Saturday, 23 June 2012 07:50

የ’ዝና’ መንገድ

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

ከስድስት ወራት በፊት ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት እናቴ ያወጣችልኝ ‘ማስረሻ የተሰኘ ስሜን ከቡሬ ወረዳ ሕዝብ አልፎ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው ለማድረግ በማሰብ ነበር። ሆኖም እንዳሰብኩት አልሆነም። እንኩዋን በመላው ኢትዮጵያ ሊታወቅ ቀርቶ እኔም ራሴ ወዲያው ነበር  የገዛ ስሜን የረሳሁት። በአስተናጋጅነት በተቀጠርኩበት ሆቴል ከወጣልኝ ስም ጋር ለመለማመድ ባደረግሁት እልህ አስጨራሽ ትግል ‘ማስረሻ’ የተባለው ስሜ ከውስጤ ተሸርሽሮ ጠፋ። ከዚያ በሁዋላ ምርጫ አልነበረኝም - “ሰባት ቁጥር” ስባል ‘አቤት’ ከማለት በቀር።

ስሜን ከፍ አድርጌ ልሰቅል የመጣሁባት አዲስ አበባ  ስሜንም ቅስሜንም ሰበረችው። አገር ቤት ሳለሁ እንደማስበው ‘ስምን መትከል’ ቀላል ሆኖ አልጠበቀኝም። ወደ አዲስ አበባ አመጣጤ በግጥም መሰላል ተወጣጥቶ ከሕዝቡ ላይ መዋል….ድብቅ ተሰጥኦዬን ማውጣት….የግጥም መፅሃፌን ማሳተም…. ‘ማስረሻ ቢተው’ የሚል ስም ከአገሪቱ ባለቅኔዎች ተርታ መጨመር ነበር። በቃ ይኸው ነው ከቤተሰቦቼ ነጥሎ ወዲህ ያመጣኝ።

በመዲናይቱ ስሰነባብት ግን ከመጽሐፍ ይልቅ ገንዘብ ማሳተም እንደሚቀለኝ አወቅሁ። አሳታሚዎች ሁሉ ግጥሜን ትቼ፣ ጠኔዬን ለማርካት ወደ አገር ቤት እንድመለስ፣ አልያም የቀን ሥራ እንዳፈላልግ መከሩኝ። ለነገሩ ባይመክሩኝም እኔም ገብቶኛል። ሁለተኛውን መርጬ በስንት ውጣ ውረድ በአስተናጋጅነት ተቀጠርኩ።

መጠጥ እወስዳለሁ…ባዶ መለኪያ እመልሳለሁ። በቃ ሲመላለሱ መዋል….ሲመላለሱ ማምሸት።

‘ስካር ማመላለስ’ የኑሮ ግዴታዬ ሆነ!

ቀጣሪዬ የሆቴሉ ባለቤት በሰጡኝ ትዕዛዝ መሠረት፤ ከቤት ውጭ ያሉትን ደንበኞች አስተናግዳለሁ። እንደ ከተማ አውቶቡስ በቁጥር እየተጠራሁ በጠጪና በቀጂ መካከል እመላለሳለሁ። መሸት ሲል ተስተናጋጁ ከዋናው ባር ተርፎ ግቢውን ያጥለቀልቀዋል። ምክንያቱን ባላውቀውም ብዙ ደንበኞች የግንብ አጥሩን ተጠግተው በሚደረደሩ መኪኖቻቸው ውስጥ ነው የሚጠጡት። እኔ የነዚህኞቹ ታዛዥ ነኝ። መኪኖች ወደ ግቢው ሲዘልቁ ምቹ ቦታ አመላክታቸዋለሁ…ክፍት ቦታ እጠቁማቸዋለሁ። የመኪናቸውን መስኮት ዝቅ አድርገው በጥቅሻ ወይም በጭብጨባ ይጠሩኛል። በግጥሜ በመመሰጥ ሳይሆን፣ ጥማቸውን ለመቁረጥ ያጨበጭቡልኛል። ፈጥኜ ከፊታቸው እቆማለሁ….ትዕዛዝ ተቀብዬ እፈጽማለሁ።

ጨለማው ሥር ቆሜ እስኪጠሩኝ እጠብቃለሁ። እየጠበቅሁ ብዙ ነገር አስባለሁ… ስለቤተሰቦቼ…ስለግጥሜ…ስለህልሜ።

በመሀል አንዱ ይጠራኛል - ያለ ስሜ!

“ሄሎ ማነህ… ሰባት ቁጥር?” ሲለኝ ሮጥ ብዬ ከፊቱ እቆማለሁ።

“ማስረሻ ነኝ” ልለው ስዘጋጅ

“በረዶ ይዘህ ና” ብሎ ያባርረኛል። ከጎኑ የቆመች ሌላ መኪና ጥሩንባዋን ታጮህብኛለች - “ና ወዲህ”  ማለት ነው። በረዶውን ሰጥቼ በጥሩንባ ወደጠሩኝ ጥንዶች እሮጣለሁ…ጎንበስ ብዬ ትዕዛዙን እጠብቃለሁ።

ጋቢና ውስጥ ጥንዶቹ ይታዩኛል። እቅፉ ውስጥ ሆና ከላይ እታች ትናጣለች። ከደረቱ ትነጥርና ወደ ኋላ ተለጥጣ የመኪናዋ መሪ ላይ በጀርባዋ ትዘረራለች…

ጎንበስ እንዳልኩ የመኪናዋ ጥሩንባ ደግሞ ይጮሀል። ይሄኔ እንዳልተጠራሁ ይገባኛል። ድምፁ የተፈጠረው የሴቲቱ አባት መሀል መሪውን ሲወቅረው መሆኑ ይገለጥልኛል። ከደረቷ ወደ መሪው ይንጣታል…ልጅቷ ወተት ብትሆን ጋቢና ሙሉ ቅቤ በወጣት! ድንግጥ ብዬ ፊቴን ሳዞር ከፊት ለፊት ጨለማው ሥር የቆመችው የቤት መኪና መብራቷን ትረጭብኛለች። ይሄ ጥሪ ነው።

ሁሉም ይጠራኛል … ወደ ሁሉም እሄዳለሁ…ሁሉም ይጠይቀኛል…አምቦ ውሃ…በረዶ…ሁለት ቢራ…ሦስት ጎርደን…ሲንግል ስቶልቺሊያ…ሒሳብ…

ይሄው ወራት አለፉ። ከአንደኛው ተስተናጋጅ በቀር ሁሉም ከዚህ ውጪ አልጠየቁኝም። ከየት መጣህ? ለምን መጣህ? ማነህ? አላሉኝም። እኔ ለነሱ ቁጥር ነኝ - ከጠጪ ወደ ቀጂ፤ከቀጂ ወደ ጠጪ የምወረወር ተላላኪ። የወጥ ቤት ኃላፊዋ ወፍራም ሴትዮ፤ እንጀራ አመላላሹ ተሸካሚና አንዳንዴ በህልሜ የምትመጣው እናቴ…እነዚህ ብቻ ናቸው “ማስረሻ” እያሉ በመጥራት ስሜን የሚያስታውሱኝ…ወደ ትናንቴ የሚመልሱኝ። ከተረሳሁበት አዲስ አበባ ወደ ተነሳሁበት ቡሬ ዳሞት የሚወስዱኝ እነሱ ናቸው።

“ይቅናህ” ተብዬ ወደ ተሸኘሁበት ቡሬ አቦ…ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ ማር እትፍ ተብሎብኝ ተመርቄ ነው የተሸኘሁት። “ይሁንልህ” ተብዬ። በእናቴ፤በእህቴ እንዲሁም መሄዴን ሰምተው ተሽንዲና ተቲሊሊ፤ ተሻኳና ተባጉና ማሪያም… ተየገጠሩ ተጠራርተው በመጡ ዘመዶቼ ታጅቤ ነው የተሸኘሁት።

እርግጥ ሁሉም መሄዴን ደግፈው አልነበረም ሊሸኙኝ የመጡት። እታለም ጌጤ…አዋ ምናለ… እማማ እንኳየሁ… “ተው ግዴለም ትምህርትህን ፈጥምና ግጥሙን በኋላ ትደርስበታለህ” ብለውኝ ነበር። ከአስረኛ ክፍል አቋርጬ ወደ አዲስ አበባ መሄዴን የሰሙ ጓደኞቼ፤ ‘በጄ’ አልላቸው ብዬ እንጂ ሊመክሩኝ ፈልገው ነበር።

ዋናው እናቴን ማሳመኔ ነበርና ነጋ ጠባ ወተወትኳት።ሁለት ባለ 32 ገጽ ደብተር ሞልቶ የተረፈ ግጥሜን ለወግ የማበቃበት ጊዜው አሁን ነው አልኳት።

“ትምህርትህስ የኔ አካል?” አለችኝ።

“ሳልሞት ወግህን ሳታሳየኝ ትተኸው ትኸድ?” ብላ ሞገተችኝ። መሄዴ ሳትሞት ወግ ላሳያት በማሰብ መሆኑን ነገርኳት። እያረጀች ነው። ልፈጥንላት ይገባኛል። እናትም አባትም ሆና ሦስታችንንም ለማሳደግ ደፋ ቀና ብላለች። የመጀመሪያዋ እህቴ ነፍስ ሳላውቅ ነው የሞተችው። ሁለተኛይቱ ዘውዴ ሽንዲ ወረዳ አንድ መምህር አገባች። ትዳሩም ትዳር አልሆነላት። ባል ተብዬው ሲያቃጥላት ኑሮ፤  እድገት  አግኝቶ ማንኩሳ ሲገባ እሷን አንድ ልጅ  አስታቅፎ ፤ወደ እናቴ ቤት ላካት። በሰው በሰው ተብሎ ለልጁ ተቆራጭ እየላከ፤ እህቴ ከእናቴ ጋር ጠላ እየጠመቀች መኖር ጀመረች።

መቁረጫው እኔ ነኝ። እህ እኔ ውለታዋን ካልከፈልኳት እናቴ አፈር መስላ እንደኖረች አፈር መግባቷ አይደል?! ትምህርቴን ጨርሼ… ኮሌጅ ገብቼ… ተመርቄ… ሥራ አግኝቼ ውለታዋን መክፈል አቅቶኝ አይደለም ። ይህቺ ሴት እኮ እያረጀች ነው!! ብትቀደመኝስ? ግጥሞቼን ይዤ ሞቷን ልቀድመው ተነሳሁ። “ማስረሻ” ብላ ያወጣችልኝን ስም ተቡሬ አቦ ላሻግረው፤ ግጥሜን ሽጬ ኑሮዋን ልደጉመው አውቶቡስ ውስጥ ገባሁ።

እናቴ ተምባና ተፀሎት በቀር አቅም የላትም። አፍዋን በኩታ ሸፍና እየተንሰቀሰቀች ተሰናበተችኝ። ዘመድ አዝማድ የሸጠውን ሽጦ እንደየአቅሙ በኪሴ ሸጉጦ “ይቅናህ” አለኝ። ያልቻለው ምክሩን አልነፈገኝም “ጎጃም በረንዳ ወርደህ የአዋ ቢተውን ልጅ ፈልገው። ተኪስህ ብር አታብዛ። ተላይ ተላይ መጣፍህን እየሸጥክ ተባንክ ነው ማጠራቀም” ምክሩንም ብሩንም ተቀብዬ ለመጽሐፌ ሕትመት አስተዋጽኦ ላደረጉልኝ ባለውለታዎቼ ባዘጋጀሁት የምስጋና ገጽ ላይ የማንን ስም ጠቅሼ የማንን ስም እንደምተው ግራ እየገባኝ አውቶቡሱ ዋጠኝ።

እያክለበለበ ዓባይን አሻግሮ ለአዲስ አበባ ሰጠኝ። ለወራት ትርምሱ ውስጥ ተመላለስሁ፤ ግጥሞቼን ይዤ ባዘንሁ። ቢያንስ በየመንፈቁ እያሳተምሁ ከሰዎች በላይ እውላለሁ…የዘመዶቼን ውለታ እከፍላለሁ ብዬ የመጣሁባት አዲሳባ ጉድ ሰራችኝ። ዕድሜ ለሬስቶራንቱ  ባለቤት! በግጥም ሳይሆን ለደንበኞች እየታዘዝኩ  በረሃብ ከመሞት ተረፍኩ - እንኳን ታሪኬን ስሜን መስማት ለማይፈልጉ ጠጪዎች “ሰባት ቁጥር” ሆኜ። ከዚያ ሁሉ ተስተናጋጅ መካከል አንዳቸው እንኳን አልጠየቁኝም- ከእኒያ ሰውዬ በቀር። የነጯ መኪና ባለቤት ስሜን ጠይቀውኛል። ስሜን አስታውሰውኛል። መምጫዬን ልስማህ ብለውኛል። ብዙ ነግሬያቸዋለሁ። በመጡ ቁጥር ካቆሙበት ያስቀጥሉኛል። “ማስረሻ፣ አጫውተኝ” ይሉኛል። እኔ ግን ስማቸውን አልጠየቅኳቸውም።  “የነጯ መኪና ባለቤት” እያልሁ እጠራቸዋለሁ። እሳቸው እንደ ሌሎች ደንበኞች አይደሉም። ሲመጡም ሲሄዱም ብቻቸውን ነው።

መሸት ሲል በነጯ መኪናቸው ብቅ ይላሉ። ደስ ይለኛል። ጨለም ያለ ቦታ ፈልጌ ካስያዝኳቸው በኋላ መስኮቱን ከፍተው የተለመደ ፈገግታቸውን ሳያስተጓጉሉ “ማስረሻ” ይሉኛል። ደህንነቴን ይጠይቁኛል። ብቻቸውን ናቸው፤ ጨዋታቸው ከሲጋራቸውና ከሞባይላቸው ጋር ነው። ሹክሹክታቸው ከኩርቫይዘር ጋር ነው። ከየአቅጣጫው የሚወጣው የጠጪዎች ትዕዛዝ ጋብ ሲልልኝ ደግሞ ከእኔ ጋር ያወራሉ (ይቅርታ እኔን ያዳምጣሉ) አሁንም አሁንም የሚለኩሱትን ሲጋራ እያቦነኑ “እሺ…ከዚያስ” ይሉኛል። መኪናው ላይ ተለጥፌ ቶሎ ቶሎ አወራቸዋለሁ።አሳታሚዎቹ ተስፋ ካስቆረጡኝ በኋላ ፍራሽ ሥር የደበቅኳቸውን የግጥም ደብተሮቼን  መልሼ የከፈትኳቸው በእሳቸው ምክንያት ነው። ስለ ግጥም ተሰጥኦዬ ያወራኋቸው ምሽት ከአንደኛው ደብተር አስራ አንድ፤ ከሌላኛው ስምንት - በድምሩ 19 ግጥሞችን አነበብኩላቸው። እሳቸው እንኳን ጨምሬ እንዳነብላቸው የፈለጉ ይመስለኛል።“የሕይወት ስንክሳር” ን አንብቤላቸው እንደጨረስኩ እንደዋዛ ፊቴን ሳዞር አንድ አንድ ሴቶችን አቅፈው እያውካኩ የሚጠጡ ሁለት ወጣቶችን ይዛ ጥግ ላይ የነበረችው መኪና በቦታዋ አልነበረችም። ተመስጬ 19 ግጥሞችን ሳነብ ጥሪያቸውን መስማት ባለመቻሌ 19 ብር እላፊ ይዘውብኝ ሄደዋል። ለነገሩ ይሂዱ… የነጯ መኪና ባለቤት መስማት ብቻ ሳይሆን መስጠትም ያውቁበታል። የጎደለውን ሒሳብ ከደመወዜ ላይ ከመቆረጥ አዳኑኝ። ለነገሩ በእያንዳንዱ ምሽት ጉርሻ ነፍገውኝ አያውቁም። ከጉርሻቸው በላይ ግን እንድወዳቸው ያደረገኝ ማዳመጣቸው ነው። ሳይሰለቹ “እህ…” ብሎ ማዳመጣቸው ነው እንድናፍቃቸው የሚያደርገኝ።አንድም ቀን ሳት ብሏቸው ስለራሳቸው አውርተውኝ አያውቁም…እኔማ ምን ያላወሯሁዋቸው አለኝ!! ዝና ለመጎናጸፍ፤ስሜን ከፍ አድርጎ ለመትከል…በስንኝ ገንዘብ አፍሼ የእናቴን ውለታ ለመመለስ ቀና ደፋ ያልኩበትን ኑሮዬን ዘክዝኬ አውርቻቼዋለሁ።

ለወትሮው የማይጠፉት የነጯ መኪና ባለቤት፤ይኸው ሁለት ሳምንታቸው ዝር አላሉም፤ ጠፍተዋል። “ምን ነካቸው?” አልኩኝ፤ በር በሩን እያየሁ። ለመጨረሻ ጊዜ ከግቢ የወጡበትን ምሽት ለማስታወስ ሞከርኩኝ።

እንደ ህልም እንደ ህልም ትዝ ይለኛል። እንደተለመደው ከመኪና መኪና እየተመላለስኩኝ ደንበኞችን አስተናግዳለሁ። ዘወትር ከቤቱ የማይጠፉት ዓመለ ሸጋዎቹ ፍቅረኛሞች፤ ሲላቀሱና ሲሳሳሙ ቆይተው ድንገት ሳላያቸው ውልቅ ብለዋል - ሁለት ብር ጉርሻና አንድ ጋዜጣ መሬቱ ላይ ጥለው። ብሮቹን በኪሴ ከትቼ፤ ጋዜጣቸውን ማገላበጥ ያዝኩኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሰውዬውን ከነጯ መኪና ውጪ አየኋቸው። ዓይኔን ማመን አልቻልኩም። ግን እሳቸው ናቸው። ጋዜጣው ላይ ፎቷቸው ይታየኛል። “ዝነኛው የፊልም ዳይሬክተር ዝናን ፍለጋ  የተሰኘ አዲስ ፊልም እየሰሩ ነው” ከሚል ርዕስ ሥር ጉብ ብለዋል። ጋዜጣውን ይዤ ተወራጨሁ። ለወጥ ቤት ኃላፊዋ ሴትዮ፤ ለውስኪ ቀጂው በሽር፤ ለአስተናጋጆቹ ፤ ለካሸርዋ… ለሁሉም አሳየኋቸው።“የነጯ መኪና ባለቤት የዋዛ ሰው እንዳይመስሏችሁ” አልኳቸው። ሁላችንም በር በሩን ስናይ ዋልን።

“ብርድ በሽታዬ ይነሳብኛል” በሚል ውጭ አላስተናግድም ብሎ አሻፈረኝ ያለው ሳሚ “ደንበኛ በዝቷል፤ ላግዝህ” አለኝ። ሰውዬው መጡ። እንደ ወትሮው ሰላምታ ሰጡኝ። እኔ ግን ሳላውቀው እንደወትሮው አልነበርኩም። በችኮላ ተጠጋሁና ጋዜጣውን እያሳየሁ “ለካ ታዋቂ ሰው ነዎት!” አልኳቸው። እየተጣደፉ ጠጡ…እየተጣደፉ ወጡ! በቀጣዩ ምሽት ግቢውን ከሞላው መኪና ውስጥ ነጯ መኪና አልነበረችም። ይሄው ስንት ጊዜዋ…

 

 

 

Read 4478 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 10:54