Saturday, 23 November 2019 12:23

“እትዬ ዘነቡ፤ ኑ ቡና ደርሷል!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መቶ ሺህ! መቶ ሺህ ብር ለሞባይል፣ ያውም ከመንግስት ኪስ! አንደኛውን ትንሽ ጨምረው ከተማ ለከተማ የምታዞር አራት ጎማ ለምን አይገዙላቸውም! እኛም አንደነግጥም ነበራ! ጥያቄ አለን…“የመንግሥት ኪስ ማለት የእናንተ ኪስ ነው…” ምናምን እንባል የለ እንዴ! ኧረ እባካችሁ፣ ቅልጥ ባለች ቺስታ ሀገር ላይ እንዲህ አይነት ቅንጦት አይሉት፣ ክብር መጠበቂያ አይሉት፣ ሞንጎሊያዎች ላይ መሸለያ አይሉት…ግራ ያጋባል፡፡ አሀ….ለአንድ ሞባይል መቶ ሺህ ብር የወጣ ይሄኔ ሌላ፣ ሌላ ስንት አይነት ለ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ የሚበቃ ወጪ እየወጣ እንደሆነ አንድዬ ይይልን እንጂ ሌላ ምን ይባላል!  (እኔ የምለው…ይሄ ነገር ‘የምቀኝነት’ ይመስልብን ይሆን እንዴ?! ለነገሩ እንዲህ አይነት ምቀኝነት አለ እንዴ! የቀበሌ የጤና ቡድን ሆኖ… “አሁን ሊቨርፑል ቡድን ነው!” አይነት ነገር እኮ ‘ምቀኝነት’ አይደለም፡፡ የ‘አፕስቴይርስ’ ዝግመት ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
“ለቤት ኪራይ አስራ ስምንት ሺ ማለት ምን ማለት ነው!” ስትሉ የነበራችሁ ወዳጆቼ፣ ያው እንግዲህ ቁርጣችሁን እወቁ፡፡ በአስር ሺህ ብር ሞባይል “በስሜ ቀን ይሰየምልኝ” ልትሉ ምንም የማይቀራችሁ… ዙሩ እጅግ በጣም ከርሮ ሀንድረድ ደፍኖላችኋል! ይሄንን ለ‘ቫር’ መተው እንጂ እኛማ በቃ ‘ፎጣውን’ ቡጢው መድረክ ላይ ወርውረናል፡፡
የምር ግን እዚህ ሀገር የሚያስደንቁን ነገሮች እያነሱ ሄዱና… አለ አይደል… “‘አንደር ዘ ኢትዮፕያን ስካይስ’ የማይሆን ነገር የለም” የሚል አስተሳሰብ ጠፍሮ ያዘንና ነው እንጂ ለሞባይል ቀፎ ‘ሀንድረድ ታውዘንድ’ ብር የመንግስት ገንዘብ…‘ይዟት፣ ይዟት በረረ፣ ይዟት በረረ!’ ሲሆን በየሚዲያው ላይም ሆነ በየስብሰባው ትንሽዬ ሱናሚ ነገር መቀስቀስ ነበረበት፡፡ የተለያየ አይነት ‘ሱናሚውንም’ ለመድነው መሰለኝ! 
ስሙኝማ...ይሄ የስብሰባ ጉዳይ… እንደ ጥሬ ሥጋ አይነት “አሁን ካላመጣህ!” “አሁን ካላመጣሽ!” የሚል የሚያንቀዠቅዥ ሱስ ነገር አለው እንዴ! የስብሰባው መአት! የታሸገ ውሀው መአት! ደግሞላችሁ እኮ… አለ አይደል…ስብሰባ ላይ የሚደሰኮረው፣ በጥናት ወረቀትና በአቋም መግለጫ ወረቀትና ቀለም የሚጨርሰው፣ መጨረሻም አሪፍዬ እራት (“በውሀ” ብሎ መጨመር ይቻላል!) ‘ቀመስ’ ተደርጎ (ቂ…ቂ…ቂ…) “ይሄ በተግባር ሲውል ሀገሪቱ ቡድን ስምንትን ትቀላቀላለች አይነት የሚፎከረው...አለ አይደል…በሁለተኛው ቀን እኮ ራሱ የአቋም መግለጫ ኦሪጂናሌው ሊጠፋ ይችላል፡፡ ቆይማ…በሥራ ቀን መሰብሰብ የለም፣ ለስብሰባ እሩቅ እየሄዱ ገንዘብ ማባከን የለም… አይነት ነገሮች  ስንባል አልነበር እንዴ! አሁን ለመጠየቅስ ምን አፍ አለን… የመቶ ሺ ብር ሞባይል ጭጭ ምጭጭ አድርጎን!
እግረ መንገድ ጥያቄ አለን…‘ቪ ኤይት’ የሚሏት መኪና አጠቃቀም ላይ የሆነ ጊዜ ገደብ ተጥሎ አልነበር እንዴ! ቦሶቻቸን ‘ቪ ኤይት’ መጠቀም የሚችሉት መቼና በምን አይነት ሁኔታ እንደሆነ ዝርዝር መመሪያዎች ነበሩ አይደል እንዴ! እናማ…እንደሰማነው ከሆነ መመሪያዎች እየተከበሩ አይደለም ተብሏል፡፡ ይሄ እኮ…አለ አይደል… ዜናም መሆን ያልነበረበት ነው:: ልክ ነዋ…ቦሶቹ መመሪያ አናከብርም ካሉ፣ የማስከበሩ ሀላፊነት የተሰጣቸው መመሪያዎቹን ያስከብሩዋ! የምን ‘ጣጣ ፈንጣጣ’ ማብዛት ነው!
እናላችሁ… የሆኑ መመሪያዎች “እየተከበሩ አይደሉም” ሲባል ነገርዬው መመሪያዎችን ማክበር የሚገባቸው ያለማክበራቸው ብቻ ሳይሆን ማስከበር ሲገባቸው ስላላስከበሩትም ነው፡፡ እናማ ማስከበር ነዋ! ወይስ መመሪያ አስከባሪዎቹ አቅማቸው ከመመሪያ ጣሺዎች አቅም አነሰ?
ስሙኝማ…ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ በዘመኑ ቋንቋ ‘ሼር’ መደራረግ የሚሉት ነገር ፌስቡክ፣ ትዊተር ምናምን አያስፈልገውም ነበር፡፡ የእኔ አይነቱን ከወጪ ቀሪ የመሰለ መልክ በፎቶሾፕ የጆርጅ ክሎኒን አስመስሎ ‘መበተን’ (ሼር መደራረግ) ብሎ ነገር የለም፡፡
“እትዬ ዘነቡ፣ ኑ ቡና ደርሷል!” ነበር፣ ያን ጊዜ ‘ሼር’ መደራረግ፡፡ እንደውም እኮ ጥሪ ሁሉ የማያስፈልገበት ጊዜ መአት ነበር፡፡ ጎረቤት ሰተት ብሎ ይመጣል፡፡
“እስካሁን ቡናው አልደረሰም እንዳትይኝ!”
“ኧረ ደርሷል፣ ቁጭ በሉ፡፡”
ዘንድሮ… “ቡና ጠጡ፣” ብሎ ነገር እየጠፋ ነው፡፡ እንደውም መጥራቱ ሌላ ነገር ሊያስከትል ይችላል፡፡
“እትዬ ዘነቡ፣ ኑ ቡና ደርሷል!”
“ቡና ደርሷል! በስንት ጊዜዋ ቡና ጠጪ ብላ የጠራችኝ የሆነ ተንኮል ብታስብ ነው፡፡ እሷን ሴትዮ ሀገሯ ከርማ መጣች ካሉኝ በኋላ እፈራታለሁ፡፡”
“ለምን! ምን ታደርገኛለች ብለሽ ነው የምትፈሪያት?”
“ዘመዶቿ እኮ መጫኛውን እንዲህ እንደ ባህርዛፍ ቀጥ የሚያደርጉ ናቸው!”
 የመጠራጠር ባህላችን የደረሰበት ደረጃ እኮ ከመግዘፉ የተነሳ…የማጋነን መብታችንን እንጠቀምበትና፣.. ቀና ብሎ ለማየት እንኳን አንገት ይቀጫል! (ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ… ስለ ቡና ስናወራ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ከሰማሁት ረዘም ያለ ጊዜ ሆኗል፡፡ በከተማችን ውስጥ አንድ የመኖሪያ ግቢ ውስጥ ነው አሉ፡፡ ከሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሆነ ሰው ተነስቶ ቡና መውቀጥ ከጀመረ … ሁሉም ተነስቶ ይወቅጣል አሉ፡፡ ‘መከላከያ’ ነዋ! “ሌሊት ተነስተሽ ቡና ከወቀጥሽ ምቀኛሽ ሁሉ ድራሹ ይጠፋል፣”  ተብላ ይሆናላ!
ወይ ደግሞ አንዷ በውድቅት ሌሊት ተነስታ ውሀ ከደፋች፣ ሁሉም ተነስቶ ውሀ ይደፋል አሉ:: አስቸጋሪ እኮ ነው!
“አቶ አስጨናቂ፤ እባክህ ዶማህን አንድ ጊዜ  ብታውሰኝ!”
“ለምን ፈልገኸው ነው?”
“ደለሉ ቦዩን ሞላውና ጎርፉ ሰተት ብሎ ሳሎን ገባ፡፡. እስቲ ቆፈር፣ ቆፈር ላድርገው፡፡”
“ሳትጠይቅ ራስህ አንስተህ መውሰድ ትችላለህ እኮ!”
እናም ዶማው ይሰጣል፡፡ ይሰጣል ብቻ ሳይሆን ሰጪው… “እኔ ሌላ የማግዝህ ነገር አለ?” ይለዋል፡፡ ማህበራዊ ኑሮ እንደዛ ነበራ!
ዘንድሮ ግን…መጀመሪያ ነገር አቶ አስጨናቂን ዶማ ለመጠየቅ ማሰቡ ከራስ ጋር ምክክርና የሙሉ ድምጽ ውሳኔ ያስፈልገዋል:: እንደ በፊቱ…“ ሳትጠይቅ አንስተህ መውሰድ ትችላለህ፣” ብሎ ነገር የለማ! ግን ደግሞ ዶማው ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
“አቶ አስጨናቂ፤ ዶማ ብታውሰኝ…”
“የታለኝ ብለህ፣ ሰበሩትና ጣልኩት እኮ፡፡” በቃ!
ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ…ከሰውየው ጀርባ እኮ ዶማው የቤቱን ግድግዳ ደገፍ ብሎ ይታያል፡፡ ደግሞላችሁ… አለ አይደል… ነገርየው ትብብር ተጠይቆና “ሰበሩትና፣ ጣልኩት…” ተብሎ ‘ዘ ኤንድ!’ አይባልም፡፡ ባለ ዶማው ሆዬ፣ ትናንት ዶማም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች ሲዋዋሱ እንዳልነበረ፣ ባለቤቶቻቸው ሹሮና በርበሬ ሲበዳደሩ እንዳልነበረ ሁሉ… ‘ጠርጥሮላችሁ’ ቁጭ!
“ይሄ ሰውዬ…” (ስሙን መጥራት እንኳን አይፈልግም፣) “…ካልጠፋ እቃ ዶማ የጠየቀኝ ምን  ለማለት ፈልጎ ነው?” (መቼም የተደፈነ ቦይ ለመቆፈሪያ የጭራሮ መጥረጊያ አይጠይቀው!) “ይኸኔ እኮ፣ አሽሙር መናገሩ ይሆናል፡፡ በእሱ ቤት እኮ እኔን በቅኔ ‹ዶማ ነህ› ማለቱ ነው!” ሊል ይችላል፡፡ እንደ ዘንድሮ የነገሮች አተረጓጎማችን… እንደዛ ማለቱ አያጠራጥርም!
እናላችሁ… ይሄ ምናልባትም ከከብት ቢያጥቡት፣ ቢያጥቡት የማይጠራ የውስጥ አካል ጋር ሊመሳሰል ምንም ያልቀረው ‘ቦተሊካችን’… ሀሳባችንን ሁሉ አስገድዶ ወሰደውና ነው እንጂ…የሄዱብንን የማህበራዊ ኑሮ እሴቶች መመለስ ቢያቅተን እንኳን … አሁን በሲባጎ ጫፍ የተንጠለጠሉትን ስለ ማዳን በመከርን ነበር!
ከመንገድ ላይ የጀበና ቡና ባለፈ…በየቀኑና በየሳምንቱ … ቢያቅተን በወር አንዴ፤ ከግቢ አጥር ወዲህና ወዲያ፣ ከኮንዶሚኒየም ግራና ቀኝ … እየተጠራራን “እትዬ ዘነቡ፣ ኑ ቡና ደርሷል!” የምንባባልበትን ዘመን ቅርብ ያድርግልንማ! ሀሳብ አለን…ወሳጆቹና ‘ነጣቂዎች’ ማንኛችሁም ሁኑ ማንኛችሁ…አለ አይደል…ማህበራዊ ኑሯችንን መልሱልን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1785 times