Saturday, 23 November 2019 11:56

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ የነዋሪዎች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ አምነስቲ አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ በክልሉ ለሚኖሩ የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆች በመንግስት በኩል  አስፈላጊው ሕጋዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ፡፡
ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ የሕዝበ ውሳኔ ቀንን ለህዳር 2012 ዓ.ም ማሸጋገሩን ተከትሎ በተለያዩ የሲዳማ ዞኖች በተፈጠረው ቀውስ 170 የሚደርሱ ዜጎች መገደላቸውን አምነስቲ አስታውሷል፡፡
ሕዝበ ውሳኔውን ተከትለው በሚመጡ ጉዳዮች በዞኑ የሚኖሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሕይወታቸው፣ በንብረታቸውና በማህበራዊ መስተጋብራቸው ምንም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው መንግሥት ዋስትና ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳሰበው ተቋሙ፤ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ማስከበር ስራዎችን እንዲሰራም ጠይቋል፡፡
የአመነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ም/ዳይሬክተር ሴዳፍ ማጋንጎ እንዳሉት መንግሥት በተቃውሞ ወቅት ያልተመጣጠነ ሃይል እንዳይጠቀም፣ የሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እንዲያረጋግጥና ሰላማዊ ስብሰባዎችን እንዲፈቅድ እንዲሁም ከምንም በላይ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች መብት እንዲያስጠብቅ አሳስቧል፡፡
የሲዳማ ዞን አስተዳደር በበኩሉ የሕዝበ ውሳኔው ሂደት በሰላም መጠናቀቁን አስታውቆ ውጤቱን ተከትሎ የደስታ መግለጫም ሆነ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሃዋሳና በዞኑ ከተሞች አይፈቀድም ብሏል፡፡

Read 11345 times