Saturday, 30 November 2019 11:54

በኦሮሚያ በ3 ወራት ውስጥ 433 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሞተዋል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

    - ባለፈው ሳምንት በ3 ቀናት 66 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው አልፏል
                   - በክልሉ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ገጠማ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ይጀመራል
                       
          በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 3 ወራት በተከሰቱ 1095 የትራፊክ አደጋዎች 433 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ፤ ገልጿል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ እገጥማለሁ ብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት በመላው አገሪቱ 4597 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡  
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ ጥፋትና ውድመት እያደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል በተሽከርካሪዎች ላይ  የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ገጠማ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ለመከሰቱ በዋና ምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል  ከፍጥነት ገደብ በላይ ማሽከርከር፣ የአሽከርካሪዎች ስነምግባር ጉድለትና የመንገዶች ሁኔታ ለማሽከርከር አመቺ አለመሆን እንደሚገኙበትም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ገጠማው በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደሚጀመርና  በሂደትም ወደ ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንደሚቀጥል አክለው ገልፀዋል:: በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ የተጣለው የደህንነት ቀበቶ የማሰር ግዴታ በተሳፋሪዎችም ላይ እንደሚጣልባቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በክልሉ በሶስት ቀናት ብቻ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የስልሳ ስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ምህረት ሻንቆ፤ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን ጠቁመዋል፡፡ አደጋውን ለመቆጣጠርና እየጠፋ ያለውን የሰው ህይወትና የሚወድመውን ንብረት ለመታደግም በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ለመግጠም መገደዳቸውን ረዳት ፕሮፌሰር ምህረት ሻንቆ ገልፀዋል፡፡
የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ የትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ለመጡት የትራፊክ አደጋዎች  ክልሉ ብዙ የትራፊክ ፍሰት ያለበት መሆኑ፣ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስና የስነ ምግባር ጉድለት፣ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ የትራፊክ ፖሊሶች በአግባቡ ቁጥጥር አለማድረግ፣ ከመጠን በላይ መጫን፣ ሱስ አስያዥ ነገሮችን እየተጠቀሙ ማሽከርከር፣ የቁጥጥር ስርዓቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ራዳር አለመኖር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በክልሉ ዋና ዋና የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት አሽከርካሪዎች በሚፈጽሟቸው ስህተቶች መሆኑን የጠቆመው መረጃው፤ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግርና የመንገዶች ሁኔታም ለአደጋው መበራከት በመንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፉት 3 ወራት በአማራ ክልል በትራፊክ አደጋ183 ሰዎች ለሞት፣ 219 ሰዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸው ታውቋል፡፡ በክልሉ ከመስከረም ወር ወዲህ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቁመው የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት መረጃ፤ ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ 1109 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውንም ይገልፃል፡፡
በትግራይ ክልል የዘንድሮው ዓመት የትራፊክ አደጋን መጠን ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ባንችልም በ2011 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ 386 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውና ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ታውቋል፡፡
አለማቀፉ የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የሞት መንስኤ ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል፣ የትራፊክ አደጋ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን፤ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃም በኢትዮጵያ ዓምና 4597 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እንዳጡ ገልጿል፡፡ 13400 ሰዎች ደግሞ ለከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል:: የትራንስፖርት ሚኒስቴር “እንደርሳለን” በሚል መሪ ቃል በትራፊክ አደጋዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን እያካሄደ ሲሆን፤ የዚሁ ፕሮግራም አካል የሆነ የእግር ጉዞ በነገው እለት ይደረጋል፡፡       

Read 1603 times