Saturday, 23 November 2019 11:55

የጀነራሉን ጠባቂ ጨምሮ 13 ግለሰቦች ከሰኔ 15 የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ ተመሰረተባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   ‹‹አሳድ›› የሚባል ድብቅ የስለላ ተቋም አቋቁመው ነበር ብሏል

            የጀነራል ሰዓረ መኮንን የግል ጠባቂ የነበረው መሳፍንት ጥጋቡና የአብን የሕዝብ ግንኙነት ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 13 ግለሰቦች ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያየዘ ትናንት ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ክስ የተመሰረተባቸው በዋናነት ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸውን ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ  ክርስቲያን ታደለ፣ አስጣራው ከበደ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አበበ ፋንታ፣ አስቻለው ወርቁ፣ ተሾመ መሰለ፣ አለምነህ ሙሉ፣ ከድር ሰኢድ፣ አየለ አስማረ፣ አማረ ካሴ፣ ፋንታሁን ሞላና በለጠ ካሳ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በእነዚህ ተከሳሾች ላይ አቃቤ ሕግ የመሰረተባቸው ክስም ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኋል ለመናድ በማሰብ ተንቀሳቀሰዋል የሚል ነው፡፡
ተከሳሾቹ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመለወጥ በማሰብ በዋና አድራጊነትና ተካፋይነት በሃይል፣ በአድማና ሕገወጥ በሆነ መንገድ የኢፌዴሪ እንዲሁም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትን ከሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ለዚሁ አላማ  ማስፈጸሚያ እንዲሆን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ ተልዕኮውን የሚፈፅሙበትን ዘዴና ሁኔታ የጸጥታ ክትትል ኦፊሰር ስልጠና በሚል ሽፋን አባላትን በመመልመልና መንግሥትን በስውር ጦርነት ስልት፣ የሥነ ልቦና ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት በማካሄድ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ የሚያስችል አደረጃጀት መፈጠር የሚያስችላቸውን ስልጠና መውሰዳቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡
ስልጠናውን ከመውሰዱ በኋላ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ዞኖችና ከክልሉ ውጭ በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በመመደብ እንዲሁም አባላቱ ተልዕኮውን ተቀብለው በተመደቡበት አካባቢ የታጠቁና አላማውን በመደገፍ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ አካላትን በመመልመል በግልና በቡድን የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሕዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣና ሥርዓቱን እንዲቀይር ሲንቀሳቀስ ነበር ይላል - ክሱ፡፡
በተለይም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተቋማትና አመራሮች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የፌዴራሉ መንግሥት ተቋማት በተለይም የአገር መከላከያ ሰራዊትና አመራሮችን በመግደል ሰራዊቱን መበተንና የሚፈፀመውን ጥቃት መከላከል ስለማይቻል በቀላሉ ስልጣን ለቆጣጠር ይቻላል በሚል ዝግጅት በማድረግ ይህንኑ አላማ በመቀበል ከአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ ተመርቶ በባለሥልጣናቱ ላይ ግድያ መፈፀሙን ያትታል የክስ መዝገቡ፡፡
ተጠርጣሪዎቹም በግድያው የተሳተፉና ጥቃቱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ በፌስቡክና በስልክ የአጭር መልዕክት ሕዝቡ የወንጀል ተግባሩን ደግፎ እንዲቆምና መንግሥትን በሃይል እንዲቀየር ያደራጁትን አካል ጨምሮ በየቦታው እንዲንቀሳቀስና ጥቃቱን እንዲፈጽም በመቀስቀስ ተግባር ላይ የተካፈሉ መሆኑን የክስ መዝገቡ ይዘረዝራል፡፡
2ኛ ተከሳሽ የሆነው መሳፍነት ጥጋቡ ቀኑ ወሩ በውል ባልታወቀ በ2011 ዓ.ም ጽጌ በተባለ ግለሰብ አማካይነት ከብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመገናኘት ጀነራል ሰዓረ መኮንን የአማራን ሕዝብ እያስገደለ ነው፤ ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅሙ አመራሮችን በማስወገድ ክልሉን እንቆጣጠራለን ስለዚህ ጀነራል ሰዓረን መግደል አለብህ፣ እንዲሁም ሌለ ተልዕኮ የሚፈጽም ደፋርና ጠንካራ ሰው መልምለህ ታገናኘኛለህ በሚል የሰጠውን ተልዕኮ ተቀብሎ ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም የአቃቢ ሕግ 1ኛ ምስክር የሆነውን ግለሰብ በማግኘት ከብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ የተሰጠውን ተልዕኮ በማስረዳት እሱ ደግሞ ጀነራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል በማሳመን፣ በግንቦት ወር ወደ ጎንደር በመሄ ከብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመገናኘት ተልዕኮ እንዲቀበል ያደረገ መሆኑ ተመልክቷል - በክሱ፡፡
ቀጥሎም ቀኑ ባልታወቀ ግንቦት ወር አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ከምስክሩ ጋር በመገናኘት ወንጀሉን የሚፅሙበትን ሁኔታ የተነጋገሩ ሲሆን በባህር ዳር ጥቃቱ ሲፈፀም መረጃውን እንዲያሳውቀውና እሱም ጀነራል ሰዓረ መኮንን ላይ እርምጃ ሲወሰድና ሁኔታውን ለማየት ሲሰባሰቡ ጀነራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል በመነጋገርና በቀን 15/10/2011 ከምሽቱ 3 ሰዓት በባህር ዳር ባለሥልጣናቱ ላይ ድርጊቱ ሲፈፀምና ድርጊቱ መፈፀሙ ሲነገረው በሽጉጥ ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራን በመግደል ለማምለጥ ሲሞክር ተከቦ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
በመዝገቡ ከ2ኛ እስከ 9ኛ ያሉ ተከሳሾ (አስጠራው ከበደ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አበበ ፋንታ፣ አስቻለው ወርቁ፣ ተሾመ መለሰ፣ አለምነህ ሙሌ፣ ከድር ሰዒድ እና አየለ አስማረ) ደግሞ ከሕግ ውጭ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከአማራ ክልል መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ውጪ የአማራ የስለላና ደህንነት ድርጅት (አሳድ) የሚል ተቋም በመገንባት ጠላት ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ሀይሎች በተለይም ሕወኃትና ኦዴፓን ለመሰለል እና በአስፈላጊ ወቅትም መንግሥትን በማዳከም የሃይል እርምጃ ለመውሰድ የስለላና የመረጃ ደህንነት ስልጠናና በተግባር ልምምድ ውስደው ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ነበር ይላል - የክስ መዝገቡ፡፡
የእያንዳንዳቸውን ተሳትፎ በተመለከተም በክሱ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በዚህ መዝገብ 12ኛ ተከሳሽ የሆኑት የአብን የሕዝብ ግንኙነት ክርስቲያን ታደለ በሕዝብ ላይ ሁከት በመፍጠር ሕገ መንግሥቱን ለመናድ በማሰብ በሚያዝያ ወር 2011 አ.ም በአማራ ክልል ባህር ዳር፣ ደብረ ታቦር፣ ጎንደር፣ ወልድያ አካባቢ በመንቀሳቀስና ተወካዮችን በማግኘት በአማራ ክልል አመፅና ብጥብጥ መነሳት አለበት፤ ሱዳን ላይ የተፈጠረው አይነት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኢትዮጵያም መካሄድ አለበት፤ ይሄ እንዲሆን መጀመሪያ የክልሉ መዋቅር ማፈረስ አለብን፣ በተሌ የአዴፓ ሃላፊዎችን የደህንነትና ፀጥታ መዋቅሩን ልንመታ ይገባል፤ የገንዘብ እና የትጥቅ ድጋፍ ከውጭም ከውስጥም ማግኘት አለብን፤ ከባለሀብቶና ከውጭ አካላት ጋር ቀጥታ ትስስር በመፍጠር የህቡዕ አደረጃጀቱን በትጥቅ ማጠናከር ይገባል፡፡ ከጸጥታው ትጥቅ እንቀማ፣ ወጣቱን ለአመጽ ማነሳሳትና ማዘጋጀት አለብን፤ ህቡዕ አደረጃጀት በመፍጠር በዩኒቨርሲቲዎች አመፅ እንዲነሳ መስራት አለብን በክልሉ ሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ መንቀሳቀስ የለበትም በሚል ተልዕኮ መስጠታቸው በክሱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በፌስቡክ ገጹ ላይ በ10/10/2011 ዓ.ም ‹‹ጥቁሩን ጥርሰ ፍንጭቱን የሕግ አዋቂውን ቦታውን ቢበቅልም ባይበቅልም ከአፈር መዛመዳቸው ግን እየሆነ መጥቷል አሁን ገብርዬም አሽከሮቹን አንበሴም ልዩ ሃይሉን ያሰናዳ መሳሪያውንም ይወልውል ከአባይ በታች ያላችሁ ሥርዓት ያዙ አይመጥናችሁም የሚል ሟቾች የቀድሞ የክልሉ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድባቸው በመግለጽ ተልዕኮ ሲሰጥ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑም በክሱ ተመልክቷል::
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በቡድን በመደራጀት በሃይል ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ የክልሉን ብሎም የፌደራሉን መንግሥት ስልጣን ለመያዝ በማሰብ አባላትን በመመልመል ለወንጀል አፈጻጸሙ የሚረዳ ስልጠና በመስጠትና በስልጠናው ላይ በመካፈል፣ ወንጀሉ እንዲፈጸም ህዝቡን በመቀስቀስና አደራጅቶ ተልዕኮ በመስጠት በወንጀሉ በቀጥታ በመሳተፍና የተፈፀመው ወንጀል ውጤት እንዲያገኝና ሕዝቡ ደግፎ እንዲቆም በመንቀሳቀስ የተሳተፉና በድርጊቱም አጠቃላይ 17 ሰው ሕይወቱ እንዲያልፍ 20 እንዲጎዳ በማድረጋቸው በፈፀሙት በሕገ መንግሥትና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል መከሰሳቸው ተመልክቷል፡፡    
ተከሳሾች በምርመራ ወቅት የተወሰደባቸው ንብረቶች እንዲመለስላቸው እንዲሁም አሁን ባሉበት ማረፊያ ቤት የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ለፍ/ቤቱ ያመለከቱ ሲሆን ጠበቆችም ደንበኞቻችንን በአግባቡ አግኝተናቸው አናውቅም በዚህም ሙሉ አገልግሎት ልንሰጣቸው አልቻልንም የሚል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱም ለምርመራ ስለተወሰደባቸው ንብረቶች በዝርዝር ለችሎት በጽሑፍ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ከደህንነት ጋር ላነሱት ጥያቄም ወደ ማረሚያ ቤት ወርደው ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግባቸው ፍ/ቤቱ አዟል፡፡
ተከሳሾቹ ለቀረበባቸው ክስ መቃወሚያ ካላቸው ለታህሳስ 1 ቀን 2012 እንዲያቀርቡ በፍ/ቤቱ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳርና አዲስ አበባ በባለሥልጣናት ላይ በተፈፀመ ግድያ የጦር ሃይሎች ጠቅላላ ኢታማዦር ሹም የነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን፣ ሜ/ጀነራል ጋዛኢ አበራ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ አዘዘ ዋሴ መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘም በአጠቃላይ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉ መገለፁ ይታወሳል፡፡

Read 11658 times