Print this page
Saturday, 30 November 2019 12:39

ዜና ዕረፍት - መንግሥቱ አበበ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    የወዳጆቹ ማስታወሻ - ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ


         ላለፉት 18 ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በከፍተኛ ሪፖርተርነት ሲያገለግል የቆየው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን የቀብር ሥነሥርዓቱ እሁድ ህዳር 14 በቀጨኔ መድሃኒያለም ቤ/ክርስቲያን ቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና የስራ ባልደረቦቹ በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመቀላቀሉ በፊት በመንግሥት እየታተመ ይወጣ በነበረው ሳምንታዊ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በዜናና አምድ አራሚነት፣. የጋዜጠኝነት ሥራን በ1977 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን ቀጠሎም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመዛወር፣ በሪፖርተርነት በኋላም የካቲት ይባል በነበረው ወርሓዊ የመንግሥት መጽሔት በተባባሪ አዘጋጅነት አገልግሏል፡፡ በመቀጠልም በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ይታተም በነበረው ዕለታዊ አዲስ  ጋዜጣም በከፍተኛ ሪፖርተርነት አገልግሏል፡፡
በመጨረሻም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወቱ እሰካለፈበት  ጊዜ ድረስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በተመደበበት የጋዜጠኝነት መስክ ሁሉ ሁለገብ ሆኖ የሰከኑና ሚዛናዊነትን የተላበሱ በሳል ጽሁፎችን ለአንባቢያን ሲያቀርብ የቆየ ከፍተኛ ሪፖርተር ነበር፡፡  
ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፤ በተለይም በማህበራዊ፤ በሳይንስና በጤና-ነክ ጽሁፎቹ በበርካታ አንባቢያን ዘንድ የተወደደና በሥራ ባልደረቦቹ የተመሰገነ ታታሪ ጋዜጠኛ ነበር፡፡  
አመለ ሸጋው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ለኢንፎርሜሽን ሳይንስ ከነበረው የጠለቀ ፍቅር የተነሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲከታተል የነበረውን የማኔጅመንት ትምህርት አቋርጦ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሳይንስ በባችለር ዲግሪ ተመርቋል::  
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል፣ በጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለፀ ለቤተሰቡ፤ ለዘመዶቹ፤ ለሥራ ባልደረቦቹና ለጓደኞቹ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ፈጣሪ ነፍሱን በመንግስተ ሰማያት ያኑርለት፡፡


         «የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ መንግስቱ አበበ፣ ከዚህ አለም በሞት በመለየቱ በእጅጉ ሀዘን ተሰምቶኛል።
መንጌን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተዋወቅሁት፣ የጉዞ አድዋ የመጀመሪያ ጉዞ ፍፃሜ ላይ፣ የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. አድዋ ድረስ ከመጡ የጋዜጠኞች ቡድን አንዱ ሆኖ ነው።
ከተዋወቅን በኋላ በተደጋጋሚ ተገናኝተናል። ፍፁም ቅን ሰው ነበር። ለስራው በግሉ የሚወስደው ከፍተኛ ኃላፊነትና ለመልካም ነገር በፍጥነት ሁሌም የሚገኝ ሰው በመሆኑ እደሰትበት ነበር። ከዚህ አለም በሞት መለየቱን በመስማቴ በእጅጉ አዝኛለሁ።
ለቤተሰቦቹና ለስራ ባልደረቦቹ በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ።”
(ያሬድ ሹመቴ - ፌስቡክ)
***
«የቀድሞ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ባልደረባዬ፣ ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ፣ ከዚህ ዓለም መለየቱን ፌስቡክ ላይ አነበብኩ።
አንዳንድ ጊዜ ከሩቅ ሆኖ ነፍስ ይማር ማለትም ይተናነቃል። ምናልባት ሕይወቱ ማለፉን መቀበል አቅቶኝ ይሆናል።
መንጌ ጥሩ ባልደረባዬ ነበር። ብዙ ሳቆችን አብረን ስቀናል። አገሬ ተመልሼ የማገኛቸው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየቀነሰ ሲመጣ በጣም ያስከፋል። ግን ምን ይባላል? የፈጣሪ ሥራ አይቀየር።
ለቤተሰቦቹና ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቤተሰቦች መፅናናቱን ይስጣችሁ። እግዚያብሔር ነፍስህን በአፀደ ገነት ያሳርፈው። ደህና ሁን፤ ወንድሜ መንጌ!”
(ጽዮን ግርማ ታደሰ - ፌስቡክ)
***
“ከዚህ ዓለም በሞት የተለየንን ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበን፣ በሥራዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅሁት በ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የ”ሕብረተሰብ” አምድ አዘጋጅ ሆኖ በሚያቀርባቸው ፅሑፎቹ ነበር።
ከዚያ በኋላ በ‘90ዎቹ መጀመሪያ  በ”ዕለታዊ አዲስ” ጋዜጣ ኤዲተርነት፣ ላለፉት 15 ዓመታት ደግሞ በተወዳጅዋ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ከከፍተኛ ሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት ሠርቷል።
በጋዜጠኝነት ሙያ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜን ያሳለፈው መንግሥቱ አበበ ፤ ጋዜጠኛነትን  ታስሮ መግነኛ፣ የፖለቲካ መሸቀጫ፣ ጥገኝነት ማግኛና ወደ ሌላ ሙያ መሸጋገሪያ ድልድይ አድርገው የሚያዩ “የሥም ጋዜጠኞች” በሞሉባት ሀገር ላይ በሙያው በቅቶ፣ በሙያው ታምኖ፣ ሥነ ምግባር ጠብቆና “ግነን በሉኝ” ሳይል፣ ድምፁን አጥፍቶ፣ ያለፈ ጎምቱ ጋዜጠኛ ነው። ስለ ጠባዩም ባልደረቦቹ ሲያወጉኝ፤ ”ትሁትና ከአፉ መጥፎ የማይወጣው ሰው ነበር” ብለውኛል፡፡
በሠላም እረፍ መንጌ !!!”
(ጀሚል ይርጋ - ፌስቡክ)
***
“መንጌ፤ ከረጅም ጊዜ ጓደኞቼ አንዱ ብቻ ሳይሆን የሙያ ባልደረባዬም ጭምር ነበር:: እኔ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ እሰራ በነበረበት ጊዜ፣ መንግስቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት ይሰራ ነበር፤ ሙያችን ያገናኘን ነበር፡፡
ከጭምትነቱ፤ ከትሁትነቱና ሰው አክባሪነቱ በላይ ስለ መንግስቱ ሳስብ በጣም የሚገርመኝ፣ ምን ቢቸገር ክብሩን የማያዋርድና ብዙዎች ዘንድ የማይታይ ጨዋ ሰው መሆኑ ነበር፡፡
ሙያውን በማክበሩና መወስለትን ስለሚጠየፍ ሳይጠቀም የኖረ ሰው ነበር፡፡
ሕመሙ በጠና ሰዓት እንኳን ሰውን ያስቸገረ እየመሰለው ዕርዳታ ማግኘት ሳይችል ተጎድቶ ያለፈ ሰው ነው፡፡  ለመንግስቱ አበበ የነበረኝን ክብር በተለየ ሁኔታ ከፍ ያደረገልኝ ሌላው ነገር ደግሞ፣ በህይወቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ያደረገው እጅግ ታላቅ ነገር ነው፡፡
በእጁ ላይ የነበረችው እጅግ ትንሽ ጥሪት፣ ለኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ እንድትውልለት መናዘዙ፣ መንጌ ለሁላችንም ትምህርት ሰጥቶን ያለፈበት ታላቅ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነፍሱን ይማርልን!...”
መለሰ አወቀ
(የቀድሞ የሙያ አጋርና ጓደኛ)
***
“ከአንደበቱ ክፉ ቃል የማይወጣው፤ በቻለው አቅም ሁሉ ለሰዎች በጎ ነገር ለማድረግና ለማስደሰት የማይታክት መልካም ወዳጄ ነበር - መንግስቱ አበበ፡፡
የመንጌ ትጋትና ጥረት እጅግ የሚያስገርም ነበር፤ በህመም እየተሰቃየ ባሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ፣ ከስቃይ ጋር እየታገለ ስራውን ለማከናወን ደፋ ቀና ማለቱን አላቋረጠም ነበር:: መንጌ ከመልካምነቱ፣ ከቅንነቱና ከትጋቱ ጋር ወደማይቀረው ሄደ! ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኑራት ጓዴ!...”
አንተነህ ይግዛው
(የስራ ባልደረባና ጓደኛ)
***
‹‹መንጌ ክብርና ኩራቱን እንደጠበቀ ነው ያለፈው››
መንጌን ያወቅኩት የአዲስ አድማስ ባልደረባ ከመሆኔ አስቀድሜ በተለያዩ የስራ ስምሪቶች ላይ ነው፡፡ በተለይም በ2003 ዓ.ም ወደ ነቀምት አብረን ከተጓዝንና አራት ቀናትን በስራ ላይ ካሳለፍን በኋላ ገራገርነቱን፣ ትህትናውን፣ ተጫዋችነቱንና ቅንነቱን ይበልጥ ለማወቅ ችያለሁ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አብሬው ስሰራ ስራውን እንዴት እንደሚወድ ከባልደረቦቹ ጋር እንዴት እንደሚግባባ ተረድቻለሁ፡፡
መንጌ በተለይ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በበርካታ ተደራራቢ ህመሞች ጫና ውስጥ ሆኖ እንኳን ከስራውና ከስራ ቦታው ላለመለየት ከህመሙ እየታገለ ወደ ቢሮ ስራውን ይዞ ብቅ ሲል በአንድ በኩል ስናዬው ደስ ሲለን በሌላ በኩል ከህመሙ ጋር የሚገጥመውን ትግል ከፊቱ ላይ ማንበብ በእጅጉ ያሳቅቀን ነበር፡፡
አንድ ቀን መንጌ ለምን እረፍት አታደርግም ለምንስ እያመመህ ትመጣለህ? ስል ጠየቅኩት ‹‹ለበሽታማ እጅ አልሰጥም ደሞም ተኝቶ ህመም ከማዳመጥ መንቀሳቀስ ይሻላል አሁን እኮ ደህና ነኝ›› አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ለምን ትመጣለህ ብዬው አላውቅም ጠፋ ካለ ግን አያስችለኝም ስልክ እደውላለሁ፡፡ ደህንነቱን ይነግረኛል:: መንጌ አንጋፋ ቢሆንም አብዛኞቹ ወዳጆቹና ጓደኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መንጌ የወጣት ነፍስ ነው ያለው፡፡ መታመሙን ሲሰሙ ገንዘብ ካልሰበሰብን ካልረዳነው ያሉት ብዙዎች ናቸው ግን እሱ በዚህ ጉዳይ አይደራደርም አይደረግም አለ፡፡ ሁለት የጋራ ጓደኞቻችን በእኔ በኩል ገንዘብ ልከው ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ከአንድ ባልደረባዬ ጋር እግሩ ላይ ወድቀን ስንሰጠው እንኳን ደስተኛ አልነበረም ሁሌም በራስ መተማመኑ ለስራው ያለው ፍቅር እኔን ያበረታኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን ክፉ ሲወጣው፣ ሲጨቃጨቅ ሰምቼው የማላውቀው መንጌ ከነደግነቱ ከነክብሩ እና ከነኩራቱ ነው የተለዬን:: የሰማይ አምላክ ነፍሱን በደጋጎች ጎን ያሳርፈው መቼም አንረሳውም፡፡ በዚህ አጋጣሚ በርካታ ጓደኞቹ ጋዜጠኞች መንጌን ለመሰናበትና ፍቅርና አክብሮታችሁን ለመግለጽ ከስራ ሰዓታችሁ ቀንሳችሁ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ስለተገኛችሁ አክብሮቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፡፡  
ናፍቆት ዮሴፍ (ጋዜጠኛ)

Read 10578 times
Administrator

Latest from Administrator