Saturday, 23 November 2019 13:27

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

  በሰማንያዎቹ አጋማሽ ገደማ ነው፡፡ በላሊበላ ከተማ አንድ እናት ዶሮ ይበልታሉ፡፡… የፋሲካ ዋዜማ እለት፡፡ እግረ መንገዳቸውን አጠገባቸው ለተቀመጠችው የሰባት ዓመት ልጃቸው ሙያውን ያስተምራሉ፡፡ አጋጣሚ ሆነና ከዶሮዋ ሆድ ውስጥ ትንሽዬ፣ የምታምር ‹ጉትቻ› ነገር አገኙ፡፡ አገላብጠው ሲያይዋት አንዳንድ የ‹ደህና› ቤተሰብ ሕጻናት ሴት ልጆች ጆሮአቸው ላይ የሚሰኳት ዓይነት ‹ጌጥ› መሰለቻቸው፡፡… ጠረግ፣ ጠረግ አርገው ለልጃቸው ሰጧት፡፡
‹‹ጆሮሽ ላይ አርጊያት››…
ልጅቱ ተቀብላቸው እያየች፤ ‹‹እማ… ማፈኛ ስለሌላት ትወድቅብኛለች፡፡ አንድ ብቻ ስለሆነች ደግሞ ልጆቹ ይስቁብኛል›› አለቻቸው፡፡
‹‹የግዜር ነገር አይታወቅም፣ ተመሳሳይ ሊገኝ ስለሚችል ሙዳዩ ውስጥ አስቀምጪያት›› አሉ እናት፡፡ …. ልጅት ግን ዓይኖቿ ነገርየዋን ተመልክተው ስላልጠገቡ በጣቶቿ እያሻሸች መጫወት ጀመረች፡፡ ስራዋን እንደዘነጋች ያስተዋሉት እናት፣ ተቀብለው መቀነታቸው ላይ ቋጠሯት፡፡
በጦር ጉዳተኝነት ምክንያት የሃኪሞች ቦርድ ጡረታ ያስወጣቸው የሴትዮዋ ባለቤት፣ የሚቀጥለውን ፋሲካ በሕይወት ለመኖር አልታደሉም፡፡ በጥበቃ ሥራ ተቀጥረው ለቤተሰብ የሚያመጧት ደሞዝ ተቋረጠች:: እናትና ልጅ ኑሮን መቋቋም ሲያቅታቸው እንደ ምንም አንድ ገንቦ ጠላ እየጠመቁ በመሸጥ ትንፋሻቸውን ለማቆየት መታገል ያዙ፡፡ እማማ ታከለች በኑሮ ውጣ ውረድ የሸመቱት የደም ግፊት ከዕለት ዕለት እየባሰባቸው ቢመጣም፣ ልጃቸው እንዳታውቅና ትምህርቷ እንዳይደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው አልቀረም፡፡ አንዳንዴ ግን ከአቅም በላይ እየሆነ ይጥላቸዋል:: ልጃቸው ስታድግ ችግሩ ስላሳሰባት እናቴ ተዳክማ የአልጋ ቁራኛ ከምትሆንብኝ “ዕድሌን ልሞክር›› በማለት ትምህርቷን ከአስረኛ ክፍል አቋርጣ ተሰደደች፡፡ ከአራት ወራት ፍዳና ስቃይ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ገባች፡፡ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላም ሌሎች ድሆች ‹‹ሎተሪ ወጣላት›› እንደሚሉት አይነት ዕድል አጋጠማት፡፡ በልቧ የወደደችው፣ በጽዳት ስራ የተቀጠረችበት፣ የውድ ጌጣ ጌጦች መሸጫ ሱቅ ባለቤት የሆነው የበኩር ልጅ አፈቀራት፡፡ ድንግልናዋን አይቶ፣ ታሪኳን ሰምቶ አከበራት:: በቤተሰቡ ባህልና ወግ ተጋቡ፡፡ ወዲያውም አስፈላጊውን ሕጋዊ ፎርማሊቲ ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት መዘጋጀት ጀመሩ:: ላሊበላ ደርሰው የእማማ ታከለችን ቡራኬ ለመቀበል ናፈቁ፡፡
አዲስ አበባ እንደ ደረሱ ያረፉት ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ …ወደ መዳረሻቸው አቀኑ:: ልጅቱ ሰፈር ሲደርሱ የተቀበላቸው እንግዳ ግን አስደነገጣቸው፡፡… የዕድር ድንኳን፡፡ እማማ ታከለች እንደትናንት አርፈዋል፡፡ የልጃቸው ናፍቆትና ችግር ተረባርበው ጣሏቸው፡፡…
***
ቀደም ብለው የተቀናበሩ ብዙ የሙዚቃ ድርሰቶች፣ ታላላቅ ስዕሎች ወይም ሌሎች የጥበብ ውጤቶች በምን ዓይነት መንገድ እንደተሰሩ ወይም እንደተዘጋጁ ለማወቅ ወይም መረጃ ለማግኘት በዚህ ዘመን አያዳግትም:: …ዕድሜ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ!!... ችግሩ የደራሲዎቹን ሀሳብና ፍላጎት በሳይንሳዊ መንገድ መረዳት አለመቻሉ ላይ ነው፡፡ ከግምት በስተቀር፡፡
ከሾፐን፣ ባህ፣ ሞዛርትና ቤትሆቨንን ጨምሮ የብዙ ፈጣሪዎች ብዙ ታላላቅ ድርሰቶች ሲሰራ (Performance ላይ) በሚፈጥረው ቃና ከመደሰትና መልዕክቱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሰዎች (ተፈጥሮን አይመለከትም) የመንፈስ መናወጥ የምንገነዘበው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው::… ሥዕልም እንዲሁ፡፡
አብስትራክት ወይም ኢምፕሬሽኒዝም የሚባሉትን ወደ ጐን ትተን፣ ፊት ለፊት በግልጽ ከሚታዩት (realistic ከሆኑት) ታላላቅ ስራዎች ውስጥ እንኳ ብዙዎቹ ከርዕሳቸው፣ ከአሳሳል ጥበብና ውበታቸው ከምንረዳው በላይ የተደበቀ ሚስጢር እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ሳይንስ ለጊዜው ይህንን ሊያረጋግጥልን አልቻለም:: ከነዚሁ ውስጥ “ሞናሊዛ” እና “የመጨረሻው እራት” እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ፡፡
ወዳጄ፡- የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥበብ፤ በኪሳችንና በቦርሳችን የያዝነውን፣ በሆዳችን የደበቅነውን፣ ጡንቻችን ውስጥ የቀበርነውን ነገር በቀላሉ ማወቅ ወይም መለየት ይችላል - ምስጋና ይግባው አእምሯችን ውስጥ ያለውን ክፋትና ደግነት ግን መለየት አልተቻለም፡፡ በ“መንፈሳዊ” ዕውቀት የበለፀገ የአእምሮ ፀጋ ግን በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ “Sciences gives us knowledge, but only philosophy can give us wisdom” እንደሚሉት፡፡ … “Sense” ሌላ!! “Sensor” ሌላ!
ሔንሪ ሚለርን ጨምሮ ብዙ ታላላቅ ፀሐፊዎች፤ ሳይንሳዊ ዕውቀት ዞሮ ዞሮ መጨረሻው ጥበብ ነው፣ የሰው አእምሮ ጥልቅና መዳረሻ ቢስ በመሆኑ ዕውነተኛ ደስታን የሚፈጥርለት ረቂቅና ፍፁም ከሆኑት የስሜት፣ የመንፈሳዊነትና በነሱም በኩል በሚደርሰው የ“መገለፅ” ፀጋ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ወዳጄ፡- ትናንት ላይ ሆነው ነገን መኖር የቻሉ ታላላቅ ሊቃውንትና የእምነት መሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ ኢየሱስ፣ ሞሀመድና ቡድሃም በዚያው መስመር መሰለፋቸው ተፅፏል፡፡ ታላቁ ኒች እሱን የምንረዳበት ጊዜ ገና መሆኑን አስቀድሞ ጽፎልናል፡፡ “My time is not yet, only the day after tomorrow belongs to me” በማለት፡፡
የፈረንሳይ ንጉስ ሉዊ አስራ ስድስተኛ በአብዮቱ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ከሱ ዘመን ሩቅ የነበሩትን የቮልቴርና የሩሶን መፃፍት አንብቦ “እነዚያ ሁለት ሰዎች ናቸው ፈረንሳይን የገደሏት (Those two men have destroyed France) ብሎ ነበር፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡
***
ወደ ታሪካችን እንመለስ፡- የእማማ ታከለች ልጅና ባለቤቷ ከሃዘናቸው እንዳገገሙ ወደመጡበት ለመመለስ ተነሱ፡፡ ልጅቱ ለማስታወሻ የሚሆኗትን የቤተሰቦቿን ትሩፋት ስትሰበስብ፣ እናቷንም ሙዳይ ብድግ አደረገች:: ከፍታ በውስጡ ያሉትን ጨሌዎችና ሌሎች ነገሮች እያገላበጠች ሳለ ባለቤቷ በተመለከተው ነገር ክፉኛ ደነገጠ፡፡ ዓይኑ የተከከለበትን “ጌጥ” አንስቶ፡-
“ይኼ የማን ነው?” ሲል ጠየቃት
“ምነው?”
“ንገሪኝ”
ትዝ አላት፡፡ በልጅነቷ ከእናቷ ጋር ዶሮ ስትበልት… ከዶሮዋ ሆድ ውስጥ የተገኘችው “አርቲ” ነበረች፡፡
እናቷ እስከ ዛሬ በማስቀመጣቸው እየተገረመች ነገረችው፡፡ ጭንቅላቱን በሃዘኔታ ነቀነቀ፡፡
“ምን ሆንክ?”
“ምናልባት ከቱሪስቶች የወደቀ ሊሆን ይችላል”
“ምንድነው ነገሩ?”
ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ምርጥ ዲያመንድ (አልማዝ) መሆኑን ነገራት፡፡
ባለቤቷ የጄምስቶን ኤክስፐርት ነው፡፡
“What?”
“Yes!”
ግድግዳ ላይ ወደተሰቀለው የእናቷና ያባቷ ፎቶግራፍ ተመለከተች፡፡ ችግራቸው ሁሉ ፊቷ ላይ ተደቀነባት፡፡ ባለቤቷን እየጐተተች፣ አርቲዋን ተቀብላ በጓሯቸው በኩል በሚያልፈው ወንዝ ውስጥ ወረወረቻት፡፡
…ባለቤቷ ዕቅፍ አድርጐ ትከሻዋን አሻሻት፡፡
“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ!!”
ሠላም!!

Read 1394 times