Saturday, 30 November 2019 12:22

“ዲ`ፋክቶ መንግስት” - የህወሓት ህልም?

Written by  ኩርኩራ ዋፎ - ከለገጣፎ
Rate this item
(2 votes)

  ለዓመታት ሲነገረን የነበረው “የኢህአዴግ ውህደት” ዘንድሮ ቁርጥ ሆኗል፡፡ ነገሩ የምር መሆኑ እየገፋ ሲመጣ ደግሞ የኢህአዴግ የውስጥ ትግል ድርጅቱን ማዋሃድ ብቻ ሳይሆን እንዲፍረከረክም እያደረገው መሆኑ ተስተውሏል፡፡ በውህደቱ ዙሪያ ሰሞኑን ከሰማናቸው ጆሮ ጠገብ ወሬዎች ውስጥ የህወሓት (ትህነግ) ማፈንገጥ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከኢህአዴግ መስራቾች አንዷና ዋነኛዋ የሆነቺው ህወሓት፣ ከማንገራገር በዘለለ ማፈግፈግ መጀመሯና “ዲ’ፋክቶ መንግስት አቋቁማለሁ” ማለቷ ግርምትን ብቻ ሳይሆን በአንዳንዶች ዘንድ ከመርግ የከበደ፣ ከመርዶ ያልተናነሰ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡ እናም በዚች መጣጥፍ ትኩረት የማደርገው የህወሓትን “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የመመስረት “ምኞት” በሚመለከት ይሆናል፡፡
ህወሓት ውህደቱን የፈራቺበት ምክንያት ቀደም ሲል ለእርሷ እንዲመች ተደርጎ የተዋቀረው ኢህአዴግ ፈርሶ ሁሉም ባለው ቁመና ልክ እንደሚወከል ስለምታውቅ ነው:: ቀደም ሲል ኢህአዴግ በነበረው ድርጅታዊ አወካከል አራቱም ድርጅቶች እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ፣ 5 ሚሊዮን ህዝብ የምታስተዳድረውን ህወሓትንና 40 ሚሊዮን ገደማ የሚያስተዳድረውን ኦህዴድን እኩል የሚያደርግ የተዛባ አወካከል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በአዲሱ ውህድ ፓርቲ እንደማይቀጥል ሲገባት ህወሓት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጀመረች፡፡ አንዴ “ውህዱ ፓርቲ ፌዴራል ስርዓቱን አፍርሶ አሓዳዊ የመንግስት ስርዓትን ለማምጣት ነው” የሚል ወከባ ትፈጥራለች፡፡ በዚህ ወከባ “አጋር” ይባሉ የነበሩትን ፓርቲዎች ለማምታታት ብትሞክርም ለ29 ዓመታት ከሀገሪቱ ፖለቲካ የተገለሉት አጋሮች ግን “አንሰማሽም” የሚል ምላሽ በመስጠት፣ የአዲሱ ውሁድ ፓርቲ አባልነታቸውን በየፓርቲያቸው ጉባዔ አካሂደው በመወሰን በአቋማቸው ጸኑ:: ቀጥላ “ሀገር ማዳን” በሚል ሰበብ መሰሎቿን ሰብስባ “የፌዴሬሽን ኃይሎች” የሚል ጎራ ለመፍጠር ብዙ ጥረት አደረገች፡፡ ይሄም ብዙ ርቀት ሊያስኬዳት እንዳልቻለ ስትገነዘብ፣ 40 ገጽ ያለው ጽሁፍ አዘጋጀችና “ዲ’ፋክቶ መንግስት አቋቁማለሁ” የሚል እንቅስቃሴ ጀመረች ሲባል ሰማን፡፡
እዚህ ላይ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ዲ’ፋክቶ መንግስት የሚቋቋመው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ትርጉም በተመለከተ ዊኪፔዲያ እንዲህ ይላል፡- “በህገ መንግስት ላይ ከተቀመጠው ድንጋጌ ውጪ በመፈንቅለ መንግስት፣ በአብዮት፣ በወረራ፣ አሊያም ህገ መንግስትን በመሰረዝና በማገድ ስልጣን መያዝ ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በሌላ ሰነድ ላይ ደግሞ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት በሕግ ዕውቅና ሳያገኙ ሕግን፣ መንግስታዊ ተግባራትንና በህግ የተቋቋሙ የመንግስት ተቋማትን በተጨባጭ ሥራ ላይ የማዋል ተግባርን ይገልፃል” የሚል ትርጉም እናገኛለን፡፡ ተመሳሳይነት ቢኖረውም አንድ ተጨማሪ ብያኔ ልጨምር፡፡ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት የአንድ ሀገርና መንግስት የሉዓላዊነት መገለጫ የሆኑትን ሁሉንም ስልጣኖች በሕጋዊ መንገድ ከያዙ አካላት ላይ በመንጠቅ ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝና  ህጋዊ መንግስት የሚሰራውን ስራ መስራት ማለት ነው” የሚልም ትርጉም በተለያዩ ሰነዶች ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
“ዲ’ፋክቶ መንግስት” የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ይህ ከሆነ፤ ከትርጉሙ ቀጥሎ አንዳንድ “ዲ’ፋክቶ መንግስት” ያቋቋሙ ሀገሮችን ታሪክ እንይ፡፡ በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ውስጥ የነበሩ እንደ አብኻዚያ (ጆርጂያ) ወይም እንደ ዶኔስክ ህዝባዊ ሪፑብሊክ (ዩክሬን) ያሉ ግዛቶች ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ በኋላ የማንንም ይሁንታ ሳይጠብቁ በዓለም ስርዓት ውስጥ ሀገር መስርተው፣  “ዲ’ፋክቶ መንግስት” አቋቁመው መኖር መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሀገራት ቀድሞም በጉልበት ወደ ሶቭየት ህብረት የተጨፈለቁ ስለነበሩ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ መመለሳቸውና ቀድሞ የነበራቸውን ዳር ድንበር ይዘው መንግስት መመስረታቸው በአግራሞት የሚታይ አልነበረም፡፡
በሌላ በኩል፤ እንደ ሰሜናዊ ቆጵሮስ ያሉ አንዳንድ ግዛቶች ዓለም እውቅና ሳይሰጣቸው “ዲ’ፋክቶ መንግስት” መስርተው ለረጅም ጊዜ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የስሪላንካዋ የታሚል ኢከላም ግዛት ከእናት ሀገሯ ተገንጥላ እውቅና ሳታገኝ በአንድ ወቅት “ዲ’ፋክቶ መንግስት” መስርታ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የስሪላንካ መንግስት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ዲ’ፋክቶ መንግስቱ ፈርሶ ወደ እናት ሀገሯ እንድትቀላቀል ተደርጓል፡፡ በኢንዶኔዥያ እንደ አቼ ያሉ “ዲ’ፋክቶ መንግስት” መስርተው የነበሩ ግዛቶች በሀገሪቱ ሰላም ሲሰፍን ወደ ነባር ክፍለ ሀገር ደረጃቸው ተመልሰዋል፡፡ እንደ ኤርትራ ያሉ ጥቂቶች ደግሞ የትጥቅ ትግል በማድረግ ነፃ መሬት በመያዝ “ዲ’ፋክቶ አስተዳደር” ከመሰረቱ በኋላ ተሳክቶላቸው ከእናት ሀገራቸው ተገንጥለው እውቅና ያለው ሀገር ለመሆን በቅተዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ምንን ያሳያሉ? አራት ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኸውም፡- አንደኛ፤ “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የመሰረቱ ገንጣይ ኃይሎች ከሌሎች “ቲፎዞ” ሀገሮች ወታደራዊ ድጋፍ ማግኘታቸው፣ ሁለተኛ፤ መገንጠልን የሚያቀነቅኑ አማጽያን በያዙት ነፃ መሬት አስተዳደራዊ መዋቅር ተግባራዊ ማድረጋቸው፣ ሦስተኛ፤ በአንዳንድ ሀገሮች የአማጺያን እንቅስቃሴ ከመጠናከር ይልቅ መከፋፈልና መበታተን እጣ ፋንታው መሆኑ እንዲሁም አራተኛ፤ የእናት ሀገር መንግስታት “ዲ’ፋክቶ መንግስት” እንመሰርታለን በሚሉ ተገንጣዮች ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውና ማሸነፋቸው አሊያም መሸነፋቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ወደ ህወሓት የ“ዲ’ፋክቶ መንግስት” ጉዳይ እንለፍ፡፡ በህወሓት እየተነሳ ያለው ሃሳብ “በሀገሪቱ ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በትግራይ ክልል ምርጫ እናካሂዳለን፣ ከዚያም ‘ዲ’ፋክቶ መንግስት’ እንመሰርታለን” የሚል እንደሆነ ከተለያዩ የክልሉ የፖለቲካ ልሂቃን ሲነገር ተሰምቷል፣ በማህበራዊ ሜዲያም ይኸው ሲናፈስ ታይቷል፡፡ ይህንን ሃሳብ በሁለት ከፍለን አንደኛ፡- “በትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድን” እና ሁለተኛ፡- “ዲ’ፋክቶ መንግስት መመስረትን” ነጣጥሎ ማየት ይቻላል፡፡
አሁን ባለው የሀገራችን ህገ መንግስት መሰረት ልክ ፓስፖርት እንደ መስጠት፣ ገንዘብ እንደማተም፣ ከመንግስታት ጋር የውጭ ግንኙነት እንደ ማድረግ፣ የመከላከያ ሰራዊት እንደ ማቋቋም፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እንደማካሄድ ወዘተ. ማንኛውንም ዓይነት “ምርጫ ማስፈጸም” የፌዴራል መንግስት ስራ ነው፡፡ እናም በትግራይ ክልል ምርጫ እናካሂዳለን ማለት ህጋዊ መሰረት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ክልሎች የፌዴራል መንግስትን ሥራ መስራት አይችሉም፤ ፌዴራል መንግስትም የክልሎችን ሥራ ቀምቶ መስራት አይችልም፡፡ በዚህም መሰረት ትግራይ በራሷ ምርጫ ማካሄድ አትችልም፡፡ ፌዴራል መንግስት ከተስማማና ምርጫ ቦርድ እሺ ካለ ግን በትግራይ እውቅና ያለው ምርጫ አካሂዶ አሸናፊው ፓርቲ ወይም ጥምር ፓርቲዎች የክልሉን መንግስት ማቆም እንዲችሉ የማድረግ መንገድን በስምምነት መፍጠር ይቻላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ልብ አድርጉ “ግምት አለኝ” ነው ያልኩት፡፡ ይህንንም ግምት ለማስቀመጥ የፈለግኩበት ምክንያት “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ አበው፣ ሁኔታው ቢያስጨንቀኝ አንዳች መላምት ለማመላከት በማሰብ ነው፡፡
ህወሓቶች “በትግራይ ዲ’ፋክቶ መንግስት እንመሰርታለን አሉ” የሚለውን ስሰማ በጭንቅላቴ ያቃጨለው “እነዚህ ሰዎች ከምራቸው ነው? ወይስ በዶ/ር ዓብይ መንግስት ላይ ጫና ፈጥረው ለመደራደር? እንመስርትስ ቢሉ በየትኛው መንገድ ማሳካት ይችላሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ህወሓቶች ህጋዊውን መንገድ ትተው በጉልበት “ዲ’ፋክቶ መንግስት” እንመሰርታለን ካሉ ግን በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ህዝብ፣ በመቀጠልም መላው የኢትዮጵያም ህዝብ “ይህንን ማድረግ አትችሉም” ብሎ እንደሚከለክላቸው አምናለሁ:: የህዝቡ ክልከላ ወዶና ፈቅዶ ባጸደቀው ህገ መንግስት ላይ በተጻፉት ድንጋጌዎች አማካይነት የሚንጸባረቅ ነው፡፡ ክልከላው የሚፈጸመው ደግሞ በሀገሪቱ መከላከያ ኃይል አማካይነት ነው፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ህዝብ በህገ መንግስቱ አማካይነት በሰጠው ስልጣን መሰረት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ይጠብቃል፣ ያስከብራል፡፡ እናም ህወሓት የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ ካላሰበች በስተቀር “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የመመስረቱ ህልም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ ትክክለኛ መንገድም አይደለም፡፡ ህወሓት የምትፈልገው የትግራይን ክልል በመገንጠል “ሀገረ ትግራይን” መመስረት ከሆነ (እኔ ባላምንበትም) በሀገሪቱ ህገ መንግስት በአንቀጽ 39 ላይ በተቀመጠው የህግ አግባብ መሰረት መጠየቅ መብቷ ነው፡፡ ዱሮም ይህ አንቀጽ የተቀመጠው ለህወሓት “የክፉ ጊዜ” መሹለኪያ ተብሎ መሆኑን አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ግን ግን ባኮረፍን ቁጥር እንገንጠል የምንል ከሆነ፣ ነገሩ ሁሉ የእቃቃ ጨዋታ እንጂ ሀገርና ህዝብ የመምራት ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የሚያዛልቅም፣ የሚያዋጣም፣ የሚጠቅምም አይመስለኝም፡፡
እንደኔ እንደኔ ለትግራይም፣ ለኢትዮጵያም የሚበጀው መንገድ “ዲ`ፋክቶ ስቴት” ማቆም ሳይሆን ዛሬም ነገም ከነገ፣ ወዲያም የተለያዩ ፖለቲካዊ መድረኮችን በመፍጠር አጀንዳ ቀርፆ መደራደር፣ መደራደር፣ መደራደር፣ … ብቻና ብቻ ነው፡፡ ባደጉትና በሰለጠኑት ሀገሮች ያሉ ፖለቲከኞች የሚያደርጉት ይህንን ነው፡፡
በመጨረሻም አንድ ነገር ልበልና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን፤ የትግራይ ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎም ከዓለም ህዝብ የተለየ እንደሆነ የሚያስቡ ይመስለኛል፡፡ በኔ ግምት እንዲህ ያለ ብዥታ ሊፈጠር የቻለው እነርሱ ራሳቸው የትግራይን ህዝብ በቅጡ ስለማያውቁት ነው ብዬ አስባለሁ:: በመሆኑም ከመቀሌ፣ ከአክሱም ሆቴል፣ …ወጣ ብለው የህዝቡን ስሜት ቢረዱ መልካም ነው፡፡ ያለበለዚያ ካድሬ የሚያመጣው “ውሸት” በህዋ ላይ ህንፃ እንዲገነቡ ብቻ ሳይሆን ውሎ አድሮ ከህዝብ ጋር ያጣላቸዋል፣ ያጠፋቸዋል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊውን በEmail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1791 times