Saturday, 23 November 2019 12:57

የጃዋር 350 መቀመጫ ህልም ነው?

Written by  ኩርኩራ ዋፎ ከለገጣፎ
Rate this item
(1 Vote)

 በዚች መጣጥፍ ትኩረት የማደርግበት ጉዳይ አቶ ጃዋር ሙሐመድ በመጪው ምርጫ “350 መቀመጫ አሸንፋለሁ” ያለውን በሚመለከት ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህ ሃሳብ “ህልም” ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ይህንን የምልበትን ምክንያት ዘርዘር አድርጌ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ለወራት ያህል መንግስትንም፣ ህዝብንም፣ ቄሮዎችንም፣ በዋናነት ኦሮሚያንና ራሱንም ጭምር ሲበጠብጥና ሲያምስ የነበረው አቶ ጃዋር ሙሐመድ፤ ወደ ባህር ማዶ ተሻግሯል፡፡ እዚያም ሁለት ዓይነት አቀባበል ተደርጎለታል ሲባል እየሰማን ነው፡፡ ደጋፊዎቹ “የጀግና” አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ተቃዋሚዎቹ ደግሞ “ወንጀለኛ ነው፣ ለፍርድ ይቅረብ” የሚል መፈክር እያስተጋቡ ነው የተቀበሉት፡፡ በበኩሌ ደጋፊዎቹም ሆኑ ተቃዋሚዎቹ በእልህ ግብግብ ውስጥ የገቡ ይመስለኛል፡፡ መቻቻልን በተገነዘበና በሰለጠነ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ ስሜታቸውን ሊቆጣጠሩ ባለመቻላቸው አልፎ አልፎ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ሲደርጉና ማዶ ለማዶ ሆነው ሲወራረፉ  አይተናል፣ ሰምተናል:: ይህ የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡ ይህንን በዚሁ ላቁምና በጃዋር ላይ ላተኩር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ይዘው ጃዋር ወደ ሀገር ቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከየዋሁ ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ከመንግስት ካዝና ጭምር ብዙ ገንዘብ መሰብሰቡን ከተባራሪ ወሬ ሰምተናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያውም ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ እናም ጃዋር በመጪው ምርጫ የሰዎችን ድምፅ በገንዘብ መግዛት ይችል ይሆናል፡፡ የድምፅ ሰጪዎችን ልብ፣ የሰዎችን ነጻ ፍላጎት፣ ስሜትና አመኔታ ግን መግዛት ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያት አለኝ!
በፖለቲካ ሣይንስ “ማህበራዊ መሰረት” የሚባል ጽንሰ-ሃሳብ አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት (Social Base) አላቸው፡፡ ለመሆኑ “ማህበራዊ መሰረት” ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ፓርቲ የሚቋቋምበት መሰረታዊ ዓላማ ይኖረዋል፡፡ ይህም ዓላማ የሚመነጨው “መብትና ጥቅምህን አስጠብቅልሃለሁ” ከሚለው ማኅበረሰብ ፍላጎት ነው፡፡ በዚያ ዓላማውም መሰረት “መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ” ለሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወገንተኛ ይሆናል ማለት ነው:: ይህም በመሆኑ አንድ ፓርቲ በአንድ ሀገር ላሉ ዜጎች ሁሉ በእኩልና በተመሳሳይ ደረጃ መብትና ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅ አይችልም፡፡ “ፓርቲ” የሚለው ስያሜም የሚያመለክተው ለተወሰኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ጥብቅናና ውግንና ያለው መሆኑን ነው፡፡ ለምሣሌ፡- የወዛደሩ (የሠራተኛው) ፓርቲ በዋናነት ለሠራተኛው (ለወዛደሩ) መብትና ጥቅም የቆመ ነው፡፡ የቡርዧው ፓርቲ የታላላቅ ከበርቴዎችን ጥቅም አስጠባቂ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ “ውግንናችን ለአርሶ አደሩ ነው፡፡ ማህበራዊ መሰረታችንም አርሶ አደሩ ነው” ይላሉ፡፡
የአንድ ፓርቲ ማህበራዊ መሰረትም በዋናነት “በማወጣቸው ፖሊሲዎች መብትና ጥቅማችሁን አስጠብቅላችኋለሁ” የሚላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህም የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚያ ፓርቲ አባል በመሆን፣ የገንዘብ መዋጮና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በማስተባበር፣ በምርጫ ወቅት ቅስቀሳ በማድረግ፣ ወዘተ. አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ:: ፓርቲው በገባው ቃል መሰረት መፈጸሙንም ይከታተላሉ፡፡
አንድ ፓርቲ ለምርጫ ውድድር የሚቀርበው በዋናነት አባላቱን፣ ደጋፊዎቹንና “መብትና ጥቅሙን አስጠብቅለታለሁ፣ እርሱም ድምፁን ይሰጠኛል” የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል በመተማመን ነው፡፡ በመሆኑም፤ማህበራዊመሰረቱንለይቶ፣ያንን የተለየ የማህበረሰብ ክፍል በማሳመን ወደ ምርጫ ካልተገባ በምርጫ ተወዳዳሪ እንጂ አሸናፊ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ አኳያ ጃዋር “ድምፁን ይሰጠኛል” ብሎ የሚያስበው ማህበራዊ መሰረቱ የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው?
እስከ አሁን የምናውቀው ጃዋር ግለሰብ መሆኑን ነው፡፡ ፓርቲ የለውም፡፡ ፓርቲ ቢኖረው ኖሮ… ዓላማውን አይተን ማህበራዊ መሰረቱን መናገር ይቻል ነበር፡፡ ያም ሆኖ ጀዋር በየመድረኩ ከሚያደርገው ንግግር አኳያ ስናየው “የጃዋር ማህበራዊ መሰረት የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው” ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ “ለሙስሊሞችም እቆረቆራለሁ ስለሚል ሙስሊሞችን እንደ ማህበራዊ መሰረት ሊያይ ይችላል - ጃዋር፡፡ ይህንን በልባችን ይዘን፣ የ350 መቀመጫውን ጉዳይ እንይ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ያለው አጠቃላይ የፓርላማ መቀመጫ ብዛት 178 ነው፡፡ ጃዋር 178ቱንም መቀመጫዎች ያሸንፋል ብለን ብንወስድ (350 – 178 = 172) ታዲያ ጃዋር 172 መቀመጫ ከየትኛው ክልል ለማግኘት አስቦ ነው… 350 መቀመጫ አሸንፋለሁ የሚለው? ማህበራዊ መሰረቱ ካልሆነ ክልል? ይሄ በጣም አስቸጋሪ ነው:: ጃዋር ከአማራ ክልል አንዲት መቀመጫ ቀርቶ አንዲት ድምፅ ማግኘት የሚችል አይመስለኝም:: ምክንያቱም “አከርካሪውን ሰበርነው” እየተባለ የሚፎከርበት አማራ፣ አያቶቹ “ጡት ቆረጡ” እየተባለ የሚወነጀለው አማራ፣ “ነፍጠኛ” የሚል ቅጽል ስም የተለጠፈለት አማራ… ጃዋርን ይመርጣል ማለት ዘበት ነው፡፡
ጃዋር 172ቱን መቀመጫ በብዛት ሙስሊሞች ካሉባቸው ከቤንሻንጉል፣ ከሐረሪ፣ ከሶማሌና ከአፋር ክልል ለማግኘት አስቦ ይሆናል፡፡ ግን ይህም አያስኬድም፡፡ ምክንያቱም፡- አንደኛ፤ አራቱ ክልሎች (ሙሉ ለሙሉ ደገፉት ቢባል እንኳ) ያላቸው የመቀመጫ ብዛት 40 ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ እነዚህ ክልሎች ከጃዋር ይልቅ መብትና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው “የራሳቸው ሰው” አላቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ሙስጠፌ ሙሐመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ትልቅ ምኞት ያላቸው ሶማሌዎች ጃዋርን ሊመርጡ አይችሉም:: ሐረሪዎች ሙሉ ለሙሉ ቢመርጡት እንኳ የመቀመጫቸው ብዛት አንድ ብቻ በመሆኑ ትርጉም የለውም:: ከአፋሮችና ቤንሻንጉሎች ጋር ጃዋር የጠበቀ ግንኙነት አለው ለማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም የጃዋር በ350 መቀመጫ መጪውን ምርጫ የማሸነፍ ምኞት “ህልም” ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡
ሌላው መታየት የሚገባው ጉዳይ፤ “ቀድሞ ነገር ጃዋር ራሱ በምርጫ ለመወዳደር የሚችልበት ህጋዊ መሰረት አለ ወይ?” የሚል ነው፡፡ በሀገሪቱ የምርጫ ህግ መሰረት አንድ ሰው በምርጫ እጩ ሆኖ ለመቅረብ በሚወዳደርበት ወረዳ ቢያንስ 2 ዓመት መኖር ግዴታ ነው:: ጃዋር ይህንን መስፈርት ስለማያሟላ ከእነአካቴው እጩ ሆኖ መቅረብ እንኳ የሚችል አይመስለኝም - የተለየ ህጋዊ ውሳኔ ካልተሰጠ በስተቀር! ጃዋር በእጩነት መቅረብ ባይችል እንኳ እርሱ ለሚደግፈው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ኢትዮጵያዊ መሆን ግዴታ ነው፡፡ ይህም በሀገሪቱ የምርጫ ህግ ውስጥ የተካተተ መሆኑን መገንዘብ ይጠቅማል::ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል::

Read 1998 times