Print this page
Saturday, 30 November 2019 12:01

የብልጽግና ፓርቲ የ10 አመት የብልጽግና እቅድ መንደፉን አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

  የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም ይዘናል” - ጠ/ሚሩ

             የብልጽግና ፓርቲ ለሚቀጥሉት 10 አመታት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጐዳና የሚወስድ እቅድ መንደፉንና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም መያዙን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የፓርቲውን መዋሃድ አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፓርቲው ህግን ተከትሎ የተመሠረተ መሆኑንና ኢትዮጵያ ከ10 አመት በኋላ የት ትድረስ የሚለውን የብልጽግና ትልም አስቀምጦ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ፓርቲ ህብረ ብሔራዊነትን፣ ፌደራላዊነትንና የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ጉዞ የሚያጠናክር መሆኑን ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ የቄሮ፣ ፋኖ ዘርማና የሌሎች ወጣቶችን ትግል ተሸክሞ ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተመሠረተ ፓርቲ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ፓርቲው በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር ቁርጠኛ አቋም መያዙን ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከእንግዲህ በሃሳብ የበላይነት እንጂ በጉልበትና ሃይል ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትን መንግስት እንደማይታገስም ተናግረዋል::
“አንዳንድ ሃይሎች  አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አሃዳዊ ስርአትን የሚያመጣ የፌደራል ስርአትን የሚያጠፋ ነው የሚል አሉባልታ ሲናገሩ ይደመጣል፤ ይሁንና በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥነው የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊት፣ ፌደራላዊት፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚያጠናክርና የሚገነባ እንጂ የማያፈርስ መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን በፕሮግራማችን ጭምር ማካተታችንን እየገለጽኩ፤ ሌሎች ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ ሃሳብ በማምጣት እንዲሞግቱንና ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ሃሳብ ይዘው እንዲቀርቡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን ላቀርብላቸው እፈልጋለሁ” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ 4 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በፈጀው የምስል ድምጽ የፌስቡክ መልዕክታቸው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ በመሠረቱ በኦሮሚያ ክልል የቄሮን ትግል፣ በአማራ ክልል የፋኖን ትግል በደቡብ ዞርማና ሌሎች የወጣት አደረጃጀቶች በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልጽግናና ሠላም ዲሞክራሲያዊና አንድነት ለማሸጋገር የተደረገ ሂደት መሆኑ ታምኖ ቄሮዎች ፋኖዎች እንኳን ደስ ያላችሁ የታገላችሁበት ፓርቲያችሁ ተመስርቷል፤ ከፓርቲያችሁ ጋር ሆናችሁ ስታነሱ የነበረውን ጥያቄ ወደ ተግባር እንዲመለስ አስፈላጊውን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ድርጅታችን የፋኖንና የቄሮን ትግል የሚያስታውስ የተግባር ማስታወሻ እንደሚያስቀምጥ ሳበስርላችሁ በታላቅ ደስታ ነው ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ አባላት ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ ልዕልናን የማረጋገጥና ህግ የማስከበር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ሃሳብ ካለው፣ በሃሳብ ገበያ ውስጥ አሳምኖ ስልጣን ከመያዝ ውጪ በሃይልና ትክክል ባልሆነ መንገድ የህዝብን ሠላም የሚያውክ ከሆነ፣ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ ልዕልናን እንደሚያረጋግጥና ለህግ ልዕልና አበክሮ እንደሚሠራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ያለብንን ድህነት፣ ያለብንን የዲሞክራሲ እጥረት፣ ያለብንን የሠላም ችግር በመፍታት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስራ እንዲያገኝ፣ በልቶ እንዲያድር በሠላም ወጥቶ እንዲገባ የሚተጋ ፓርቲ ሲሆን፤ ይሄንንም በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ ያሠፈርን መሆናችንን አውቃችሁ ሌሎች ከኛ የሚቃረኑ ሃይሎች ካሉ አማራጭ ሃሳብ እያቀረቡ በሃሳብ ልዕልና ብቻ ማሸነፍ የሚችሉበትና ሠላማዊ መንገድ የሚከተሉበትን መንገድ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በመሆን እንዲያረጋግጥ ጥሪዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡


Read 5063 times