Saturday, 23 November 2019 13:25

የአገር ቤት ጨዋታ

Written by  በታደለ ገድሉ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

    “--መቼም አንተ ዘምተህ ሙያ አትሠራበት
እኔስ በአገልግሌ ፈትል አረኩበት፣
እኔስ በናእጃዬ ፈትል አኖርኩበት፣
አንተ በመሣሪያህ ምኑን ሠራህበት
ከማጀት ግባና ድፍድፉን ዛቅበት፡፡ --”

ወላጅ እናቴ ወ/ሮ ትሁን አሸነፍከ፤ ቀልድ መቀለድ፣ ጨዋታ መጫወት፣ ግጥም መግጠም፣ ተረት መተረትና መዝፈን ትወድድ ነበር። ቀደም ሲል ከትዝታዋ ማኅደር እየመዘዘች እንዳጫወተችኝ፤ በቀድሞ ዘመንና አሁንም አልፎ አልፎ  በተለይም በገጠሩ አካባቢ ትዳር ለመያዝ ሲፈለግ ወንዱ የእርሻ፣ የአደን፣ የዋና፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የተኩስ ሙያ ቢያውቅ፣ ሴቷ ደግሞ እንጀራ መጋገር፣ ጠላ መጥመቅ፣ ወጥ መሥራት፣ መፍተልና፣ መስፋት ብትችል ይመረጥ ነበር፡፡ በሁለት ተጋቢ ቤተሰቦች መካከል የሚመሠረተው ጋብቻ፤ እነዚህን ነገሮች ከሞላ ጐደል መነሻ ያደርግ የነበረውም ትዳሩ የተቃና እንዲሆን በማሰብ ነው፡
በወላጅ እናቴ ወ/ሮ ትሁን አሸነፍከ አባባል፤ ትዳሩ ከተመሠረተ በኋላ ጠንካራ የሆኑት ባልና ሚስት ተፋቅረው፣ ልጆች ወልደው ንብረት አፍርተውና ‘’አንቱ’’ ተብለው ሲኖሩ፤ ኑሮ ያልተሳካላቸው፣ ፍቅር ያላስተሣሠራቸው፣ በስንፍና የተሞሉት ደግሞ ኑሮአቸው የንዝንዝ፣ የጭቅጭቅ፣ የንትርክ፣ የሁከት፣ የቅንዓት፣ የመናናቅ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ከነአካቴውም ትዳራቸው የሚፈርስበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ የትዳሩ መፍረስ ምክንያት በባል ወይም በሚስት ሊላከክ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የማይጥም፣ የማይረባና ጠንክሮ የማይሠራ ባል የገጠማት ሴት፤ ዐረም ስታርም፣ ወፍጮ ስትፈጭ፣ እንጀራ  ስትጋግርና አሻሮ ስትቆላ፤
‘’ሁለት ለምድ አጎዛ መጨገያ የነሣው’’
ወድዳ የከረመች ይመስለዋል  ለሰው፡፡  
ወይኔ ልጅቱ እንዲያው ተበላሸሁ
የጠጂቱ ገንቦ ባተላ ተሟሸሁ።
አታሞ ሲመታ ልቡ እማይደነግጥ፤
ይህስ አህያ ነው ወንዝ ወንዙን የሚግጥ፡፡
አታሞ ሲመታ የማይገሸንጠው፣  
ይኸስ አህያ ነው ገበያ እሚሸጠው፡፡  
ደራርበው ቢይዙት አይከብድም በርበሬ፣  
አንተስ ያካርሚኝ ነህ እንደቅጥር በሬ፡፡  
አጋማሽ ዘንጋዳ ያለልክ አቡከቼው፣
ሞላ ገነፈለ መሄዴ ነው ትቼው፡፡”
-- እያለች ብሶቷን በእንጉርጉሮ ትገልጻለች።
 እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቤቱን በደንብ የማትይዝ እንቅልፋምና ሰነፍ ሴት የገጠመችው ባልም እንዲህ እያለ በሚስቱ ላይ ይዘፍናል፤
‘’ ---ማበለቻውን ዶሮ ደፍቶብሽ፣
መሰቅሰቂያውን ልጁ ጥሎብሽ፣
ከወደኋላሽ ጨርቅሽ አልቆብሽ፣
የአምቻ እንግዳ ተቀምጦብሽ፣
በጓሮ ሆኜ  ወየው ስቄብሽ፡፡
ተሰብሰብ ጐረቤት እይልኝ ጉዷን፣
ቀለቧን ሰጥቼ ትልቀቀው ቤቴን፡፡
‘’አስፈጨው አለችኝ አስፈጨሁላት፣
አስቦካው አለችኝ አስቦካሁላት፣
አስጋግረው አለችኝ አስጋገርኩላት፣
አቅርበው አለችኝ አቀረብኩላት፣
አጉርሰኝ አለችኝ ጉርሻ ሰጠኋት፣
በአፏ እንደያዘችው እንቅልፍ ወሰዳት፣  
ልብ አድርግ ጉልቻው እሳት ቢፈጃት፣
ወርጄ ወጥቼ እናቷን ልጥራት፡፡
የጭልምልሜ እናት እመይቴ ሰገዱ፣
እሳት ይፈጃታል ልጅዎን ይውሰዱ፤
ብዬ ብነግራቸው እየተናደዱ፤
እንኳን ሊወስዱልኝ ትክረም ብለው ሄዱ፡፡”
--- እያለ የሚስቱን ስንፍና ይናገራል፡፡
በተለይም ባል ባለጠመንጃ ሆኖ ግን በጠመንጃው ሙያ ካልሠራበት፣
ሚስት ንቀቷን በግጥም መግለጧ አይቀሬ ነው።
‘’ስጠኝ መሣሪያህን እንኩሮ ላውጣበት፤
መቼም አንተ ዘምተህ ሙያ አትሠራበት፡፡
እኔስ በአገልግሌ ፈትል አረኩበት፣
እኔስ በናእጃዬ ፈትል አኖርኩበት፣
አንተ በመሣሪያህ ምኑን ሠራህበት
ከማጀት ግባና ድፍድፉን ዛቅበት፡፡
የበርበሬ ጥላ አያስጥል ጠሐይ፤
እኔ ሰው መስለኽኝ ቁመናህን ባይ፣
ባሌን ውሽማ አርጉት ሳልሰማ ሳላይ፤
ለውሻ ዳረጐት ጥዬ አላውቅም ወይ፡፡
--- እያለች በነገር ስትጋረፍ፣ እርሱም በእርሷ ላይ ያየውን እንከን እንዲህ  ይገልጠዋል፡፡
‘’አለ ጠመንጃዬ ክፉ አትናገሪ፣
ያውልሽ አልጋ ላይ አውርደሽ አንኩሪ፣
መቼም አንቺ ጥደሽ ደኅና አትጋግሪ፡፡”
--ይህ ስለ ምን እንጀራ መጋገር የማትችል መሆኗን ያስረዳል፡፡ የማይሠራውንና ቀኑን ሙሉ ከቤት ተጐልቶ የሚውለውን ባል፣ ጐረቤቶችም ስለማይወዱት፤  
‘’--- በጋ ጠሐይ ፈሪ ክረምት ዝናም ፈሪ፣
ልጁ እንጀራ ሲለው በጅብ አስፈራሪ፡፡
ይኼ ነወይ ባልሽ የተጐልቶት፣
እኔስ ጉዲት መስሎኝ ልቀመጥበት፡፡
ይኸ ነወይ ባልሽ በደጀ ያለፈው፣
አንደበሬ ቆዳ የተንከረፈፈው፣
ይኸ ነወይ ባልሽ በደጀ ያለፈው፡፡
አህያ ነው ብዬ በዱላ ልዘርፈው፡፡”
---እያሉ ይዘፍኑበታል፡፡ ወላጅ እናቴ እንደነገረቺኝ፤ ቀጭን ከወፍራም እየፈተለች ቤተሰቧን የምታለብስና ታቦት የምትስም ሴት በገጠሩ ከፍተኛ ከበሬታ ሲኖራት፣ የማትፈትለዋ ደግሞ ትተቻለች፤ ትናቃለች፡፡  
“ጀበና ታቦቱ ስኒ ልቃቂቱ፣
መገነዣ ጠፋ እናቷ ቢሞቱ፡፡
ባመት ተመንፈቋ ብታሠራ ኩታ፣  
ዘመዶቿ ሁሉ ሊሞቱ ደስታ፡፡
ባመት ተመንፈቋ ብታሠራ ቀሚስ፣
ዘመዶቿ ሁሉ ይሏታል ግንድ አልብስ፡፡”
---እየተባለ ይቀለድባታል፡፡ በትጋት የማትፈትለዋንና በሌሊት እየተነሣች እህል የማትፈጨዋን ሚስት፤ ባልም እንደዚህ እያለ ይተቻታል፡-
‘’ --- በዓመት ሡሪ ፈታይ በወር  ሽልቃቂ፣
ሂጂ ወደናትሽ አትሞሻለቂ...’’  
እንዝርቱን ብትይዥው መቼም አያምርብሽ
ወስፌውን ብትይዥው መቼም አያምርብሽ
ማርጣውን አንስተሽ ለጥፊው ከሬብሽ፡፡
« ደጋኑ አለቀሰ ተኝተሽ ሌሊት፤
ወፍጮው አለቀሰ ተኝተሽ ሌሊት፤
ተጣብቋል መሰለኝ ጐንሽ ከመሬት፡፡  
ግልገል ዶሮ ሲጮህ አትነሽም ወይ፣
ደግሞ እንደልብሳችን ዱቄት ልግዛ ወይ፡፡»
እርሻ የማያውቅና ጅላጅል የሆነ ባል የገጠማት ሚስት ደግሞ፡-
«እሳቱን አንድደው አኔ ልተኛ ነው፣
ተነሥ ውኃ ቅዳ አንሥራው ባዶ ነው።  
ዘንጋዳ ፍጭ ስልህ ያንን እንጉላይ፤
ከዚያው ቀንሽልኝ ማለትህ ነወይ?
ከዚያው ቀንሽልኝ ማለቱን ተውና፣  
ዝም ብለህ ተቀምጥ ስሙ ባል ነህና፡፡  
ሥራ የማይሠራ ሰነፍ ባል እግብቼ፤
እህል እህል ሲሉ ከረሙ ልጆቼ፡፡»
---በማለት ትዘፍንበታለች፡፡ ሙያ የሌላትና ነዝናዛ ሚስት የገጠመችውም በዕድሉ እያዘነ እንደዚህ ይቆዝማል፡-
‘’ሙጃሌ ተጉዛ ሙጃሌ ተጉዛ፣
ስትኖር ተነዛንዛ ስትሄድ ገንዘብ ይዛ፤
የሠራሁትን ቤት ጣለችው ወዝውዛ፡፡
ነዝናዛ ሚስትና ጨቅጫቃ ሚስት ያለው፣
ከሰው ለቅሶ አይሄድም እቤቱም ለቅሶ ነው፡፡
ሙያ እምታውቅና ተወዳጅ ሚስት ያለው፣
ከሰው ሠርግ አይሄድም ከቤቱም ሠርግ ነው::
እንዲህ ወደጓሮ የተጮኸ እንደሆን፤
ሱሪዬን ስገፍሽ ምን ትለብሸ ይሆን---»
---እያለ ያንጎራጉራል፡፡ የባልና ሚስቱ የሌሊት ልብሳቸው (የባል) ሱሪ ብቻ መሆኑንም ግጥሙ ይገልጣል፡፡ እርሷም ባሏ እንቅልፋም ስለሆነ ሌሊት ተነሥቶ ለመውጣት እንደማይችል ታውቀዋለችና፡-     
‘’ያንተ ያብቃህ እንጂ ነቅቶ ለመነሣት፣
እኔስ ኮተት ብዬ እሞቃለሁ እሳት፡፡
ነጭ በልቶ  ዳጉሣ ድንች በልቶ መንገድ፣
ደረመን ይሆናል አይጠቅም ሰው
መውደድ።’’
---ብላ ትመልስለታለች፡፡  
መቼስ ባላገር ሲሠራ ውሎ አንድ እንጀራና ሁለት ብርጭቆ ጠላ ብቻ ቢሰጡት ጐኑ እንደማይነሣ ይታወቃል፡፡ እና ወ/ሮ አስናቁ አምጣቸው የተባለች ሴት፣ በደቦ እህል ለምታሳጭዳቸው ሰዎች በምሣ ሰዓት እህል ውሃ ይዛ ትሄዳለች፡፡ በደቦ ጤፍ የሚያጭዱት ገበሬዎች ምሳ ለመብላት ከመቀመጣቸው እንጀራው አልቆ ወጡ ብቻ መቅረቱን ይገነዘባሉ:: በዚህ ጊዜ፡-
“እቴ ምኑ ቅጡ እቴ ምኑ ቅጡ፣
እንጀራው አለቀ ሳይጀመር ወጡ፡፡»
--እያሉ በደጋሽዋ ሴት ሲያፌዙባት ይውላሉ። እርሷ ግን ‘’ማታ ደግሼ እክሳችኋላሁ» ብላ ወደ ቤት ብትመለስም ያዘጋጀችው ድግስ በእጅጉ ያንሳታል፡፡ እና ማታም አጨዳ የዋለው ሰው ከቤት ገብቶ አንዳንድ እንጀራና ውኃ የበዛበት ሁለት ሁለት ብርጭቆ ጠላ እንደቀመሰ ድግሱ ያልቃል። ይህን የተረዳው ባሏ ወደ ማጀት  ገብቶ ‘’አስናቁ’’  ብሎ ሲጠራት ‘’ኧረ ምኑ ቅጡ አያ ማማው’’ ትላለች። ሥራ ላይ የዋሉ ሰዎቹም ያለ ይሉኝታና ኀፍረት ወዲያው እንደሚከተለው ግጥም እየገጠሙ ያዋርዷታል:: እንዲህ በማለት፡-
‘’አያ ማማው መልስ አትወላገድ፤
ጠላው ሁለት ሁለት እንጀራው አንዳንድ፣
ይህችን ካልሰደድካት አትባልም ወንድ፡፡
አንድ እህል አንድ ውኃ ሲያደርጉ ብታይ፣  
በቧንቧ ሳበችው ሜደርን ከላይ፡፡”
---ብለው በወይዘሮ አስናቁ አምጣቸው ላይ ዘፍነውባታል፡፡ ሜደር ከደጀን  አካባቢ  ተነሥቶ ወደ ይጉል ባላገሮች መንደር እየተወረወረ፣ ወደ ዓባይ ወንዝ  የሚፈስስ የጅረት (የወንዝ) ስም ነው። እርሷም ይኸ ሁሉ ችግር የተከሠተው በባሏ በእቶ ማማው ስንፍና መሆኑን ለመግለጥ:-
‘’አልቀረበም እንጂ እህሉ ተሟልቶ፤
ጠላና እንጀራውን ወጡን አዘጋጅቶ፣
ብሉልኝ ጠጡልኝ ማለት መቼ ጠፍቶ፣»
---ብላ በመመለስ እንደዘፈነችባቸው እመዋ አውግታኛለች። ቂጣ ብቻ እየጋገሩ መብላት እህል ይጨርሳል ተብሎ ይታመናልና፣ አፍለኛ ቂጣ በየጊዜው እየጋገረች ከባሏ ተደብቃ መብላት የለመደች ሚስት ያገባ ጐበዝ ተግባሯን ሲገልጥ፡-  
«እዩልኝ ስሙልኝ እዩላት ስሙላት፤
ከእኔ ከተለየች ዳግመኛ ሆድ አላት።
ከእኔ ከተለየሽ የበላሽው ቂጣ፣  
ጮሌ ሴት ብትይዘው ነሐሴን ባወጣ፡፡»
---እያለ ይተርትባታል፡፡ በገጠሬው አካባቢ ያልተሳካ ትዳር ሲገጥም ባል ወይ ሚስት በድብቅ መቀማማትም የተለመደ ነው፡፡ ባል በጐረቤት አካባቢ ወዳጅ ካለችው፡-  
“መፍተል መዳመጥስ የኛም ልጅ ታውቃለች፣
ደግሞ እምታሳሳ በጐረቤት አለች።
ያገዳ ጐጆ ነው ጉብሌ ቤትሽ፤
እኔ ቀሪሽ ልሁን ጅብ እንዳይበላሽ፡፡”
--እያለ በድብቅ ፍቅሩን ይገለጣል። በይፋ መናገር ሲፈልግም፡-
‘’አንድ ላም አለችኝ እበላለሁ በርጐ፣
የጐረቤትን ልጅ እዚያው ኮተት አርጐ፡፡  
የጐረቤትን ልጅ የጓሮን በርበሬ፣  
እዚያው ኩርሸም ኩርሸም ሳያሰሙ ወሬ፡፡»
---በማለት ያንጐራጉራል፡፡ የገጠር ሴቶች በወንድ ሲጣሉም የስለ ምን ግጥም ይደረድራሉ::
የሰው ባል የነጠቀች ሴት፡-
“ከባላ ደንቆሮ አይደርስም ዘሀሽ፤
አንቺን ከእኔ ጋራ ማን ደረደረሽ፡፡  
ባልሽን ጠብቂው አሠርተሽ ማማ፣  
እኔማ የት ልሂድ ካባቴ ባድማ፡፡  
አልወራረድም ትበልጭኛለሸ፣
ድንኳን የተከለ ወጥ ትሠሪያለሽ፣  
ሻሽ የጠመጠመ ትጋግሪያለሽ፡፡  
ሐሰቴም እንደሆን ባልሽ ምስክሬ፣  
ጥርሱ ላይ ተገኘ የበርበሬው ፍሬ፡፡”
---እያለች ዋናዋ ሚስት ሙያ የሌላት መሆኗን ጭምር ገልጣ ታባጫታለች፡፡ ወጥ መሥራት/ እንጀራ መጋገር፣ በርበሬ፣ ማዳቀቅ ካልቻለች ሚስት መባል አይገባትም ስትላት ነው፡፡  
አምባ ለአምባ እየዞረ ጋለሞታ ሴት ሲፈልግ የሚውለውን ወንድም፡-
“ፉዴ የመንደሩ ፉዴ የመንደሩ፣
መዝጊያ የገፋበት ተልጧል ግንባሩ፡፡  
አምባ ላምባ  ‘’ፉዴ’’  እጀታ ከርካሚ፣  
ረጅም ጎፈሬ እባሽ ተሸካሚ፣  
እጀታ ከርካሚ ዓይነ ትልልቁ፣
መች ይሄዳል ሥራ ሴቶች ከአላለቁ፡፡”
--- እየተባለ  ይዘፈንበታል፡፡  
***
የቃላት ፍች፡-- ማበለቻ= የምጣድ ማሰሻ፡፡ መጨጊያ= ትራስ፡፡ አናጃ = ትልቅ ቅል (ፈትል የሚቀመጥበት ቅል) ዳረጐት = ቁራሽ እንጀራ፤ ጉርሻ፡፡ ጉዲት = ቁርጫ መደብ (‘’ዲ’’ ሲነበብ ይጠብቃል) ደረመን = እከክ ጉስቁልና፡፡ ማርጣ = የጎሽ ጭራ ግንባር የጀግንነት ምልክት:: ደንቆሮባላ = ዝሀ መዝጊያ (ማጠንጠኛ) ዕንጨት:: ፉዴ = ሠነፍ  አምቦዛላጭ  አውደልዳይ፡፡ እባሽ = የሻገተ እህል፡፡ አባጨ = ተሣለቀ፤ አፌዘ፡፡


Read 491 times