Print this page
Saturday, 30 November 2019 11:57

ኦነግ የመልካም ግንኙነት ጥሪ ለፖለቲካ ሃይሎች አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)


           ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስጊ ሆኗል ያለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ይህን አስጊ ሁኔታ ለመቀልበስ የፖለቲካ ሃይሎች መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እንዲቀራረቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡  በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ቤተ እምነቶችን በመጠቀም የፖለቲካ ችግሩን ወደ ህዝብ ግጭት ለመቀየር ጥረት እየተደረገ ነው ያለው ኦነግ የዚህም ዋንጭ ኢትዮጵያ የተመሠረተችበት የተለያዩ አመለካከቶችን አጣምሮ ማስተናገድ የማይችል ፀረ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ባህል ነው ብሏል፡፡
ውስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ተሳትፎ ካልሆነ በቀር ዘላቂ መፍትሔ እንደማያገኝ ያስገነዘበው ኦነግ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሃይሎች መካከል የሚታዩ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ በተለመደው መልኩ አንዱ ወገን ሌላውን በኃይል ደፍጥጦና አፍኖ እልባት ያገኛል ብሎ ማሰብ ከከንቱ ህልምና ምኞት የሚያልፍ አይደለም ብሏል፡፡
በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ችግሩን በተመለከተ ቁጭ ብለው መነጋገርና መወያየት ሲችሉ መሆኑን ያስገነዘበው ኦነግ  በሀገሪቱ ታሪኮች፣ ዛሬ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ መስማማት መፍጠር የሚቻለው ተቀራርቦ በመወያየት ነው ብሏል፡፡
ለዚህም ኦነግ በራሱ ተነሳሽነት የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት ማቀዱንና ይህን ሃሳብ የሚደግፉ አካላት ከሱ ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች እንዳሉ ሆኖ የተለያየ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎችም በመልካም ግንኙነትና በመደማመጥ ለሀገርና ለህዝቦች ሰላም ሲባል መወያየትና በሚቻላቸው ላይ በመተጋገዝ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ኦነግ በዚህ መግለጫው አስገንዝቧል፡፡


Read 1626 times