Print this page
Monday, 25 November 2019 00:00

በ2019 በዓለም አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ወጣት ኮከቦች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

  በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የ2019 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ላይ በ2019 የዓለም ተስፈኛ አትሌት ዘርፍ ላይ  3 የኢትዮጵያ አትሌቶች ከመጨረሻ እጩዎች ውስጥ ተፎካካሪ ሆነው ገብተዋል፡፡ በሴቶች ምድብ በ2019 ተስፈኛ አትሌት እጩ ሆና የቀረበችው ለምለም ሃይሉ ስትሆን በወንዶች ምድብ ደግሞ  በ2019 ተስፈኛ አትሌት ምርጫ የመጨረሻ እጩ የሆኑት አትሌት ሰለሞን ባረጋ እና አትሌት ለሜቻ ግርማ ናቸው፡፡በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ32ኛ ጊዜ የሚዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች የሽልማት ስነስርዓት  በፈረንሳይ ሞናኮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
አትሌት ለምለም ኃይሉ በ2019 ተስፈኛ አትሌት ምርጫ ከመጨረሻዎቹ 5 እጩዎች አንዷ ለመሆን የበቃችው በውድድር ዘመኑ ከ20 ዓመት በታች የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በ1500 ሜትር ስላስመዘገበች፤ በአፍሪካ ጨዋታዎች በ1500 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በመውሰዷ እና በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማሽ ፍፃሜ በመድረሷ ነው፡፡ ሌሎቹ እጩዎች በ100 ሜትር መሰናክል ከ20 ዓመት በታች አዲስ የዓለም ክብረወሰን በ12.7 ያስመዘገበችው ጃማይካዊቷ ብሪትኒ አንደርሰን፤ በከፍታ ዝላይ 2.04 ሜትር በመዝለል ከ20 ዓመት በታች አዲስ ሪከርድ ያስመዘገበች፣ በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የወሰደችውና በአውሮፓ ከ20 ዓመት በታች  ሻምፒዮን የሆነችው ዩክሬናዊቷ ያሮስላቫ ማሁቺክህ፤ ከ20 ዓመት በታች ምድብ የ20 ኪ ሜ ርምጃ ውድድር የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ያላት፣ በ10 ኪሜትር የርምጃ ውድድር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እና የደቡብ አሜሪካ ሪከርድ የያዘችው የኢኳዶሯ ግሌንዳ ሞርጀን እና በ100 ሜትር እና 200 ሜትር ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሪከርዶችን ያስመዘገበችው አሜሪካዊቷ ሻካሪ ሪቻርድሰን ናቸው፡፡
አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ2019 ተስፈኛ አትሌት ምርጫ ከመጨረሻዎቹ 5 እጩዎች አንዱ የሆነው  በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ በመጎናፀፉ፤ በ5000 ሜትርና በ10ሺ ሜትር ከ20 ዓመታት በታች የዓመቱን ፈጣን ሰዓቶች በመያዙ  እንዲሁም በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ12 ኪሜትር አዋቂዎች ውድድር 5ኛ በመውጣቱ ነው፡፡ አትሌት ለሜቻ ግርማ በበኩ ሌላኛው እጩ ሆኖ የቀረበው በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ ከማግኘቱም በላይ ከ20 ዓመት በታች የዓመቱን ፈጣን ሰዓት የያዘ እና  ያስመዘገበ እና የኢትዮጵያን የ3ሺ ሜትር መሰናክል ሪከርድ ስለጨበጠ ነው፡፡  ሌሎቹ እጩዎች በ400 ሜትር ከ20 ዓመት በታች ክብረወሰንን 7 ጊዜ ያሻሻለው፣ በ400 ሜትር መሰናክል ከ20 ዓመት በታች የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው፣ በፓን አፍሪካን ጌምስ ሻምፒዮን የሆነውና በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 7ኛ ደረጃ ያገኘው የብራዚሉ አሊሰን ዶሳንቶስ፤ በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የአውሮፓ ሻምፒዮን፣ በ1500 ሜትር ከ20 ዓመት በታች የዓለምና የአውሮፓ ሪከርድ የያዘው፣ በ5000 ሜትር ከ20 ዓመት በታች የአውሮፓ ሪከርድ ያለው፣በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር 4ኛ ደረጃ ያገኘና በ5000 ሜትር 5ኛ የወጣው የኖርዌዩ ጃኮብ ኢንግረጊብስተን ፤ እንዲሁም በመዶሻ ውርወራ ከ20 ዓመት በታች የዓመቱን ከፍተኛ ርቀት ያስመዘገበና በዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5ኛ ደረጃ ያገኘው የዩክሬኑ ሚካሄሎ ኮካሃን ናቸው፡፡


Read 8547 times