረገጥ አመለካከትና ተግባሮችን በጽናት የሚታገል የሚለው ከመስፈርቶቹ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካል ሲሆን ፓርቲው በፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንት እንዲመራ እንዲሁም የፕሬዚዳንቱ ስልጣን በጊዜ ገደብ እንዲገደብ ደንቡ ይደነግጋል፡፡ ዝርዝር መመሪያውም በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ይወጣል፡፡
አዲሱ “ብልጽግና” ፓርቲን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ ጉባኤ አድርጐ በምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግና በቀጣዩ ምርጫ ፓርቲው እንዲወዳደር መታቀዱም ታውቋል፡፡
ከዚህ ውህደት ራስን ያገለለው ህወኃት፤ ከዚህ በኋላ በምን መልኩ እንደሚጓዝ እስካሁን የጠቆመው ነገር የሌለ ሲሆን፤ የኢህአዴግም ሆነ አጋር ድርጅቶች አመራሮችም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡     

Read 2782 times