Print this page
Saturday, 23 November 2019 12:10

የዋልያዎቹ ዝነኛ ድል በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     • ዋልያዎቹ 600 ሺ ዩሮ ዝሆኖቹ 185.93 ሚሊዮን ዩሮ
          • አንድ ዋልያ በአማካይ 26ሺ ዩሮ አንድ ዝሆን በአማካይ 8.45 ሚሊዮን ዩሮ
          • 2 ፕሮፌሽናል ዋልያዎች 22 ፕሮፌሽናል ዝሆኖች

             በ2021 እኤአ ላይ ካሜሮን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  በሚካሄደው የምድብ ማጣርያ ዋልያዎቹ ዝሆኖቹን 2ለ1 በማሸነፍ ዝነኛ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄደው የምድብ ማጣርያ ከወር በፊት በመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች የተጀመረ ሲሆን የየምድቡ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ደግሞ ባለፈው ሰሞን ተከናውነዋል:: በኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 11 ከአይቬሪኮስት፤ ከኒጀርና ከማዳጋስካር ጋር መደልደሉ ሲታወቅ ባለፈው እሁድ ባህርዳር ላይ ዋልያዎቹ በሁለተኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ዝሆኖቹን ማሸነፋቸው ለአገሪቱ እግር ኳስ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው፡፡
ባህርዳር ላይ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የዋልያዎቹን የማሸነፊያ ግቦች ያስቆጠሩት ሱራፌል ዳኛቸው እና የቡድኑ አምበል ሽመልስ በቀለ ናቸው፡፡ ዋልያዎቹ ዝሆኖቹን  በሜዳቸው ማሸነፋቸው በአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ ያላቸውን ተፎካካሪነት ከማለምለሙም በላይ ከአፍሪካ ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱን የረቱበት ታሪክ በመሆኑ በመላው የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ዘገባዎች መደነቅን አትርፎላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በውጤቱ ማግስት ለሙሉ ቡድኑ የ800 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት አበረክቷል፡፡ የሽልማት ስነ ስርዓቱ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የተካሄደ ሲሆን የቡድኑ አባላት ከ20 እስከ 30 ሺህ ብር ሽልማት ሲሰጣቸው ወደፊት በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ለማነሳሳት  ነው ተብሏል። ፌደሬሽኑ በታሪካዊው ውጤት ማግስት ለዋልያዎቹ የማበረታቻ ሽልማቱን ማበርከቱ የሚመሰገን ሲሆን በቀጣይ ብሄራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ካበቁ ይህን ያህል ሽልማት ይጠብቃችኋል በሚል ማነሳሻ ከአሰልጣኙ እና ከብሄራዊ ቡድኑ አባላት ለመስራት ማቀድ ያስፈልገዋል::  በቀጣይም ቡድኑ በውጤታማነቱ የሚቀጥል ከሆነ በጨዋታ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር ሽልማት እንደሚያበረክትላቸው ፌደሬሽኑ መግለፁም ከዚሁ አቅጣጫ ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡በሌላ የምድቡ ሁለተኛ ዙር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ማዳጋስካር ከሜዳ ውጭ ኒጀርን 6ለ2 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ግስጋሴን ቀጥላለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የ3ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከኒጀር ጋር የሚገናኘው ከ9 ወራት በኋላ ሲሆን በዚሁ ወቅት  ኮትዲቯር ማደጋስካርን በአቢጃን የምታስተናግድ ይሆናል፡፡ በ4ኛው ጨዋታ በሜዳው ከኒጀር ጋር፤ በ5ኛው ጨዋታ በሜዳው ከማዳጋስካር እንዲሁም በስድስተኛው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ከአይቬሪኮስት ጋር የሚገናኝ ይሆናል:: ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የያዘውን ውጤት ለማስጠበቅ በቀጣይ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት 9 ወራት ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ ለቡድኑ በሚያወጡት የዝግጅት መርሃ ግብር ለመስራት ፌደሬሽኑ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ያለበት ሲሆን፤ በተለይ ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ መስራት ያስፈልገዋል፡፡ ዋልያዎቹ በኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ላይ ያስመዘገቡት አንፀባራቂ ድል በስፖርቱ ላይ የፈጠረው መነቃቃት እንዲቀጥል ነው፡፡ በሚቀጥሉት 9ወራት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቢያንስ 3 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት ቡድኖች ጋር ማድረግ ያለበት ሲሆን ይህን በማሳካት ረገድ በተለይ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ በሚያወጣው መርሃ ግብር መሰረት ለመስራት ከፍተኛ ሃላፊነት ይኖርበታል፡፡  
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኮትዲቯር አቻው ጋር  በአፍሪካ ዋንጫ ዋና ውድድር በማጣርያ እና በሴካፋ ላይ ለአምስተኛ ጊዜ ነው::  ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በ1968 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ውድድር ላይ ሲሆን በመጀመርያው ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋ 1 ለ0 አሸንፋ በመልሱ ደግሞ ኮትዲቯር በተመሳሳይ ውጤት አሸንፋ ነበር፡፡ በ1970 እኤአ ላይ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለ3ኛ ጊዜ ተገናኝተው ኮትዲቯር 6ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፏ ሲታወስ ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በአፍሪካዊ ቡድን በሰፊ የግብ ልዩነት የተሸነፈችበት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡ ባለፈው ሰሞን ሁለቱ ቡድኖች ለአምስተኛ ጊዜ ባህርዳር ላይ በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከመጫወታቸው በፊት ደግሞ ከ9 ዓመታት በፊት በሴካፋ ውድድር ላይ ተገናኝኘተው ነበር::
የዓለም እግር ኳስ የተጨዋቾች የዝውውር ገበያ በመከታተል የሚሰራው ትራንስፈር ማርከት ድረገፅ እንዳሰፈረው 23 ተጨዋቾች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ስብስብ በአማካይ እድሜው 24.3 ዓመት ሆኖ ሲመዘገብ በዝውውር ገበያው የተተተመነው በ600 ሺህ ዩሮ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ከአገር ውጭ ይጫወታሉ ተብለው የተጠቀሱት 2 ተጨዋቾች ሲሆኑ የቡድኑ የዋጋ ተመንም በእነዚህ ተጨዋቾች መውጣቱን በትራንስፈርማርከት ድረገፅ የሰፈረው አሃዛዊ መረጃ ያመለክታል፡፡  በግብፁ ክለብ  ማስር ኤል ማክሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ  በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቡድኑ ውድ ተጨዋች ሆኒ ሲጠቀስ በ400ሺ ዩሮ የዝውውር ገበያ ዋጋው ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስው በ200 ሺ ዩሮ የዝውውር ገበያ  ተመን የተሰጠው ጋቶች ፓኖም ናቸው፡፡
የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን  በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 56ኛ ከአፍሪካ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤  ከኢትዮጵያ ጋር የተጋጠመው ቡድን በ22 ተጨዋቾች የተገነባና በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው ዋጋቸው ሲተመን በ185.93 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ የዝሆኖቹ  22 ተጨዋቾች በሙሉ  ፕሮፌሽናሎች ሲሆኑ በአማካይ እድሜያቸው 27.0  ዓመት ነው፡፡ ከአይቬሪኮስት ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው ውድ ዋጋ ያለው ለአርሰናል ክለብ የሚጫወተውና ትውልዱ በፈረንሳይ የሆነው ኒኮላስ ፔፔ 75 ሚሊዮን ዩሮ በመተመን ነው፡፡ በቀኝ ክንፍ መስመር ላይ የሚጫወተው ኒኮላስ ፔፔ በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛውን የዝውውር ሂሳብ ያስመዘገበ አፍሪካዊ ተጨዋች ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በሚካሄደው ማጣርያ በምድብ 11 መሪነቱን ከ2 የምድብ ጨዋታዎች በኋላ በ6 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ ማዳጋስካር ስትሆን፤ ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ እና ያለምንም ግብ ክፍያ እንዲሁም በተመሳሳይ ነጥብ ያለምንም ግብ ክፍያ ሁለተኛ እና ሶስተኛውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡ ኒጀር ያለንም ነጥብ በአምስት የግብ እዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡
በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታዎች ማዳጋስካር ኢትዮጵያን በራያን ራቬልሰን ጎል 1ለ0 በሆነ ውጤት አንታናናሪቮ ላይ ማሸነፏ ይታወሳል:: ማዳጋስካር በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ከኢትዮጵያ 95 እርከን ከፍ ብላ ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በወቅቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ኒኮላስ ዲፒውት ማዳጋስካር ለመጀመርያ ጊዜ በተካፈለችበት የግብፁ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የነበረው ጥንካሬ በምድብ ማጣርያው መደገሙን መጠራጠራቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ በህንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው የአፍሪካ ደሴት 3 ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነችውን ናይጄርያ እንዲሁም ዲ.ሪ ኮንጎን በማሸነፍ አስደናቂ ውጤት አስመዝግባ በሩብ ፍፃሜው በቱኒዚያ ተሸንፋ ነበር የወደቀችው፡፡
በሌላ የምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ ኮትዲቯር በአቢጃን ኒጀርን አስተናግዳ 1ለ0 ያሸነፈችው በኬጄ  ጎል እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ መመራት ከጀመረ በኋላ በ6ኛው የቻን ማጣርያ ላይ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ በነበረው ተሳትፎ ሳይሳካለት ቀርቶ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡ በ2020 እኤአ የሚካሄዳው የቻን ሻምፒዮና መስተንግዶ ከኢትዮጵያ ሃላፊነት በመሰረተ ልማት አለመሟላት መወሰዱ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ በማጣርያ ወደዚህ ውድድር ሊገባ አለመቻሉ የሚያስቆጭ ነው፡፡ በሌላ በኩል በ2022 እኤአ ላይ ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በአፍሪካ ዞን በሚደረገው ማጣርያ በመጀመርያው ዙር ከሚሳተፉት 28 ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋልያዎቹ በዚሁ ዓለም አቀፍ የማጣርያ ውድድር  በመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ የተመደበው ከደቡብ አፍሪካዋ ሌሶቶ ጋር ነው፡፡ ከሁለቱ ቡድኖች  ጥሎ ማለፍ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ የሚገኙትና በምድብ ማጣርያ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚሰለፉት 26 አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ ይሰለፋል፡፡ አዞዎቹ በሚል ቅፅ ስማቸው የሚታወቀው የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ 144ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ 23 ተጨዋቾች የሚገኙበት ስብስቡ በአማካይ እድሜው 26.4 ዓመት ሆኖ ሲመዘገብ በዝውውር ገበያው የተተመነበት ዋጋ በ 675 ሺ ዩሮ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ መመራት ከጀመረ በኋላ ከአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ በፊት በ6ኛው የቻን ማጣርያ ላይ ከቅድመ ማጣርያው አንስቶ ተሳትፎ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቶ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል፡፡ በ2020 እኤአ የሚካሄዳው የቻን ሻምፒዮና መስተንግዶ ከኢትዮጵያ ሃላፊነት በመሰረተ ልማት አለመሟላት መወሰዱ የሚታወስ ሲሆን ቡድኑ በማጣርያ ወደዚህ ውድድር ሊገባ አለመቻሉ የሚያስቆጭ ነው፡፡
በሌላ በኩል በ2022 እኤአ ላይ ኳታር በምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በአፍሪካ ዞን በሚደረገው ማጣርያ በመጀመርያው ዙር ከሚሳተፉት 28 ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዋልያዎቹ በዚሁ ዓለም አቀፍ የማጣርያ ውድድር  በመጀመርያ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ የተመደበው ከደቡብ አፍሪካዋ ሌሶቶ ጋር ነው፡፡
 ከሁለቱ ቡድኖች  ጥሎ ማለፍ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ ላይ ወደ የሚገኙትና በምድብ ማጣርያ ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚሰለፉት 26 አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ ይሰለፋል፡፡ አዞዎቹ በሚል ቅፅ ስማቸው የሚታወቀው የሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የዓለም የእግር ኳስ 144ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ 23 ተጨዋቾች የሚገኙበት ስብስቡ በአማካይ እድሜው 26.4 ዓመት ሆኖ ሲመዘገብ በዝውውር ገበያው የተተመነበት ዋጋ በ 675 ሺ ዩሮ ነው፡፡


Read 3973 times