Saturday, 23 November 2019 13:19

ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አሁን
አምስት
በአዳራሹ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ግትሩ ሎቂሬ አሁንም በማንገናኝበት መንገድ ላይ ቆሞ እየጠበቀን ነው፡፡ ሁናቴው በጣም አሰልቺ እየሆነ መጣ፡፡ ሎቂሬም ከኛ በላይ ተንገሽግሾ አረፈው፡፡
በጭንቀት ቁልጭ ቁልጭ ማለታቸውን ያላቋረጡ ዓይኖቹን እኛ ላይ እያንከራተተ “ንገሩኝ እኮ ነው የምላችሁ …እስከ መቼ ነው ትልቁንም ትንሹንም ነገር እኔ የማብራራላችሁ…?” የምትል ጥያቄ ወረወረወብን፡፡ “መቼ ነው ራሳችሁን ችላችሁ የስም ዓይጠሬውን ፕሬዝዳንታችንን ንግግር ለመረዳት እና ለማስረዳት የምትሞክሩት?... መቼ ነው እባክህ ሎቂሬ አብራራልን ከሚል ጥገኛ አስተሳሰብ የምትላቀቁት?...መቼ ነው የምትለወጡት?... እየተሽቀዳደማችሁ እኔም ላስረዳ…እኔም ላብራራ የምትሉት መቼ ነው?...” ሲል ደነፋ ሎቂሬ…
በ“መቼ ነው” ድንፋታው ብንን ያሉት እማማ ኩንዳሬም “መቼ ቢሆን ይሻላል?” ሲሉ አጉተመተሙ፡፡ በእንቅልፍ ጫና የተከደነ ዓይናቸውን ሳይገልጡ…
የኛ ሳቅ ሊገነፍል ደረሰ፡፡ የሎቂሬ ቁጣም እንደዚሁ ጨመረ፡፡
የግንባሩ ደም ስር ተገታተረ፡፡ የዕልህ ሳግም ይተናነቀው ጀመር፡፡ ካንጀቴ የገነፈለበትን እንባ ለመቆጣጠር እየሞከረ…
“በተለይ ወጣቶች ልብ ብላችሁ እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ፡፡ ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንታችን እንደናንተ አልደላቸውም፡፡ የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉት ናይት ክለብ ሳይደንሱ…ፋሽን ሳይለብሱ…መጠጥ ሳይቀምሱ…ጫት ሳይቅሙ…ኮረዳ ሳይስሙ ነው፡፡”
ይህን ሲናገር ከከፍተኛ ሀዘን የመነጨ አንድ መንሰቅሰቅ ሰማሁ፤ መንሰቅሰቁን ተከትዬ ዘወር ስል ዋርሁም ፖፖን ተመለከትኩ፡፡ ይህን ለማመን ቢከብድም አፉን በመሀረብ ከልሎ በመንሰቅሰቅ ላይ የነበረው ራሱ ዋርሁም ነበር:: “ይሄ ትውልድ ከሀገሩ እና ከወገኑ ይልቅ ለፋሽን ለሴት፣ ለዳንስ፣ ለመጠጥ፣ ለጫት እና ለመሳሰሉት እርኩሰቶች ነው የሚጨነቀው” እያለ ሲያማርረን እንዳልኖረ ሁሉ---ይሄውና -- አሁን ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንታችን በወጣትነታቸው ፋሽንና ሴት ባለማሳደዳቸው፣ ባለመደነሳቸው፣ ባለመጠጣታቸው እና ባለመቃማቸው ትልቅ ነገር እንደቀረባቸው የተረዳ መስሎ ሲያለቅስ ተመለከትኩ፡፡
ሌሎቹም ሆዳሞች ተከትለውት ከንፈራቸውን ይመጡ ጀመር፣ ሎቂሬም ይበልጥ በስሜት ገንፍሎ መናገሩን ቀጠለ፡፡ “አዎን…እንደናንተ ሴት ሳያማልሉ…ኳስ ሳይከታተሉ…ፒዛ ሳይበሉ…” አለና ዝም አለ፡፡
ዓይኖቹን ባዶው አየር ላይ አፍጥጦ ዝም አለ:: ሌሎቹም በ“ሉ” የሚያልቁ ቃላትን በመፈለግ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “ምነው ደህና ዋሉ…” ብሎ ይሄን ስብሰባ በገላገለን እያልኩ በማሰላሰል ላይ ሳለሁም “ነገር ግን እሳቸው በወጣትነት ነፃ መብታቸውን እንደናንተ ሳይጠቀሙበት…የተሟላ ቤታቸውን ሳይኖሩበት …የወጣትነት እድሜያቸውን ሀሩር እየጠበሳቸው …ቁር እያንዘፈዘፋቸው …የቀይ ጥቁር ሆነው …ከሰውነት ተራ ወጥተው ወጣትነታቸውን በየበረሃው የፈጁት እናንተ በምቾት እንድትኖሩ እና በነፃነት እንድትናገሩ ነበር፡፡
ይሄ ያሁኑ ዝምታችሁ በርሳቸው ተጋድሎ እና በጓደኞቻቸው መስዋእትነት በተገኘው የመናገር ነፃነት ላይ እንደማላገጥ ይቆጠራል” እያለ የ“መልስ ስጡኝ” ጥሪውን አጠናክሮ እና አክርሮ አዳራሹን ከሞሉት የመስሪያ ቤታች ሠራተኞች ላይ ዓይኑን ቢያንከራትትም እስካሁን ጥሪውን ተቀብሎ እጁን ያወጣ ሰው አልነበረም፡፡ ወደፊትም ለመንጠራራት ካልሆነ በቀር ብስጦን ለማብራራት ማንም እጁን እንደማያወጣ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
መሳሳቴን ያወቅኩት ሎቂሬ እጁን ወደ አንድ አቅጣጫ ወርወር አድርጐ “እሺ እዚያ ጋ” ሲል ነው፡፡ የሁላችሁንም ዓይኖች የሎቂሬ እጅ ወደተወረወረበት አቅጣጫ ተወረወሩ፡፡ ፍልጥ ፍልጥ ጥርሶቹን ከጢሙ መሀል ፍልጥጥ አድርጐ “አመሰግናለሁ የድካው ልጅ…” ሲል ሰማን፡፡ ከዚያም “ሁሉም ነገር የተጀመረው ቅዳሜ ምሽት ነው…” ሲል ጀመረ ጅባካ…
“ያው እንደሰማችሁት ቅዳሜ ምሽት ስም አይጠሬው ፕሬዚዳንታችን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አስደናቂ እና አነቃቂ የሆነ ታሪካዊ ቃል ተናግረዋል፡፡ ቃሉም --ብስጦሽቁዋጭቁዋጣሽ..ነው፡፡ በዚያ ምሽት ያንን እንግዳ ቃል በተናገሩበት ቅጽበት መጀመሪያ ፊቴ ድቅን ያላችሁት እናንተ ናችሁ፡፡
ለመሆኑ ስም አይጠሬነታቸው በዚያ እንግዳ ቃል በኩል ያስተላለፉት ሚስጥራዊ መልዕክት ምን ያህል ይገባቸው ይሆን ስል አሰብኩ” ብሎ እንደመመሰጥ አለ፡፡ ፍልጥ ፍልጥ ጥርሶቹን ፍልጥጥ አድርጐ…
እኔም እንደዚህ ያለ ግልጽ ኤረር ውስጥ ምን ዓይነት ሚስጥራዊ ፍቺ ሊያወጣ ይሆን እያልኩ…ያንንም ሚስጥራዊ ፍቺ ካሁኑ እየፈራሁ ጥርስ ጥርሱን በስጋት በመመልከት ላይ ሳለሁም “የዚህን እንግዳ ቃል ትርጉም ከብስጦ እጀምራለሁ” አለ፡፡
“ስም አይጠሬው ፕሬዚዳንታችን ብስጦ ሲሉ በአንድ በኩል በኛ ተጋድሎ የተደመሰሰው ወታደራዊ መንግስት ሩቅላዋን አከብራለሁ…ሙኢኛንም እናገራለሁ…ያሉትን ሁሉ እየረሸነ እና እየጨፈጨፈ ሚስቶችን ያለ ባል…ልጆችን ያለ አሳዳጊ…እና ወላጆችን ያለ ጧሪ ባስቀረበት አሰቃቂ ዘመን የነበረውን ንኩን ብስጦን ማስታወሳቸው ነው፡፡  
ምንጭ፡- (ከደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር” የተሰኘ አዲስ ልብ ወለድ መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ፤ ጥቅምት 2012 ዓ.ም)


Read 3211 times