Saturday, 23 November 2019 13:23

አደራው

Written by  እስክንድር ኃይሉ (eskhailu@gmail.com)
Rate this item
(4 votes)

   ጸጉሬን  እየተቆረጥኩ ነው - “ታምሩ የወንዶች ባርበሪ”። ፀጉር አስተካካዩ ወሬ ይዟል፤ ሙግት ብለው ይሻላል፤ ቤቱን ካከራዩት ሠው ጋር። እኔ ግን ትዕግስቴ እየተሟጠጠ ነው።
“አረ እባክህ ቶሎ በልልኝ፤ እዚህ ዋልኩ እኮ” አልኩ በብስጭት።
መልስ አልሠጠኝም፤ ሙግቱን ቀጥሏል።
“ስማ ታምሩ፤ ነግሬሃለሁ። 2000 ብር ከበደኝ ካልክ፣ እቃህን ጠቅልለህ ውጣ!” አሉ አከራዩ።
ታምሩ፣ በቶንዶስ በቀኝ በኩል ፀጉሬን ለማስተካከል ዞሯል፤ የግራውን ሳይጨርስ። ቀልቡ ስራው ላይ አይደለም፤ እያየም አይመስለኝም የሚቆርጠኝ። ይባስ ብሎ ቶንዶሱን አስቀምጦ አከራዩ ላይ አፈጠጠ።
“ለዚህ ኩሽና 2000 አልከፍልም። እወጣልዎታለሁ። ይብላኝ ለርሶ እንጂ፣ ደንበኞቼ የሄድኩበት ይከተሉኛል”
“ጥሩ፤ ዛሬውኑ ውጣልኝ”
“ሠውዬ፣ እኔን መጀመሪያ አስተካክለህ ጨርስና ትወጣለህ” አልኩ - ቢቸግረኝ።
ሞባይሌ ይጮሀል፤ ከቅድም ጀምሮ። አላነሳሁትም፤ ባለቤቴ ነች።
ዛሬ ጠዋት ተጣልተን ነው የተለያየነው። መጣላት ሳይሆን ትንሽ ግጭት ብጤ። ዛሬ ቢሾፍቱ ለስራ ሄዳለች። አዳሯን ነው የሄደችው። መሄድዋ አደለም ያናደደኝ። በጠዋት፣ ጎረቤታችን ወ/ሮ አማከለች ጋ ሄዳ፣ እሷ ስለማትኖር ልጃችን ከትምህርት ቤት ስትለቀቅ እንድያመጥዋት አደራ ስትላቸው አበገነችኝ። እኔ አባትዋ እያለሁ፤ ባዳ መለመን? እኔ አልችልም አላልኳትም።
በዚህ ተናድጄ ነው በጠዋት አምቧጓሮ የፈጠርኩት። “አይ ያንተ ነገር። አንዴ አልተመቸኝም፤ አንዴ ረሳሁት ብለህ እንዳትቀርባት ብዬ ነው” ስትለኝ የበለጠ ቱግ አልኩ። ረሳሁት ብለህ?... እንዴት ነው ልጄን የምረሳው! ደግሞስ፣ ስራ የት አለና ነው፣ ልጄን ከት/ቤት ለማምጣት ጊዜ ያጣሁትና ያልተመቸኝ። ደላላ ሁሉ በየካፌው ድዳችንን አስጥተን አደል እንዴ የምንውለው። ይሄን ደግሞ ጠንቅቃ ታውቃለች። በተለይ፤ በሚጡ ጉዳይ ለአደራ አትበቃም ብላ እንደ ዘበት መናገር ልማድዋ ነው። ይሄ በጣም ያናድደኛል። ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ፣ በጣም ብሶባታል። ምንም እድል አትሰጠኝም።
መቆጣቴን አይታ መለስ አለች። “እሺ፤ እኔማ እንደ ሌሌሎቹ ልጆች፣ አባትዋ ቢያመጣት ደስ ይለኛል” ስትል፣ ተቃጠልኩ። እኔ ከሌሎች አባቶች አንሳለሁ?
“ብቻ፣ አደራህን ዘጠኝ ሰዓት ከት/ቤት ስለምትለቀቅ፤ እሩብ ጉዳይ ድረስላት። ብቻዋን እንዳትቀር አደራ!!!”
ያደራው ብዛት!
ልጄን ከት/ቤት አምጥቺያት አላውቅም። እንዴት አድርጌ? እድሉ መች ተሰጥቶኝ። ሚጡ፣ ዛሬ ከት/ቤት የማመጣት እኔ እንደሆንኩ ስትሰማ፣ በደስታ ፈነደቀች - “ባቢ ጓደኞቼ አባት የለሽም እያሉ ይተርቡኛል። ዛሬ አሳያቸዋለሁ፤ ታድዬ”። ወይኔ ልጄ! ሳልሞት በቁሜ።
ንዴቴን ለመወጣት፣ ወ/ሮ አማከለች ቤት ሄጄ፤ “ተውት ግድየለም። ልጄን እኔ አመጣታለሁ” አልኳቸው ኮስተር ብየየ።
“እርግጠኛ ነህ? እኔ እኮ ምንም ስራ የለኝም። ተጎልቼ ነው የምውለው” ብለው መለሱልኝ።
እርግጠኛ ነህ ብለው ይጠይቁኛል! ምን አይነት ጥያቄ ነው! ለነገሩ አልፈርድባቸውም። ዞሮ ዞሮ የባለቤቴ ግርፍ ናቸው። ከባለቤቴ የሰሙትን ነው መልሰው የሚነግሩኝ። “እኔ አመጣታለሁ አልኩዎት እኮ” ብዬ ጥያቸው ወደ ጉዳዬ ሄድኩ።
ከጠዋት ጀምሮ ሌላ ሃሳብ አልነበረኝም። ልጄን ከት/ቤት የማምጣት ጉዳይ ብቻ! አለም ብትገለበጥ ዛሬ አላረፈፍድባትም። ሚስቴንም ዛሬ አሳያታለሁ! እኔ ነኝ ለእምነት የማልበቃው? “ተሳስቻለሁ፤ ይቅር በለኝ ነው የማስብላት”!
ካፌ ቁጭ ብዬ አስሬ ሰዓቴን አያለሁ። ሌላ ነገር ማሰብ አልቻልኩም። ጊዜው ደግሞ ገና ነው። ካፌ ቁጭ ብዬ በጭንቀት ከምብከነከን፣ ልንቀሳቀስ... ወደ ት/ቤቱ ጠጋ ልበል... ብዬ መንገድ ጀመርኩ። ሚኒ ባሱ ሀያሁለት ጣለኝ። ት/ቤቱ ቅርብ ነው፤ የአስር ደቂቃ መንገድ ቢሆን ነው። ገና አንድ ሰዓት ተኩል ይቀራል። አይ ጭንቀት! ዝም ብዬ ነው ምሳዬን ሳልበላ በርግጌ መንገድ የጀመርኩት። ተረጋግቼ ጊዜውን መጠቀም እችላለሁ። ፀጉሬን ለመስተካከል “ታምሩ የወንዶች ባርበሪ” ዘው አልኩ። ፀጉር ለመቆረጥ ቢበዛ 30 ደቂቃ ቢፈጅብኝ ነው።
“እስኪ እግዜር ያሳያችሁ። ሀያሁለት አካባቢ፣ በ1000 ብር የሚከራይ ቤት ይገኛል እስኪ እናንተ መስክሩ”፣ አከራዩ ወደ እኛ እያዩ ተናገሩ።
“ደግሞ ይሄን ጉድጓድ፤ ቤት ብለው ነው የሚያስፈራሩኝ፤ ስሙልኝ ብቻ!”፣ ታምሩ በተራው የደንበኞችን ፍርድ ይማፀናል።
“ጣሪያው እንደጉድ ያፈሳል። በክረምትማ ቤቱ ባህር ነው። ስራ መስራት አይቻልም። በዚያ ላይ ሽንት ቤቱ፣ የሰፈር ቆሻሻ መጣያ ነው የሚመስለው። መንገደኛው፤ ሠካራሙ ሁሉ ነው የሚገባበት። ለዚህ ነው 2000 ብር የምከፍለው? ያሾፋሉ?”
“አማርኛ አይደለም እንዴ የምናገረው? ካልቻልክ ውጣ፤ ለሌላ አከራየሁዋለሁ!”
በቃ፤ ከገባሁ ጀምሮ እንደዚሁ ያለ እረፍት ይጨቃጨቃሉ። በቶንዶስ ነካ ነካ ያደርገኝና፣ ወዲያው ተመልሶ ንትርኩን ይቀጥላል። ከእኔ በኋላ የመጣው ሠውዬ ተስተካክሎ ሄደ። እሱን ያስተካክለው ተቀጣሪ ነው፤ የእኔ አሰተካካይ ዋናው ባለቤት ነው። አይ እድሌ!
ስልኬ እንደገና ጮኸ። ሚስቴ ናት።
“እኔ ወጥቼ ማን ሊገባልዎት፤ ባዶውን ታቅፈውት ነው የሚቀሩት፤ እኔ እንደሆንኩ…”
ስልኬ ይጮሀል!
“ወይ አንሳው፤ ወይ አጥፋው። አላስወራ አልከን እኮ!” ታምሩ በቁጣ ጮኸበኝ።
ለሱ ብዬ ሳይሆን፡ ሚስቴን ለማረጋጋት ስልኬን አነሳሁ።
“ለምንድን ነው ስልኬን የማታነሳው፤ ተጭንቄ ልሞት ነው” አለች ሚስቴ።
“ሳይለንት ላይ አርጌው ነው። ሁሉ ነገር ሰላም ነው” ብዬ ዋሸሁ።
“ደረስክላት! ዘጠኝ ሰዓት ሆኗል!”
ለአፍታ ቃላት ጠፉኝ።  “እ… አዎ…ደርሼአለሁ። ከሩቅ እያየሁዋት ነው”  ሌላ ውሸት።
“ሚጡን አየሃት? እርግጠኛ ነህ?”
“ልጄ ትጥፋኝ እንዴ? ጀመርሺኝ ደግሞ! በይ ቻው ቻው” ስልኩን ዘጋሁባት - “አቅርባት፣ ላናግራት” ብላ ጉዴ እንዳይፈላ።
ሰዓቱ ግን አስደንግጦኛል። 9 ሰዓት! እንዴት ሄዷል እባካችሁ።
ብድግ አልኩ! ፊቴን በመስታወት ስመለከት፤ ሌላ ድንጋጤ ተጨመረብኝ። ፀጉሬ ግጥብጥብ ብሏል። ከግራና ከቀኝ መድምዶኛል። ከፊት ያለውን አልነካውም። ከበስተኋላ ደግሞ፣ ጀምሮ ትቶታል። የባለገር ልጅ ባለ ቁንጮ አድርጎኛል። ተራ የሚጠብቁ ደንበኞች በሳቅ ሲጉተመተሙ፣ ደምስሬ በንዴት ተገታተረ።
“ስማ እንጂ! ትቀልዳለህ? ምንድነው እንደዚህ ገጥበህ የተውከኝ” አለኩ በቁጣ።
አጅሬ ሊደነግጥ ነው! “ታገሳ! መቼ ጨረስኩ” መልሶ እኔን ተቆጣኝ።
“ከአንድ ሰዓት ተኩል እዚህ ጎልተኸኝ ነው፤ ታገስ የምትለኝ? ገንዘቤን ከፍዬ እኮ ነው የምቆረጠው”
“እዚህ እኮ ቁምነገር ነው የያዝነው! መታገስ ካልቻልክ መሄድ ትችላለህ” ብሎኝ ቁጭ።
ሰዓት አልፎብኛል፤ መሄድ አለብኝ። ግን እንዴት ነው እንደዚህ ሆኜ የምሄደው።
ተቀጣሪውን ፀጉር አስተካካይ እንኳን ጨርስልኝ እንዳልለው፣ አዲስ ደንበኛ ያዟል። አሳዘንኩት መሰል፤ “ሃያ ደቂቃ ይስጡኝ፣ ቀጥዬ እርስዎን አሰተካክልዎታለሁ” አለኝ።
ሃያ ደቂቃ፣... አንድ ደቂቃም የለኝም። ልጄ ት/ቤት ደጃፍ ብቻዋን ቀርታ ቁልጭ ቁልጭ ስትል ታየኝ። የሚስቴም ቁጣ ታየኝ፡ ደግሞም ልክ ነች። ለማስረዳትም ይከብዳል። ለመውጣት ኮቴን ከተሰቀለበት አወረድኩ።
“ሂሳብ” አለ ይሄ የማያፍር ሰውዬ። ብልጭ አለብኝ። ቶንዶሱን ቀምቼ አናቱን ብለው ደስ ባለኝ። ሳፈጥበት፤ “በቃ ግዴለም፤ ዛሬ ምሬሀለው”
አለ። የማነው ደረቅ!
አከራዩ ይስቃሉ፤ “አይ ታምሩ! ደንበኞቼ የሄድኩበት ይከተሉኛል ስትል አልነበረም? እስኪ ይሄ ሰውዬ ሲከተልህ እናያለን” ሲሉ አንጀቴን አራሱኝ።
ከኪሴ የቢዝነስ ካርዴን አውጥቼ ለአካራዩ ሰጠሁዋቸው። “ጋሼ! ካርዴን ያዙ። ደላላ ነኝ፤ ቤትዎን ዘንጠው 3000 ብር እኔ አከራይልዎታለሁ” አልኳቸው።
“እግዚሀብሄር ይባርክህ ልጄ! ይሄ ሞላጫ 2000 ብር አልከፍለም፤ ሲል 3000 ብር የሚከፍል ተገኘልኝ፤ ታምሩ፤ ሰማህ - 3000 ብር!”
“በነፃ ባስተካከልኩህ ጠላት ትሆነኛለህ? ሁለተኛ እዚህ ቤት ድርሽ እንዳትል” አለኝ ታምሩ።
መልስ ለመስጠት ጊዜ አልነበረኝም። ወጥቼ እየከነፍኩ ወደ ልጄ ት/ቤት ዳገቱን በሩጫ ተያያዝኩት።
በራሴ በጣም ነው የተናደድኩት። ሚስቴ የፈራችው ደረሰ። ያንድ ቀን ፈተና ማለፍ አቅቶኝ፤ እንደዚህ ልውደቅ? ት/ቤቱ ደጃፍ ስደርስ፤ ተማሪዎች የሚሄዱባቸው ሚኒባስ ታክሲዎች፤ የቤት መኪናዎች ቆመዋል።
ግራ ተጋባሁ! ያረፈድኩ መስሎኝ ነበር። ሳይ ግን፤ ተማሪዎቹ ገና አልወጡም። ቁና ቁና እየተነፈስኩ አንዱን ወላጅ ስጠይቅ፤ “ዘጠኝ ተኩል ነው የሚለቀቁት፤ ገና 15 ደቂቃ ይቀራቸዋል” አለኝ፤ ፀጉሬን በመገረም እየተመለከተ። እንዴ፤ ሚስቴ 9 ሰዓት ነው የሚለቀቁት አደል እንዴ ያለችኝ? ፈንጠር ብዬ ልጄን መጠበቅ ጀመርኩ።
ጎረቤታችን ወ/ሮ አማከለች፤ ቱስ ቱስ እያሉ ከች አይሉ መሰላችሁ? “ወ/ሮ አማከለች እዚህ ምን ይሰራሉ፤ እኔ አመጣታለሁ ብየዎት አልነበረም እንዴ?” ብዬ አፈጠጥኳቸው። “ኧረ እኔ፣ ሾላ ገበያ እየሄድኩ ነው። ደግሞ ገበያም አትሄጂም ብለህ ልትከለክለኝ ነው? ሆ! ሆ!” ብለው ተሞጣሙጠውብኝ መንገዳቸውን ቀጠሉ። ልቤ ግን አላመናቸውም።
ዘጠኝ ተኩል ተደወለ። ልጆቹ አንዴ ግር ብለው ወጡ። እኔም እንደሌሎች ወላጆች በጉጉት ሚጡን ፍለጋ ዓይኔ ወዲያና ወዲህ ይቃኝ ጀመር።
ከሩቅ አየሁዋት። ጓደኞቿ አጅበዋታል፤ ለምን እንደሆነ ገባኝ፤ አባቴን ላሳያችሁ ነው ጨዋታው።
እጄን ሳወዛውዝ አይታኝ፤ “ባቢ! ባቢ! ያውና አባቴ” እያለች እየሮጠች መጣች። ጓደኞቿ ይከተልዋታል። እኔ ጋር ስትደርስ፣ ፈገግቷዋ ተቀይሮ ሽምቅቅ አለች። ጓደኞቿ፣ መሳቅ ጀመሩ። ልጄ ደግሞ ማልቀስ። “ባቢ ምን ሆንክ! ጓደኞቼን አንተን ላስተዋውቃቸው ብዬ... እንደዚህ ታዋርደኛለህ? ፀጉርህ ምንድን ነው?”
ምን መልስ አለኝ?
  እኔማ ዛሬ ብዙ ነገር አስቤ ነበር። ከልጄ ጋር አሪፍ ጊዜ ላሳልፍ፤ ኬክ ጋብዣት፣ ግዮን የልጆች መጫወቻ ቦታ ልወስዳት ነበር። ነገር ሁሉ ተበላሸ።
ሚኒ ባስ ውስጥ ግማሹ ሲስቅብኝ፤ ግማሹ ሲጠቋቆምብኝ እንደተሳቀቅኩ ሰፈር ደረስን። ቤት ስንገባ ሚጡ አኩርፋ ቁጭ አለች። እኔም ይውጣላት ብዬ ዝም አልኩ።
ቀስ እያለች እየሠረቀች ታየኝ ጀመር። በመጨረሻ፣ መሳቅ ጀመረች። እኔንም አሳቀችኝ። አይ የልጅ ነገር! የገጠመኝን አወራኋት። ለሷ ከማረፍድባት ያገር መሳቂያ መሆንን እመርጣለሁ። አቅፋ ሳመችኝ። “ከእንግዲህ ወዲያ ከት/ቤት አንተ አምጣኝ” አለችኝ። ከእንግዲህማ አባትነቴን ማንም አይነጥቀኝም። እንደማመጣት ቃል ገባሁላት።
ልጄ እንደተኛችልኝ ሚስቴ ጋር ደወልኩ፤ እንዴት እንዳናደደችኝ! ዘጠኝ ተኩል የምትለቀቀውን ልጄን ዘጠኝ ሰዐት ብላ ትዋሸኛለች? ያረፍዳል ብላ እኮ ነው፤ ፀጉሬን በአግባቡ የምስተካከለውን፤ ወይኔ ያገር መሳቂያም ሆንኩ እኮ፤ ቆንጮ? በአሁን እድሜዬ? ሆ! ሆ!፤ ሚስቴ ስልኳን አታነሳውም፤ ይበልጥ ተናደድኩ፤ ደግሞ ረስቼው ይባስ ብላ ወ/ሮ አማከልቸን መላክዋ! እሳቸውንማ ቆይ ብቻ ልክ ልካቸውን የምነግራቸው፤ ብድግ ብዬ፤ ቤታቸው ሄድኩ ፋታም አልሰጠሁዋቸውም፤ እንደገባሁ ተንጣጣሁባቸው፤
“የሰው ትዳር ሊያፈርሱ ነው? በማያገባዎት ገብተው የሚበጠብጡት” ምን ያላልኩዋቸው ነገር አለ፤ ወረድኩባቸው፡፡
ዝም ብለው አዳመጡኝ።
  “ቁጭ በል ልጄ! የምነግርህ ነገር አለ” ፊታቸውን ቁምጭጭ አደረጉ
“ባለቤትህ ብሸፍቱ የሄደችው ለስራ አደለም፤ ዝቋላ ጠበል ልትጠመቅ ነው”
“የምን ጠበል? ታማለች እንዴ?”
“አዎ ስድስት ወር ሆናት ከታመመች፤ ሀኪም ከእንግዲህ ሶስት ወር ብቻ ነው የቀረሽ ብሏታል”
አለም ተገለባበጠችብኝ
“የልጅዋ ነገር ጨንቅዋታል፤ አደራው ላንተ ብቻ አደለም፤ ለእኔም ነው ልጄ”
በድንጋጤ ደነዘዝኩ፤
ቤቴ ገብቼ፤ ልጄን አቅፌ፤ ጣራ ጣራውን እያየሁ ተኛሁ።

Read 2808 times