Saturday, 30 November 2019 12:10

“ሊሴ ገ/ማርያም ት/ቤት የቀደመ ባህሉን እየተከተለ አይደለም”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግሥት ስምምነትና ይሁንታ በ1958 ዓ.ም ነበር ሊሴ ገብረ ማሪያም ትምህርት ቤት የተቋቋመው፡፡ የአሁኗን ርዕሰ ብሔር ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በርካታ ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ከዚሁ ት/ቤት ወጥተዋል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ት/ቤቱ፤ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያና የፈረንሳይ መንግሥት፣ በድጋሚ ስምምነት አድርገው ሥራውን ቀጥሏል፡፡ በዚሁ ት/ቤት ተምረው ያለፉና ልጆቻቸውን እዚሁ ት/ቤት የሚያስተምሩትን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገራት ዜጎች በዚሁ ት/ቤት ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በት/ቤቱ ግልጽነት የጎደላቸው በርካታ አሰራሮች እንዳሉ ወላጆች ይናገራሉ፡፡ ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ወላጆች ከወላጅ ኮሚቴው ጋር በቸርችል ሆቴል ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በት/ቤቱ አስተዳደር ላይ ያሏቸውን ቅሬታዎች አንስተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በት/ቤቱ አሉ በተባሉ ችግሮች ዙሪያ ከወላጅ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ግሩም አበበ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች።


          አሁን ት/ቤቱ ያለበት አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ት/ቤቱ በበጎ መልኩ ብዙ ለውጦች አሉት:: አለም ሲዘምን እየዘመነ መምጣቱ የሚካድ አይደለም፡፡ በፈረንሳይ መንግሥትና በፈረንሳይ ሥርዓተ ትምህርት የሚተዳደር ነው፡፡ ቦታው በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም ሲቋቋም ደጃዝማች ገ/ማሪያም አሁን ት/ቤቱ ያለበትን ሰፊ ቦታ ሰጥተው ነው:: እንደገናም እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም የአሁኑ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ፣ ስምምነቱ ተሻሽሎ የሊዙም ሁኔታ ታይቶ ተፈርሟል፡፡ ሆኖም በዚህ አዲስ ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በቸልተኝነት ይሁን በስራ ብዛት ጫና ባናውቅም፣ ብዙውን መብት አሳልፎ ለፈረንሳይ መንግሥት ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌ ይሄ ት/ቤት የሚተዳደርበት ቦርድ በአዲስ መልክ ቢቋቋምም፣ ጥርስ ያለው ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቦርዱ ስብሰባ ሲያካሂድ፣ የኢትዮጵያ ተወካይ አልተገኘም ነበር። ባለፈው ዓመት እኛም “የኢትዮጵያ ተወካይ ስብሰባው ላይ ካልተገኘ አንሳተፍም” የሚል አቋም ይዘን ነበር፡፡ በዚህ መሰረት የፈረንሳይ ኤምባሲ የባህል አታሼ ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ከዚያ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በሃላፊነት ላይ የሚገኙት አቶ ዘላለም ሙላቱ፣ የዚህ ትምህርት ቤት የቦርድ አባል መሆናቸውን በደብዳቤ አሳወቀ፡፡
ከዚያ በኋላስ አቶ ዘላለም መሳተፍ ጀመሩ?
በጣም የሚያስገርመው ይሄ ነው፡፡ ት/ቤቱ ባለፈው ጊዜ አንድ ውሳኔ ለማሳለፍ ሲሰበሰብ  አልተሳተፉም፡፡ ለኢትዮጵያ መንግሥት “ት/ቤቱ ለስብሰባ ጋብዟችኋል ወይ?” ብለን ስንጠይቅ፣ “ምንም የስብሰባ ግብዣ አልደረሰኝም” አለ:: ነገር ግን የወላጅ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ባልተሳተፈበት ሁኔታ ተሰብስበው ውሳኔ አሳለፉ፡፡ የያዙት ቃለ ጉባኤ አቶ ዘላለም ሙላቱ ይልና ‹‹ኤክስኪዮድ አብሰንስ›› ይላል:: ሳይጋበዙ እንዴት ነው የሚገኙት? በእንዲህ አይነት ሥርዓት የጎደለው ማናለብኝነት በት/ቤቱ ይታያል፡፡ ለእኛ አገር ሕግ የመገዛቱን ነገር ችላ እያሉት ነው፡፡ እኛም ይሄ የማንቂያ ደወል ስለሆነ፣ ከሳምንታት በፊት ከኤምባሲው የባህል አታሼ ጋር ስብሰባ አድርገን፣ “ሕግና ሥርዓት ይከበር፣ ግልፀኝነትና የኦዲት ሪፖርት ይቅረብ” የሚሉ ጥያቄዎች አንስተናል፡፡ አሁን ችግሩ ምንድን ነው ካልሺኝ፣ የፈረንሳይ መንግሥት የዚህን ት/ቤት መምህራን ከእነደሞዛቸውና ጥቅማ ጥቅማቸው ይመድብና ለመምህራኑ ከሚሰጠው 53 በመቶውን መልሶ ይወስደዋል፡፡ ት/ቤቱ የሚመራው ግን በ‹‹MLF›› ነው፡፡
“MLF” ማነው? ሥራው ምንድን ነው?
‹‹ሚሲዮን ላይክ ፍሮንሴዝ›› ይባላል በዓለም ላይ የሚገኙ ከ200 በላይ የፈረንሳይ ት/ቤቶችን የሚያስተዳድር የፈረንሳይ ሚሽን ነው:: ባለፈው ዓመት “MLF” ዳይሬክተሩና እኛ ሁለት ጊዜ ተሰብስበን፣ በግልጸኝነትና ታማኝነት ላይ የተነጋገርን ሲሆን ት/ቤቱ የበጀቱን ዝርዝር እንዲሰጠን ጠይቀን ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ “እኛን ብቻ እመኑን፣ በጀቱን ምንም አናደርገውም” ይላሉ፡፡ አሁን ባለንበት 21ኛው ክ/ዘመን ላይ እንደዚህ የሚባል ነገር ደግሞ የለም፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 የኢትዮጵያና የፈረንሳይ መንግሥት በአዲስ መልክ ያደረጉት ስምምነት አብዛኛውን መብት ለፈረንሳይ የሰጠ ነው ወዳሉኝ ሀሳብ እንመለስና… እስቲ ተላልፈው የተሰጡትን መብቶች ይንገሩኝ…
አንዱና ዋነኛው ስምምነት፤ በሁለቱ መንግሥታት መካከል በአካዳሚክ፣ በአስተዳደርና በፕሮጀክቶች ጉዳይ ላይ የሚወስን ቦርድ ያቋቁማል ይላል፡፡ ይሄ ቦርድ በፈረንሳይ ኤምባሲ የባህል አታሼ ነው የሚመራው፡፡ ፕሮቪዘሩ የቦርዱ ፀሐፊ ነው፣ ሶስት ወላጆች ማለትም አንድ የኢትዮጵያ ወላጆችን የሚወክል፣ ሁለተኛው የፈረንሳይ ወላጆችን የሚወክል፣ ሦስተኛው የሌሎች ዜጎች ወላጆችን የሚወክል ሲሆን፤ አንድ የተማሪ፣ አንድ ደግሞ የአስተማሪ ወኪሎች፤ በአጠቃላይ 8 አባላት ያሉት ቦርድ ነው የተቋቋመው፡፡ ነገር ግን በስምምነቱ ላይ ምን ይላል… “የገንዘብ ጭማሪም ላይ ወላጆችና ት/ቤቱ መስማማት ካልቻሉ የሚወስነው ‹‹ MLF›› ነው” ይላል፡፡ ተመልከቺ! እነሱ በወላጅ ላይ የፈለጉትን ያህል ጭነው፣ እኛ አንችልም ብንልና ባንስማማ፣ የእነሱ ሚሲዮን የፈለገውን ውሳኔ የማሳለፍ መብት ተሰጥቶታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ “ይሄ ት/ቤት እንደ ቀድሞው የሕዝብ ት/ቤት ነው” ይላል፡፡ ፈረንሳዮቹ ቅር የሚላቸው “መንግሥት ይህን መሬት ሰጥቷችሁ እንዴት የሕዝብ ት/ቤት ነው ትላላችሁ” ብለው ነው:: ምክንያቱም በቀደመው ጊዜ ት/ቤቱ ሲቋቋም ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት 100 ሺህ ብር ድጎማ ያደርግ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያ ነገር ቀርቷል። ነገር ግን መሬቱ ከሊዝ ነፃ ሆኖ ሕንጻዎቹ ሁሉ ነፃ ሆነው፣ መምህራኑም ምንም አይነት ቀረጥ ሳይከፍሉ ነው የሚያስተምሩት፡፡ የተጣለባቸው ምንም ቀረጥ የለም ማለት ነው:: ት/ቤቱ ከውጭ ፈርኒቸርና ሌሎች እቃዎች ሲያስገባ፣ ከቀረጥ ነፃ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ብዬ እንዳልኩት፣ በሥራ ጫና ይሁን በሌላ፣ ትንሽ ለትርጉም አሻሚ የሆነ ስምምነት ነው ያደረገው:: አሁን አምስት ዓመቱ እያለቀ ነው፡፡ በየአምስት አመቱ ስምምነቱ ይታደሳል፡፡ ነገር ግን ተቃውሞ ከሌለና ጥያቄ ካልመጣ በዚያው ሊቀጥል እንደሚችል ይገልፃል:: ሌላው በት/ቤቱ ካሉት 1850 ተማሪዎች 1200 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ 15 በመቶው ፈረንሳዊያን ሲሆኑ ሌሎች ዜጎች 5 በመቶ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች 80 በመቶ ሆኖ ሳለ ሶስቱም እኩል አንድ አንድ ውክልና ይዘው ቦርድ ላይ መቀመጣቸው ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ስምምነት በሰከነ መልኩ እንደገና ቢያየውና ቢገመግመው የሚል ሀሳብ አለን፡፡ እኛ አገር ያለው የዚህ ት/ቤት አስተዳደር ሌላው ዓለም ካሉት የፈረንሳይ ት/ቤቶች አስተዳደር የተለየ ነው፡፡ በሌላው አለም ወላጆችና “MLF” በጋራ የሚመሩበት አሰራር ነው ያለው - ‹‹ጄሲዩ ዲሬክት›› ይባላል፡፡ እዚህ ይህ የለም፡፡ ለዚህ ነው ጥልቅ ግምገማና መሻሻል ያሻዋል የምንለው፡፡
የክፍያ ጭማሪን በተመለከተም ወላጆች ጥያቄ ያነሳሉ…
ጭማሪን በተመለከተ የዛሬ አምስት ዓመት በ2012 ‹‹ት/ቤቱ ሊፈርስ ነው፣ እንዴት ይሁን›› ተብሎ 200 ፐርሰንት ነው ጭማሪ የተደረገው፡፡
200 ፐርሰንት ሲጨመር አጠቃላይ ክፍያው ስንት ይሆናል ማለት ነው?
ይለያያል፡፡ ለምሳሌ 30 እና 40 ሺህ ብር በአመት ይከፍል የነበረ ሰው፣ ወደ 60 እና 70 ሺህ ብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የዱሮውን አላውቀውም፡፡ በግሌ ለምሳሌ በመጀመሪያው ሴሚስተር 51 እና 55 ሺህ ብር እከፍላለሁ፡፡ ሁለተኛው ሴሚስተርም ላይ እንዲሁ እከፍልና ባለፈው ዓመት በዓመት 80ሺህ ከከፈልኩ በአሁኑ ዓመት 95 ሺህ ብር እከፍላለሁ ማለት ነው፡፡ ገንዘቡ አይደለም የሚቆጭሽ፤ የከፈልሽው ገንዘብ ግልጽነት በጎደለው መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ደስ አይልም፡፡ በፊት ግልጽ የሆነ በጀት ለወላጅ ኮሚቴ ይሰጡን ነበር፡፡ ከ2014 ዓ.ም ወዲህ ግን ቀርቷል፡፡
ለምን ቀረ ብላችሁ አልጠየቃችሁም?
“አስፈላጊ አይደለም፤ ለወላጅ ኮሚቴ የበጀት ዝርዝር ምን ያደርግላችኋል” አሉ፡፡ ሚስተር ጂን ክርስቶፍ ዱቤር የሚባለው የMLF ዳይሬክተር መጥቶ ‹‹እንዲህ አይነት የበጀት ዝርዝር ከወላጆች ጋር እያጋጨንና አደጋ እያመጣ ስለሆነ መቅረት አለበት›› አለን:: ለምሳሌ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአስተማሪዎች ብዙ የደሞዝ ጭማሪ እንደተደረገ ነግረውናል፤ ይሁን ይጨመር፡፡ ግን ማን ተቀጥሮ ነው? ለምን ተጨመረ? ጭማሪው በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ምን እሴት ጨመረ? የሚለውና መሰል ነገሮች ምላሽ ማግኘት አለባቸው:: ሌላው ያልነገርኩሽ… እኛ ከባለፈው አስተዳደር ጋር መወያየት የጀመርንበት አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ የ5 ዓመቱ ስትራቴጂክ ፕላን ስላለቀ አዲስ መቀረፅ     አለበት ብለን ተወያየን:: ጥሩ ይቀረፅ ግን የባለፈው ይገምገምና ጥሩ ተመክሮዎችን ወስደን ክፍተቶቹን ሞልተን፣ አዲስ ለመቅረጽ ግብአት ይሆነናል ተባለ:: እናም ስጡን አልናቸው፡፡ ምላሽ ሳይሰጡ አንድ አመት አለፈ፡፡ ለአምባሳደሩ ስናመለክትና ጉዳዩን እንደማንተወው ሲያውቁ ‹‹እንዲያውም እንደዚህ አይነት ዶክሜንት ኖሮ አያውቅም” ብለው ቁጭ አሉ፡፡ ታዲያ በምን ደንብ ነው ስንመራ የነበረው? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰልንም፡፡ ነገር ግን ምላሽ እንፈልጋለን:: በሌላ በኩል፤ ት/ቤቱ ውስጥ በ300 ሺህ ዩሮ ጂምናዚየም ይሰራል ተብሎ በጀት ተይዞለት እንደነበር አርካይቭ ውስጥ ሰነድ አግኝተናል:: ሆኖም እስካሁን 1.2 ሚ.ዩሮ ፈጅቶም እንኳን ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ስንጠይቃቸው ገንዘቡ የመግዛት አቅሙ ቀነሰ (ዲቫሉየት አደረገ) ምናምን ይላሉ፡፡ ነገር ግን በጣም ግልጸኝነት የጎደለው አካሄድ ነው የሚሄዱት፡፡ የሚገርምሽ… ይሄ ት/ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በውጭ ኦዲተር ኦዲት ተደርጎ አያውቅም፡፡
ወላጆች ለመጽሐፍ በዶላር ክፈሉ መባሉን መቃወማቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ ምን አይነት መጽሐፍ ነው? ስንት ዶላር ነው የምትጠይቁት?
መጽሐፍቱ ለልጆቻችን እውቀት መዳበር ከፈረንሳይ አገር የሚገዙ ናቸው። በዶላር እርግጠኛ አይደለሁም ግን በኢትዮጵያ ገንዘብ ከ3ሺ-4 ሺህ ብር አንድ ሰው ይከፍላል፡፡ ይሄንን በዶላር የምንከፍለው እንዴት ነው? ከብላክ ማርኬት ገዝተን ነው ወይስ ከየት ነው የምናመጣው? ይሄ ወንጀልም ነው በማለት አብዛኛው ወላጅ አልከፈለም፡፡ ነገር ግን የከፈሉም እንዳሉ ሠምተናል፡፡ ዶላሩን ከየት አምጥተውት እንደሆነ አናውቅም፡፡ ይሄ ራሱ ሕገ ወጥነት ነው፡፡
የወላጅ ኮሚቴው ፈረንሳይ አገር በሚገኘው ትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር እንጂ እዚህ አገር እውቅና ያለው አይደለም፡፡ በዚህ አገር እውቅና ለማግኘት የሚገድባችሁ ነገር አለ?
እርግጥ ነው የወላጅ ኮሚቴው እዚህ ቢመሰረትም የፈረንሳይ ትምህርት ቤት በመሆኑ እውቅና ለማግኘት ፈረንሳይ አገር በሚገኝ ‹‹ፐርፌክቹር›› በተሰኘ ማለትም በትምህርት ሚኒስቴር መመዝገብ አለበት፡፡ የዓለም የሊሴ ትምህርት ቤቶች የወላጆች ኮሚቴ ማህበር አባልም ነን፡፡ በየአመቱም 200 ዩሮ የአባልነት መዋጮ እንከፍላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ለመመዝገብ አንዳንድ ሂደቶች ላይ ነን፤ የሚያግደን ነገር ያለ አይመስለንም፡፡
ት/ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ ቢሮን እንደቀማችሁ ገልጻችኋል፡፡ በምን ምክንያት ነው የቀማችሁ?
ት/ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ የመብት ተከራካሪ እንዲኖር የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ወላጆች ተደራጅተው ጥያቄ ሲጠይቁ፣ ከእነሱ መብት በተቃራኒ የቆሙ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን እኛ ይህን ሁሉ የምናደርገው ለልጆቻችን ደህንነት ነው፡፡ ት/ቤቱ መዋያ ቤታቸው በመሆኑ ያለውን እንቅስቃሴ ማወቅና መገምገም አለብን፡፡ እነሱ ፋይናንሱን ባልና ሚስት ሆነው እየመሩ፣ ገንዘቡ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እየባከነ፣ ልጆቻችን ደርሰው የሚመለሱበት (ብቻ) ት/ቤት እንዲሆን አንፈልግም፡፡ የሰራተኛ ቅጥር ላይ እንኳን ግልጽነት የለም፡፡ ብዙ ፀሐፊዎች ፈረንሳዮች ናቸው፡፡ ፈረንሳይኛን አቀላጥፈው የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል፤ ለምን አይቀጠሩም? ኢትዮጵያዊያን ሊይዙት የሚገባውን ቦታ በሙሉ እነሱ ናቸው የያዙት፡፡ ይሄም ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ የፈረንሳይ ኤምባሲ የሰራተኛ ቅጥርን በተመለከተ “ማስታወቂያ በጓሮ አትለጥፉ፤ ግልጽ በሆነ መንገድ አወዳድራችሁ ቅጠሩ” ብሏቸዋል፡፡
ወደ ቢሮ ሁኔታ ስንመለስ በዚህ ዓመት ለስራ ስንገባ ዘግተውታል፡፡ ያለ ምንም ቅድመ እውቅናና ደብዳቤ ንብረታችንን አውጥተው የሆነ ስቶር ውስጥ በመክተት ክፍሉን ወስደነዋል አሉን፡፡ ተመልከቺ፤ ቢሮው ውስጥ የ40 ዓመት ዶክመንት ክምችት ነው የነበረው:: ያንን ሁሉ አርካይቭ ስቶር ውስጥ ቆልፈው “ኑና ውሰዱ” አሉን፡፡ በመኪና ጭነን ወዴት ነው የምንወስደው? እኔን የሚያሳዝነኝ ነገር፣ በት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ አራትና አምስት ቤተሰብ ሙሉ አፓርታማ ይዞ ይኖራል፡፡ ለእኛ ግን አንድ ክፍል ቢሯችንን ቀሙን፡፡
በስብሰባችሁ ላይ ዶ/ር ሚካኤል የተባሉ ወላጅ ሲናገሩ፣ እናንተ በዚህ ት/ቤት ትማሩ በነበረበት ዘመን የገጠሩም የከተማውም፣ የሀብታሙም የደሃውም፣ የመንግሥት ሰራተኛውም የነጋዴውም ልጅ ሁሉ የሚማርበት ት/ቤት ነበር፡፡ አሁን ያ ባህል ጠፍቶ፣ የሀብታም ልጅ የሚማርበት ብቻ ሆኗል፤ የቀድሞ ባህሉን መመለስ አለብን ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ ምን ማለት ነው መሰለሽ… ማንኛውም ተቋም የተቋቋመበት አላማ ይኖረዋል። አላማውን ተከትሎ መስራት እንጂ ከአላማው መውጣት የለበትም፡፡ እኛ ማንኛውንም አግባብ ያልሆነ ነገር ከመቃወም ወደ ኋላ አንልም:: ለምሳሌ አንድ ሰው ልጁን ሊያስመዘግብ ሲመጣ እንዴት የባንክ ስቴትመንት ይጠየቃል? የድርጅት ስቴትመንትና የግል ሀብት እንዴት ይጠየቃል? ይሄኮ የግል ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ይበልጥ የምበሳጨው ት/ቤቱ በመጠየቁ ሳይሆን ስቴትመንታቸውን በሚሰጡት ወላጆች ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያለው ሰው የባንክ ስቴትመንት ያቀርብላቸዋል፡፡ ይሄ መብትና ግዴታን ያለማወቅ ይመስለኛል፡፡ እነሱም ይህን መብቱን የማያውቅ ወላጅ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው እንደፈለጉ የሚሆኑት፡፡ እኔ ወደ ውጭ ስሄድ ለኤምባሲ ስቴትመንት ሳቀርብ እንኳን እበሳጫለሁ::
ወደ ጥያቄሽ ልመለስ፡፡ በ2012ቱ ስምምነት ላይ ሀበሻ ወላጆች ከሚከፍሉት ገንዘብ 10 በመቶው ለችግረኛ ወገኖች ነፃ የትምህርት እድል አገልግሎት ይውላል ይላል። ለምሳሌ እኛ ሀበሻ ወላጆች በዓመት ከ100 ሚ. ብር በላይ እንከፍላለን:: ከዚህ ውስጥ 10 ሚ. ብሩ በቀጥታ ስኮላርሽፕ ለሚፈልጉ ልጆች መዋል አለበት ማለት ነው፡፡ ‹‹በየዓመቱ የሚጨመርብኝን ሁሉ እከፍላለሁ›› የሚል ቅድመ ሁኔታ ሁሉ ያስፈርሙሻል፡፡ ይሄን እንደፈለጉ እንዲያደርጉ ክፍተቱን የፈጠረላቸው የስምምነቱ መላላት ይመስለኛል፡፡ ስምምነቱ እንደገና መገምገም አለበት ያልኩሽም ለዚህ ነው:: ግልጽነት ይጎድላቸዋል። ለምሳሌ ሊሴ የፈረንሳይ ት/ቤት ስለሆነ በፈረንሳይ ስታንዳርድ ሕንጻው መሰራት አለበት ብለው አማካሪ ከሊባኖስ አስመጡ:: ሰውየው በየወሩ ከሊባኖስ እየበረረ እየመጣ ነው የጂምናዚየሙን ግንባታ የሚያማክረው:: ለመሆኑ ይሄ አማካሪና ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የመስራት ፈቃድ አለው ወይ? የሚለው ጥያቄያችን ነው፡፡ አሁን እኛ ይሄንን ስንናገር፤ የኢትዮጵያ መንግስትና የፈረንሳይ መንግስትን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል ይሉናል፡፡ እኛ የፈረንሳይን መንግስት እየከሰስን አይደለም:: በዚህ ት/ቤት ያሉ ግለሰቦች ብልሹ አሰራር፣ የፈረንሳይን መንግስት ይወክላል ብለንም አናምንም፡፡ ዞሮ ዞሮ ት/ቤቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ ነው፡፡ እኛ ይህን ሁሉ እንከፍላለን፤ እንደዚያም ሆኖ አይበቃም ይላሉ፡፡ ግዴለም እንጨምር ግን እንዴት እንደምታወጡትና ጥቅም ላይ እንደምታውሉት አሳዩን ነው የምንለው፡፡ የእኛን የባንክ ስቴትመንት እነሱ ከጠየቁ፣ እኛ ገንዘባችን ምን ላይ እንደሚውል፣ ምን እሴት እንደጨመረ የማወቅ መብት የለንም እንዴ? በዚያ ላይ በውጭ ኦዲተር ለምን ኦዲት አይደረጉም? ይሄ ሁሉ ጥያቄያችን እንዲመለስ እንጠይቃለን፡፡


Read 4496 times