Saturday, 23 November 2019 11:48

የምግብ ሰብል እና የቁም እንስሳት ዋጋ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    ክረምቱ ለሰብል እና ለእንስሳት አመቺ እንዳልነበር ተገልጿል

                  በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የታየውን የክረምት (መኸር) እና የበልግ የዝናብ ስርጭትን መነሻ በማድረግ የአለም የምግብ ፕሮግራም ሀገሪቱ ለሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት የሚኖራትን የምግብ ዋስትና ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በአብዛኛው የክረምቱ ሁኔታ ለሰብል ምርት አመቺ እንዳልነበር ገልፆ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት በአገሪቱ የምግብ ሰብልና የቁም እንስሳት ዋጋ በከፍተኛ መጠን ይጨምራል ብሏል ፡፡ ሀገሪቱ ለምግብ ዋስትና የሚሆናትን አብዛሃኛውን የሰብል ምርት የምታገኘው በክረምት (መኸር) ወቅት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ ያለፈው ክረምት የዝናብ ስርጭት ግን የተዛባ መሆኑ ለሚቀጥሉት ዘጠኝ ወራት የምግብ ዋስትናዋን የሚፈታተን ይሆናል ብሏል፡፡
ቀደም ሲል ከራሣቸው አልፎ ለገበያ የሚሆን ሰብል ያመርቱ በነበሩ የሰሜን ምስራቅ አማራ፣ ምስራቅ ትግራይ እና ሰሜን አፋር አካባቢዎች ዝቅተኛ ዝናብ በመዝነቡ ለምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በምስራቅ ሀረርጌ፣ ጉጂ፣ ባሌ አካባቢዎች በክረምቱ ከሚጠበቀው በታች የሆነ ዝናብ መዝነቡን ያስገነዘበው ሪፖርቱ በዚህም መነሻ በቀጣዮቹ ዘጠኝ ወራት ሀገሪቱ ለምግብ እህል እጥረት ትጋለጣለች ብሏል፡፡ አርብቶ አደር አካባቢዎች በሆኑት ሰሜን አፋር፣ የምስራቅ ሐረርጌ፣ ጉጂ፣ ሶማሌ አካባቢዎች የዝናቡ እጥረት መፈጠር በዋናነነት ለቁም ከብቶች ዋጋ መናር ምክንያት እንደሚሆንም ሪፖርቱ አትቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሰብል ዋጋ መጨመር እና ለቁም ከብቶች ዋጋ መወደድ የተጋለጠች ትሆናለች ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
ዋጋቸው በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ተከታታይ ጭማሪ ሊያስመዘግብ ይችላል ተብለው ከተገለፁት የሰብል ምርቶች መካከልም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ገብስ ተጠቃሽ ሆነዋል-በሪፖርቱ፡፡ መንግስት ይሄን ሁኔታ ተረድቶ የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግም የአለም የምግብ ፕሮግራም ከትናንት በስቲየ ባወጣው ሪፖርቱ አሳስቧል፡፡ በዚሁ ሪፖርት ላይ በተለይ ባልተጠበቀ መልኩ በመስከረም እና በጥቅምት የዘነበውን ከመደበኛ በላየ ዝናብ ተከትሎ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ እና ሶማሌ ክልሎች 205ሺህ ሰዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የሰው እጅ ጠባቂ መሆናቸውንና በርካታ የቤት እንስሳት በጐርፍ ማለቃቸውን አስታውቋል፡፡

Read 1959 times