Saturday, 23 November 2019 12:25

የኢሕአዴግን ውህደት የምንዳኝበት ሚዛን፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

      የኢህአዴግ ነገር! ለ20 ዓመት ያጓተተውን የፓርቲ ውህደት፣ በ1 ዓመት ለማጠናቀቅ ይጣደፋል፡፡
በጐው ነገር! ቃል የገባቸውን መልካም ሃሳቦች፣ ለመተግበርና ለማሟላት እየጣረ ነው፡፡
በኢኮኖሚ በኩል፣ የመንግስትን የቢዝነስ ፕሮጀክቶች ወደ ግል ለማዛወርና ብክነትን ለመግታት፣ የግል ኢንቨስትመንት መሰናክሎችን ለማቃለል፣ የማሻሻያ እቅዶችን እየተገበረ ነው፡፡
የኢህአዴግ ውህደት ደግሞ፣ ሌላው የፖለቲካ ለውጥ ነው፡፡ ግን ጥሩ ለውጥ ነው ወይ?
ዘረኝነትን ከሚያባብስ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ቅኝት›› የሚያላቅቅ ባይሆንም፣ የኢህአዴግ ውህደት፣ በትክክለኛ ሃሳብ በጥንቁቅ ተግባር ከተከናወነ፣ ከጥፋት የሚያድን ጥሩ ጅምር ሊሆን ይችላል፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ለአገራችን፣ ቁጥር 1 የህልውና አደጋ ነውና፡፡
ለ50 ዓመታት ሲስፋፋና ሲንሰራፋ የቆየውን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ከአገራችን ችግሮች ሁሉ እጅጉን ስር የሰደደ ቁጥር አጥፊ ስህተት ስለሆነ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ማረም እና ማስወገድ አይቻልም፡፡
ነገር ግን ይህን ስህተት ከወዲሁ ለማስተካከል፡፡ ወደ ትክክለኛው የስልጣኔ ፖለቲካ ለመጓዝ፣ ከእለት ወደ እለትም በግስጋሴ ለመሻሻል ካልተጋን፣ የማያዳግም ክፉ ጥፋት ይሆናል፡፡
የኢህአዴግ ነገር! ኢህአዴግ 5 እና 10 ዓመት እየቆየ፣ በራሱ ላይ “አብዮት” ያካሂዳል፡፡ አንዳንዶቹ መልካምና ውጤታማ ለውጦች ናቸው፤ ገሚሶቹ ደግሞ የብልሽት ወይም የኪሳራ፡፡
ራሱን ‹‹የብልፅግና ፓርቲ›› ብሎ መሰየሙ፣ ለኢህአዴግ አስገራሚ ‹‹አብዮት›› ነው:: ‹‹ሕዝብ››፣ ‹‹ሕዝቦች››፣ ‹‹ዴሞክራሲ››፣ የሚሉ የተለመዱ ቃላትን ትቶ፣ ‹‹አብዮታዊ›› ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ልማታዊ›› ከማለት ይልቅ ‹‹የብልፅግና ፓርቲ›› ተብሎ መጠራትን መምረጥ፣ ተራ የቃላት ለውጥ ሊመስል ይችላል፡፡ ግን፣ በተለይ ኢሕአዴግን ለመሰለ ኮምጨጭ ላለ ፓርቲ፣ ከጠቅላላ የፓርቲው ለውጥ ጋር ተዳምሮ ሲታይ፣ የስያሜ ምርጫው እንደ ‹‹አብዮት›› የሚቆጠር ለውጥ ነው:: ‹‹ለውጥ›› ብቻ ሳይሆን ተስፋ ሰጪ መልካም ለውጥ ነው - ጥሩ የመሻሻል ጅምር፡፡
በእርግጥ፣ ‹‹አብዮት›› ሲባል፣ ለዘብ ባለ ትርጉሙ፣ ‹‹ከፍተኛ ለውጥ›› ለማለት እንጂ፣ ከታች ወደ ላይ ተከርብቶ ተገለበጠ፤ ከግራ ወደ ቀኝ ተሽከርክሮ መልኩ ተለወጠ፤ ሁለመናው ተቀየረ ማለት አይደለም፡፡ ለምን? አሁንም እንደቀድሞ፣ ‹‹ሕዝባዊ፣ ልማታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ነኝ›› ማለቱ አልቀረም፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ አሁን በሚያካሂደው ለውጥ …
አንደኛ… ለግለሰብ ህልውናና ክብር፣ ለግለሰብ  ነፃነትና መብት  ምን ያህል ተጨማሪ ትኩረት ይሰጣል?
ሁለተኛ፣ ለግለሰብ ጥረትና ንብረት፣ ለግል ኢንቨስትመንት እና ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ምን ያህል ተጨማሪ ዋጋ ይሰጣል?
ሦስተኛ፣ ለግል ማንነትና ለግል ሃላፊነት፣ ለሕግ የበላይነትና ለዳኝነት ፍትህ ምን ያህል ተጨማሪ ክብር ይኖረዋል?
የኢሕአዴግን ውህደት የምንዳኝባቸው ሚዛኖች እነዚህ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የለውጡ መልካምነትና መጠን የዚያኑ ያህል ይሆናል፡፡
ሚዛኖቹን ለማገናዘብ፣ እንደ መነሻ በቅድሚያ የመጀመሪያውን ‹‹አብዮት››፣ እንመልከት፡፡
  ያልተጠበቀ ‹‹አብዮት›› ነው ማለት ይቻላል፡፡ አክራሪ ኮሙኒስት የነበሩ የኢህአዴግ ድርጅቶች፤ በ82 ዓ.ም “ገበያ ቀመስ ኢኮኖሚ” እና “ብዙ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍ ፖለቲካ” የሚል የተሻለ አቋም ይይዛሉ ብሎ ማን ጠበቀ?
በእርግጥ ይሄ ለውጥ፣ እንደ “አብዮት” የሚቆጠር መልካም የአቋም ለውጥ ቢሆንም፣ “ጊዜያዊ” ለውጥ እንደሆነ ተነግሮ ነበር - በበርካታ የኢሕአዴግ መሪዎች፡፡
ከ5 ዓመት በኋላ ግን፣ በቋሚነት በ“ህገመንግስት” ውስጥ ገብቶ በ87 ዓ.ም ፀድቋል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ከኮሙኒዝም ይሻላል፡፡
ነገር ግን፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ፣ ከግል ኢንቨስትመንት ይልቅ የመንግስት ድርሻ እንዲገዝፍ፤ ሰፊ እድል የሚሰጥ ነው - ህገመንግስቱ፡፡ ‹‹ሶሻሊዝም ዘመም ሕገ መንግስት›› ነው ማለት ይቻላል፡፡
እንዲያም ሆኖ፤ የመስራት ነፃነትና የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበራሉ ይላል - ሕገ መንግስቱ፡፡  
በሌላ አነጋገር፣ የሶሻሊዝምና የካፒታሊዝም አዝማሚያዎችን ያደባለቀ፣ ገበያ ቀመስ ‹‹የቅይጥ ኢኮኖሚ ቅኝት›› የሚያመዝንበት ሕገ መንግስት ነው፡፡
ሁለተኛ ነገር፣ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ መብት፣ የህዝብ መብት፣ የቡድን መብት፣ የብዙሃን መብት›› እና ተመሳሳይ የኋላቀር ፖለቲካ አንቀፆች የጐሉበት ህገመንግስት እንደመሆኑ፤ ስልጡን ፖለቲካን የሚቃረን የ “Collectivism” ቅኝት የገነነበት ሰነድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቢሆንም ግን፣ ለግል ማንነትና ለግል ኃላፊነት ቦታ በመስጠት፣ የግለሰብ መብቶችም እንደሚከበሩ በመዘርዘር፣ የስልጡን ፖለቲካ መሰረታዊ ፍሬ ሃሳብን የ‹‹Individualism›› ቅኝትን) አካትቷል - ህገመንግስቱ፡፡
በሌላ አነጋገር፣ ኋላቀርና ስልጡን ፍሬ ሃሳቦችን ያደበላለቀ ቅይጥ የፖለቲካ ቅኝት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሦስተኛ ነገር፣ ‹‹ቅይጥ የስርዓት ቅኝት›› ነው - ሕገ መንስቱ (የሕግ የበላይነትንና ስርዓት አልበኛ ዴሞክራሲን ያደበላልቃልና፡፡)
20ኛው ክፍለዘመን፣ የሶሻሊዝምና የናሽናሊዝም፣ የኮሙኒዝምና የትይባሊዝም አቀንቃኞች የገነኑበት ዘመን እንደመሆኑ ፣ የአገራችን አንጋፋ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎችም፣ “የህዝብ ሉዓላዊነት፣ ህዝባዊ መንግስት፣ ያልተገደበ ዲሞክራሲ” የሚሉ በርካታ መፈክሮች ነበሯቸው፡፡ “በህግ ያልገደበ ስልጣን” ያስፈልጋል ማለታቸው ነው፡፡
ኢህአዴግም እንደ ሌሎቹ የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎች፣ “ያልተገደበ ዲሞክራሲ፣ ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲ…” ይል ነበር፡፡
በሕዝበ ውሳኔ አማካኝነት “የመገንጠል” መብት… ተብሎ በህገመንግስት የሰፈረውን አንቀጽ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ትዳርና የንግድ ሽርክና እንኳ እንዲህ በዘፈቀደ አይፈርስም:: ባልተገደበ የስርዓት አልበኝነት ዴሞክራሲ ግን፣ አገር በቀላሉ ይበተናል፡፡
ህዝቡ በድምጽ ብልጫ የሚያፀድቀው የልማት ተግባር ሲኖር፣ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ስራ የመፈፀም ግዴታ እንዳለባቸው የሚያመላክት አንቀጽም አለ፡፡ ሕዝቡ ከወሰነ፣ ባርነትም ይፈቀዳል እንደማለት ነው፡፡
መንግስት በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ በጀት መመደብ አለበት  የሚል አንቀጽስ፣ ትርጉሙ ምንድነው? መንግስት በዜጐች ላይ ያሻውን ያህል ታክስ የመጫን ያልተገደበ ስልጣን አለው ማለት ነው፡፡
“ያልተገደበ ዲሞክራሲና ያልተገደበ ስልጣን” በሚል አስተሳሰብ የተቃኙ ለአምባገነንት የሚያመቹ እንደነዚህ አንቀፆች የመኖራቸው ያህል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ህዝብ”፣ “መንግስት” “ፓርቲ”፣ “ባለስልጣን” …ሁሉም ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያስገድዱ አንቀፆችንም ያካትታል ህገመንግስቱ፡፡  
አምባገነንነትን አልያም ስርአት አልበኝነትን የሚያበረታታ ‹‹ያልተገደበ ዴሞክራሲና ያልተገደበ ሥልጣን›› የሚል ኋላቀር ቅኝት አለ በአንድ በኩል፡፡ በሌላ በኩልስ? የሕግ የበላይነትን የሚያስቀድም ስልጡን ስርአትን፣ ለሕግ ተገዢ የሆነ መንግስትን፣ የሕግ አከባበርን የሚቆጣጠሩና የሚከታተሉ የተወሰኑ ሰዎችን በ5 ዓመት አንዴ ብቻ በምርጫ ‹‹የሚቀጠሩበት››፣ በሕግ የተገደበና በሕግ ስር የሚካሄድ የዴሞክራሲ አሰራርንም በሕገ መንግስት ተደንግጓል፡፡
በሌላ አነጋገር፣ ሕገ መንግስቱ፣ ቅይጥ የስርአት ቅኝትን የያዘ ነው - ለሕግ የበላይነት የተገዛ ውስን ዴሞክራሲ (ስልጡን ፖለቲካ) ከአንድ በኩል፣ ሕግና ስርአት የማይገዛው የዘፈቀደ ዴሞክራሲ (ኋላ ቀር ፖለቲካ) በሌላ በኩል የተቀላቀለበት ቅይጥ ስርአት ነው፡፡
በአጭሩ፣ ቅይጥ ፖለቲካ፣ ቅይጥ ኢኮኖሚና ቅይጥ ስርአት፣ በ1982 እና በ1987 ዓ.ም፣ በ5 ዓመት ልዩነት፣ በተከናወኑ የኢሕአዴግ ለውጦች አማካኝነት የመጡ ክስተቶች ናቸው::
ከ5 ዓመት በኋላ፣ በ1992 ዓ.ም የተጠነሰሰው ‹‹ተሃድሶ›› የተሰኘው ለውጥ ደግሞ፣ የቅይጡን ቅኝት አዝማሚያ ወደተሻለ አቅጣጫ እንዲያዘነብል አግዟል - (የግለሰብ መብት፣ ነፃ ገበያ እና የሕግ የበላይነት›› መሰረታዊ የስልጡን ስርአት ምሰሶች እንደሆኑ የሚተነትን አስተሳሰብ ቦታ ያገኘበት ጊዜ ነውና)፡፡
ከ5 ዓመት በኋላ፣ በ1997 ዓዓም፣ ፀዳ ያለ ምርጫ ለማካሄድ የተደረገው ሙከራም፣ እንደ ጥሩ የለውጥ ጥረት ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚሁ ያልተሳካ ሙከራ ማግስት ግን፣ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል - የኋሊት የሚመልሱ የፖለቲካ አፈናዎችን አባብሷል፡፡
ከ5 ዓመት በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም፣ ‹‹መተካካት›› በሚል ስያሜ ከተጀመረው የመሪዎች ለውጥ ጋር፣ ኢሕአዴግ በአንድ በኩል ትንሽ ዘና ለማለት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹በኢኮኖሚ ተሳካልኝ›› ብሎ፣ አናቱ የዞረበት ጊዜ ነው - በብዙ የቢዝነስ ፕሮጀክቶች ብዙ ብክነቶችን አስከትሏል፡፡
ከ5 ዓመት በኋላስ 2007 ዓ.ም፣ ኢሕአዴግ እና አገሪቱ መናወጥ የጀመሩበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ወዲህ ብዙ ለውጦችን አይተናል፡፡
አሁን ከ5 ዓመት በኋላ፣ በ2012 ዓ.ም ደግሞ፣ የኢሕአዴግ ውህደት መጣ፡፡


Read 11152 times