Print this page
Tuesday, 26 November 2019 00:00

የ2020 የግራሚ ሽልማት ዕጩዎች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

                 - ሊዞ በ8 ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛለች
                  - ሚሼል ኦባማ ለሽልማት ታጭተዋል

           በአለማችን ታላቁ የሙዚቃ ሽልማት እንደሆነ የሚነገርለት የግራሚ ሽልማት የ2020 ዕጩዎች ዝርዝር፣ ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገ ሲሆን በስምንት ዘርፎች ዕጩ ሆና የቀረበችው ዝነኛዋ ድምጻዊት ሊዞ፣ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
“ኮዝ አ ላቭ ዩ” በተሰኘው ተወዳጅ አልበሟ የአመቱ ምርጥ አልበምና የአመቱ ምርጥ ሙዚቃ ዘርፎችን ጨምሮ በድምሩ በስምንት ዘርፎች ከታጨችው የ31 አመቷ አሜሪካዊት ድምጻዊት ሊዞ በመቀጠል በብዛት የታጩት ሊል ናስ ኤክስ እና ቢሊ ኢሊሽ ሲሆኑ ሁለቱም በስድስት ዘርፎች ለሽልማት ታጭተዋል፡፡
በአምስት ዘርፎች ለሽልማት የታጨችው ሌላኛዋ ዝነኛ ድምጻዊት አርያና ግራንዴ፣ በብዛት በመታጨት የሶስተኛ ደረጃን በያዘችበት የዘንድሮው የግራሚ ሽልማት፤ በአብዛኛው አዳዲስና ሴት ድምጻውያን በዕጩነት የቀረቡበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለዘንድሮው የግራሚ ሽልማት በቀዳሚዎቹ አራት ዘርፎች በሙሉ የታጨችው የ17 አመቷ ድምጻዊት ቢሊ ኢሊሽ፤ በለጋ ዕድሜዋ ለግራሚ ሽልማት በመታጨት አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧ ታውቋል፡፡
የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በቅርቡ ለንባብ ባበቁት “ቢካሚንግ” የተሰኘ የግለ-ታሪክ መጽሐፋቸው የድምጽ ቅጂ “ዘ ቤስት ስፖክን ዎርድ አልበም” በሚለው ዘርፍ ለግራሚ መታጨታቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ባለቤታቸው ባራክ ኦባማም በዚሁ ዘርፍ ለሁለት ጊዜ የግራሚ አሸናፊ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡
ለ62ኛው የግራሚ ሽልማት በ84 የተለያዩ ዘርፎች በድምሩ ከ22 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች ቀርበው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በተከታታይ ዙሮች በተደረጉ ማጣሪያዎች የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች መመረጣቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
 በመጪው ጥር ወር መጨረሻ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ስቴፕልስ ሴንተር የሚከናወነውና በሲቢኤስ ቴሌቪዥን በቀጥታ የሚተላለፈውን የ2020 ግራሚ ሽልማት በመድረክ አጋፋሪነት የምትመራው ታዋቂዋ ድምጻዊት አሊሻ ኪስ እንደምትሆንም ተነግሯል፡፡

Read 7766 times
Administrator

Latest from Administrator