Saturday, 23 November 2019 12:07

60ዎቹ የደርግ ሰለባ ባለስልጣናት ሲታወሱ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 ንጉሳዊውን ሥርዓት ገርስሶ በመጣል ስልጣኑን የተቆጣጠረው የደርግ ሥርዓት የዘውዳዊውን መንግስት ከፍተኛ የጦርና የሲቪል ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ማዋል ጀመረ፡፡ ደርግ በንጉሳዊው ሥርዓት ውስጥ በተለያዩ የስልጣን ደረጃዎች ላይ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር እያዋለ ማሰር ሲጀምርም ባለሥልጣናቱ ከሕግ አግባብ ውጪ በዜጎች ላይ የፈጠሩአቸው ችግሮች እየታዩና እየተጣሩ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ቃል ገብቶ ነበር፡፡
ከ60ዎቹ የደርግ ሰለባ ባለሥልጣናት መካከል የመጀመሪያውን የሞት ጽዋ የቀመሱት በውጊያ ብቃታቸው የተከበረና ገናና ስም የነበራቸውና ኮዳ ትራሱ በሚል የቅጽል ስም ይታወቁ የነበሩት ጀነራል አማን ሚካኤል አምዶም ነበሩ፡፡ ጀነራል አማን በኮሪያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ላዘመተችው ሰራዊት አዛዥ ሆነው አመራር መስጠታቸውም ይታወሳል፡፡ ህዳር 13/1967 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ጀነራል አማንን በቁጥጥር ስር አውለው ወደ ደርግ ጽ/ቤት ይዘዋቸው እንዲመጡ ለወታደሮች ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ይህንን ትዕዛዝ የተቀበሉት ወታደሮችም ጀነራሉን አስረው  ለማምጣት ቢሄዱም እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም፡፡ ከተጧጧፈ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ጀነራሉ ሞቱ፡፡
በማግስቱ ማለትም ህዳር 14/1967 ዓ.ም ደርግ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው 59 የንጉሱ ስርዓት ባለሥልጣናት ሕይወት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተሰበሰበ፡፡
ደርግ በወቅቱ በቁጥጥር ስር ባዋላቸው ባለሥልጣናት ላይ አቅርቧቸው ከነበረው ክሶች መካከል በአስራ ሰባቱ የንጉሱ ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ ሀይል መጠቀም በሚል ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በወታደራዊ መኮንኖቹ ላይ ደግሞ ስልጣንን መከታ በማድረግ ከሕግ አግባብ ውጪ ስልጣንን መጠቀም፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማነሳሳት ደባ መፈፀምና ታላቁን የኢትዮጵያን የአመጽ እንቅስቃሴ ለማዳፈን መሞከር እንዲሁም የገቡትን ቃል ኪዳን ማጠፍና በወታደሩ መካከል ልዩነት መፍጠር የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ደርግ በእነዚህ ወንጀሎች ክስ መስርቶ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የንጉሳዊ አስተዳደር መንግስት ባለሥልጣናት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ሲሰበሰብም እዛው የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በተሰበሰቡበት አዳራሽ ምድር ቤት ውስጥ እስረኛ ባለሥልጣናቱ ይገኙ ነበር፡፡
የንጉሳዊው ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖቹ ላይ የሞት ቅጣት ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት ውሳኔውን ከደርግ ባለሥልጣናት መካከል ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ በጥብቅ ተቃውመውት እንደነበር ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደርስ “እኛና አብዮቱ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸውታል፡፡ ውሳኔው የአብዛኛውን የደርግ ባለሥልጣናት ይሁንታ አግኝቶ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ማምሻውን ደርግ እንዲህ የሚል መግለጫ አወጣ፡፡
ምክር ቤቱ (ደርግ) የተለያዩ ሸረባዎችን በማድረግ አገሪቱ በደም አበላ እንድትታጠብ ተደጋጋሚ መሰሪ ተግባራትን የፈፀሙትን የቀድሞዎቹን የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣኖች በሞት መቅጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ይህ ውሳኔ ባለፉት ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ ሲሰቃዩ የቆዩትን ምንም አይነት ወንጀል የሌለባቸውን ንፁሀን ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ሲባል የተደረገ ነው። ስለሆነም ምክር ቤቱ (ደርግ) በመጥፎ አሰራራቸው ጥፋተኛ ሆነው በተገኙት ፍትህ እንዲስተጓጎል ደንቃራ ሲሆኑ በቆዩት የአገሪቱን ሰነድ ሚስጢር ለውጪ ወኪሎች በሸጡና በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያን ታላቁን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ በተሰለፉት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት ሰጥቷል፡፡
በወቅቱ ሁኔታው በዜጎች ላይ የፈጠረው ድንጋጤ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህ የደርግ ውሳኔም ህይወታቸውን ካጡት ታላላቅ ባለስልጣት መካከል አክሊሉ ሀብተወልድ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ራስ መስፍን ስለሺ፣ ልዑል አስራተ ካሣ ደጃዝማች ለገሰ ብዙ፣ ደጃዝማች ከበደ አሊ እና አፈንጉስ አበጀ ደባልቅ፣ ይገኙበታል፡፡ ይህ ድርጊት ከተፈፀመ እነሆ ነገ ህዳር 14/2012 አርባ አምስተኛ ዓመቱን ይይዛል እነዚህ የደርግ ሰለባ የቀድሞ የዘውዱ ሥርዓት ታላላቅ ባለሥልጣናት ከተቀበሩበት የጅምላ መቃብር አጽማቸው ተቆፍሮ እንዲወጣና በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡
ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያምን ጽሑፍ በመርጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡      


Read 4098 times