Saturday, 23 November 2019 11:49

የአማራ እና ኦሮሞ አክቲቪስቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ውይይት አካሄዱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የአማራ እና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በሁለቱ ህዝቦች መቀራረብና አንድነት ዙሪያ ምክክር ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን ረቡዕ ጥቅምት 10 ቀን 2012 የአማራ እና ኦሮሞ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ላይ ያለፉ ታሪኮችን እያነሱ ማህበረሰቡን ባልተገባ ተግባር የማነሳሳት ድርጊት በሁለቱም ወገን ሲፈፀም መቆየቱን አንስተው ከዚህ በኋላ የማይደገምበት ሁኔታ ሊፈጠር እንሚገባ ምክክር ማድረጋቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአዲስ አድማስ አስተረድተዋል፡፡
በውይይታቸው ማጠቃለያ ባወጡት የአቋም መግለጫም ሁለቱን ህዝቦች ሊያጋጭ የሚችሉ ጽሑፎችን በማህበራዊ ሚዲያ ላለማስተላለፍና የህዝቦችን መቀራረብ ለመፍጠር መወሰናቸውም ታውቋል፡፡ በዚሁ የአቋም መግለጫቸው ሠላምና መረጋጋትን በሀገሪቱ መፍጠር የሚቻልባቸውን መንገዶች ለማመላከትና ሀገሪቱን የማረጋጋት ድርሻቸውን ለመወጣትም ቃል ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማውገዝ ህዝብን ለመነጣጠል የሚሠሩ አካላት ለህግ እንዲቃረቡም በአቋም መግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የአማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች የሠላም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህ ኮንፈረንስ ላይም የሃይማኖት መሪዎች አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ተሳትፈዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይም የሁለቱ ህዝቦች አንድነት ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሁሉም የየድርሻቸውን ለመወጣት ቃል መግባታቸውን ተሣታፊዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በሃይማኖቶች መካከል፣ በብሔሮች መካከል በዘላቂነት ህብረትና አንድነት መፈጥር የሚቻልበት ሁኔታ ላይም የተለያዩ ምክር ሃሳቦች ከተሰብሳቢዎች መቅረባቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንዲሁም መንግስት የተማሪዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅና አጥፊዎችን በህግ ያለማወላወል እንዲቃጣ በሠፊው ምክረ ሃሳቦች መቅረባቸውን ተሣታፊዎች አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ የውይይት መድረኮች ቀደም ብሎ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ባለ ሀብቶች የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
እነዚህ የውይይት መድረኮች በቀጣይ እስከ ዞንና ወረዳ እንደሚዘልቁም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

Read 10835 times