Saturday, 30 November 2019 12:47

“ለምን አትጠፈጥፋትም!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

    “እውነት ለመናገር በፖለቲካው አካባቢ በርከት ያሉ ሴቶች ወደ ስልጣን መውጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ አሪፍ በሚመስል መልኩ እየተንቀሳቀሱ ይመሰላል፡፡ ግን ደግሞ ሰፊው ህብረተሰብ ውስጥ ያሉት በየቀኑ የሚገጥማቸው ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡--”


           በየትምህርት ቤቱ ይደረጋሉ ስለሚባሉ ነገሮች የምንሰማቸው ለጆሮ የሚከብዱ ናቸው፡፡ እናማ…የተጋነኑትን ነገሮች ወደ ጎን ትተን እውነቱን ብናይ፣ እጅግ በጣም የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ፡፡ የሚያሳስበን ነገር ደግሞ እነኚህ እየተፈጸሙ ያሉ አጉል ነገሮች፣ ከአሁኑ መፍትሄ ካልተበጀለላቸው… ዛሬ የተተከለው ዋናው ‘ጦስ’ የሚመጣው ነገ ነው፡፡ ትናንት የተዘሩ መጥፎ ዘሮች  ውለው አድረው ምን እንደሚያስከትሉ አሁን በከፋ መልኩ እያየን ነውና!
    
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በዛ ሰሞን ነው….የሆኑ ሴቶች ስለ አንዲት ጓደኛቸው ነበር የሚያወሩት! የሆነ የተጠሩበት ግብዣ አለ መሰለኝ… ይህች የተባለችው ጓደኛቸው፣ አልመጣም ማለቷን ነበር የሚያወሩት፡፡
“…የምትመጣ አይመስለኝም፡፡”
“ለምንድነው የማትመጣው! እሺ ብላ አልነበር እንዴ!”
“እባክሽ ቤት ውስጥ ችግር አለ…”
በኋላ ወሬያቸውን ሲቀጥሉ፣ ችግር የተባለው ምን መሰላችሁ?… ባል የተባለው ሰው በሆነ ባልሆነው ሰበብ እየፈለገ ይደባደባል አሉ፡፡ የምር ግን… አለ አይደል… በዚህ ዘመን እንደዚህ አይነት በዱላ የሚያምኑ ‘ዘመናዊ ትምህርት’ የቀሰሙ ሰዎች መኖራቸው…አለ አይደል… ትንሽ ያሳፍራል፡፡ (በፖለቲካውም እኮ ያው ነው! ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ...እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… ምን የሚባል ነገር አለ መሰላችሁ… የእኛ ሀገር ወንዶች በእውቀትም ሆነ በሌላ ከእነሱ በለጥ ከሚሉ ሴቶች ጋር አብሮ መኖር አይፈልጉም የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ወዳጃችን ነበር…በእውቀቱ ገፋ ያደረገና በእኛ አተረጓጎም ‘ዘመናዊ’ የሚባል ሰው፡፡ እናላችሁ…ሚስት ሊያጋባ በወሰነ ጊዜ “እንደኔ ዘመናዊ የሆነች…” ምናምን አላለም፡፡ ገጠር ሄዶ መሰረታዊ ትምህርት እንኳን ያልቀሰመች ኮረዳ ይዞ መጣ፡፡ ወዳጆቹ ለምን እንደዚህ አይነት ውሳኔ እንደወሰነ ሲጠይቁት … ምን ቢል ጥሩ ነው፡፡ ‘የተማረች አግብቼ አሳምነኝ፣ ላሳምንህ! ጭቅጭቅ ውስጥ ምን ከተተኝ!” ብሎ አረፈው፡፡ ቀሺም ምክንያት!
እናላችሁ…ለትውልድ አስተማሪ መሆን የሚገባቸው ሰዎች… አለ አይደል… ‘በአስራ አንደኛው ሰዓት ጉርምስናቸው እየፈላባቸው ተቸገርን፡፡    
“ደስ ያለህ አትመስልም፣ ምን ሆነሀል?”
“ምን እባክ፣ ቤት ውስጥ ያቺ ሴትዮ…”
“ምን ሆናችሁ?”
“የምላትን አትሰማም፣ እኩል ትለፋለፈኛለች!”
“አንተ እሷን ምን እመኚ፣ አትመኚ አሰኘህ!  ፊት እየሰጠህት እኮ ነው፡፡ ደህና አድርገህ ብትጠፈጥፋት ልክ ትገባለች፡፡”
በአሁኑ ጊዜ እንዲህ የሚል ወንድ የለም ብሎ ማሰቡ ሰዋችንን አለማወቅ ነው፡፡ የሞራል ስብራቱ እኮ በህክምናው ቋንቋ ‘ክሮኒክ’ የሚሉት አይነት ነው ሆኗል፤፡ 
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ኬንያ ውስጥ አንድ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፡፡ ወንዶች ተሰብስበው ሴቶች ላይ አቤቱታ አቀረቡ ይባላል፡፤ ምክንያቱ ምን መሰላችሁ… “ሚስቶቻችን እየደበደቡ አስቸገሩን!” በሚል ነው፡፡ እና አሁን እንዲህ አይነት ታሪክ እኛ ሀገር ከቀሺም ፊልሞች አንዱ ሆኖ “በሁሉም የመንግስትና የግል ሲኒማ ቤቶች” ቢመረቅ… “የሚጽፉት ቢያጡ ነው እንጂ አሁን ሚስት ባሏን ደበደበች ብለው ፊልም ይሠራሉ?!” ይባል ነበር፡፡
ሚስቱ ስትደበድበው “ድረሱልኝ፣ ደበደበችኝ” ላለማለት “ኧረ ተጋደልን!” ብሎ እሪታውን አቀለጠው የተባለው ሰው… ተረት ሆኖ ቀረ ወይስ ተገኘ! (‘የፌስቡክ ቃና’ ያለባት አነጋገር አትመስልም!? “አንተ እንዲህ፣ እንዲህ ያልከው ልጅ ግን ደህና ነህ?” የሚሏት አሁን፣ አሁን እየተለመደች የመጣች ነገር ማለት ነው፡፡)
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የባልና የሚስት ነገር ካነሳን አይቀር ከጥቂት ዓመታት በፊት ሆነ የተባለ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሆነ ጎሳ አባላት ሊጋቡ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ በጎሳው ልማድ መሰረት… ሙሽራው ቀድሞ ሙሽሪት ቤት ደርሶ የሆኑ ስነስርአቶች ከተካሄዱ በኋላ ነው “ይዟት፣ ይዟት በረረ፣” የሚፈቀድለት፡፡ በስፍራው ደግሞ ጋብቻውን ፈቅደው የሚባርኩ አባቶች እየጠበቁ ነው፡፡
ታዲያላችሁ… በጎሳቸው ባልተለመደ መልኩ ሙሽራው ያረፍዳል፡፡ የተወሰነ ሰዓት አሳልፎ “ማን አለኝ ከልካይ…” በሚል ሙሽሪትን ‘ይዞ ሊበር’ ይመጣል፡፡ የተቆጡት አባቶች ደግሞ “በምንም አይነት ዛሬማ ይዟት አይሄድም፡፡ መጀመሪያ ሊቀጣ ይገባል፣” አሉ፡፡ የተላለፈበት ቅጣት ምን መሰላችሁ?… አንዲት በአካባቢው የታሰረች ፍየል ነበረች፡፡ “ፍየሏን እንድታገባ ወስነናል!” ተባለ፡፡ ታሪኩ የተገኘበት ምንጭ ላይ ስለ ‘ሃኒሙን’ ምናምን የጠቀሰው ነገር የለም፡፡   ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… አሁንም መሰልጠኗን በአብዛኛው ‘ውስጣቸው ለቄስ’ በሆኑ፤ መስታወት በረከሰባቸው ህንጻዎች ለማስመስከር እየሞከረች በምትመስልዋ አዲስ አበባ ውስጥ ባለቤቶቻቸውን ምናልባትም ልጆቻቸውንም በመደበደብ የሚታወቁ አባወራዎች መኖራቸው አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ይሄ ‘ወንድነት ማሳየት’ የሚሉት ነገር በዚህ ዘመን መጃጃል ነው (በወጣቶቹ ቋንቋ “ፋራነት!” ነው) …‘ወንድነት’ የሚሉት ነገር የሚለካው ደግሞ ከእኩያ ጋር ሳይሆን ደካሞች የሚባሉት ላይ ጡንቻን በመሞከር ነው፡፡  
 ስሙኝማ…ወንድነት ስለሚለው ነገር ካነሳን አይቀር፣ አሁንም ወደ ኬንያ ልመልሳችሁ፡፡ ከሀገሪቱ ፕሬዚደንቶች አንደኛው ‘ወንድነታቸው’ ላይ… “እሱ እኮ ዝም ብሎ ሰጋቱራ ቢጤ ነው፣” የሚሉ አሉባልታዎች ይናፈሱ ነበር:: ፕሬዚደንትዬው ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው?…ሚስታቸውን አደባባይ አወጡና… “ወንድ መሆኔን መስክሪ…” ይሏቸዋል፡፡ እናላችሁ…ሴትየዋ ‘መሰከሩ’ ተባለ፡፡
መሀል ከተማ ነው፡፡ ሁለቱ ሴቶች አስራ ስድስት፣ አስራ ሰባት አካባቢ ቢሆናቸው ነው፡፡ እናማ… እየተሳሳቁ እየሄዱ ሳሉ ‘ለከፋ’ የሚባለው ነገር ይገጥማቸዋል፡፡ “እና፣ ምን አዲስ ነገር አለው፣” ሊባል ይችላል፡፡ ግን ሦስቱ ለካፊዎች እድሜያቸው ቢጋነን፣ ቢጋነን ከአስርና ከአስራ አንድ አያልፍም፡፡ እናላችሁ… ከሁሉም በላይ አንደኛው ልጅ ወደ ሴቶቹ ዞሮ ያሳይ የነበረው አካላዊ እንቅስቃሴ…አለ አይደል… “የት ነው እንዲህ አይነት ነገር የተማረው!” የሚያሰኝ ነው፡፡ ለነገሩማ… ዘንድሮ ህጻናቱ ሁሉ ‘ስማርት ስልኮቻቸው’ በ‘ፖርኖ’ ምስሎችና ቪዲዮዎች የተሞሉ አይደሉ እንዴ!?
 እና ጉልበተኞች ባሎች… ለምን ጡንቻችሁን እኩያዎቻችሁ ላይ አትሞክሩም! አሀ…በአሁኑ ጊዜ እኮ ወፈር ያሉ ጡንቸኞች የሚያስፈልጓቸው የሚመስሉ በዝተዋል፡፡ አሀ…“ለጣይም ፈንጋይ አለው፣” በሉልና! ራሷን መከላከል የማትችል ሚስት ላይ ማይክ ታይሰን ለመሆን ከመሞከር ስንቱ… “ትከሻው ያበጠ፣ ልቡ ያበጠበት…” የሚባል አይነት መአት አለ አይደል እንዴ!
እውነት ለመናገር በፖለቲካው አካባቢ በርከት ያሉ ሴቶች ወደ ስልጣን መውጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ አሪፍ በሚመስል መልኩ እየተንቀሳቀሱ ይመሰላል:: ግን ደግሞ ሰፊው ህብረተሰብ ውስጥ ያሉት በየቀኑ የሚገጥማቸው ነገር አስቸጋሪ ነው:: “ስርአት አልበኝነት ውስጤ ነው…!” ያልን ይመስል፤ ሁሉም ነገር ግራ በተጋባን በዚህ ዘመን፣ በተለይ የመንገድ ላይ ለከፋ የሚባለው ነገር እየባሰበት እንደሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ የምር ግን... በተለይ ወጣት ሴቶችን መተናኮል… አለ አይደል… “ሰው ያየኛል…” ተብሎ የማያሰቅቅ፣ “ጦስ ያስከትልብኛል…”  የማያስብል ማንም ተቆጪ የሌለበት ድርጊት ሆኗል፡፡
ደግሞላችሁ… ይበልጡኑ የሚያሳሰበው ደግሞ ህጻናቱ የታላላቆቻቸውን ባህሪይ እየወረሱ መሆናቸው ነው፡፡ በየትምህርት ቤቱ ይደረጋሉ ስለሚባሉ ነገሮች የምንሰማቸው ለጆሮ የሚከብዱ ናቸው፡፡ እናማ…የተጋነኑትን ነገሮች ወደ ጎን ትተን እውነቱን ብናይ፣ እጅግ በጣም የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ፡፡ የሚያሳስበን ነገር ደግሞ እነኚህ እየተፈጸሙ ያሉ አጉል ነገሮች፣ ከአሁኑ መፍትሄ ካልተበጀለላቸው… ዛሬ የተተከለው ዋናው ‘ጦስ’ የሚመጣው ነገ ነው፡፡ ትናንት የተዘሩ መጥፎ ዘሮች  ውለው አድረው ምን እንደሚያስከትሉ አሁን በከፋ መልኩ እያየን ነውና! ስሙኝማ...ይህን ነገር ደጋግመን የምናነሳው ነገርዬው ከእለት እለት እየባሰበትም ዝምታው ቢበዛብን ነው፡፡ መንገድ ላይ ይህ ሁሉ ወከባ የሚደርስባቸው እኮ እናቶች፣ ሚስቶች፣ እህቶች፣ የትዳር ጓደኞች ናቸው፡፡
እናማ…“ለምን አትጠፈጥፋትም!” የምትባሉ አባወራዎች፣ ረጋ በሉማ! ማቀፍን የመሰለ መልካም ነገር እያለ መምታትን ምን አመጣው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1289 times