Sunday, 01 December 2019 00:00

ትዝታ ዘ ፋና ሬዲዮ

Written by  ኦሃድ
Rate this item
(0 votes)

   ኢሕአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት፣ “የሰላምና መረጋጋት” በሚል ስያሜ ሥራ  የጀመረው የሬዲዮ  ጣቢያው፤ የተለያዩ ባለቤቶችን ቀያይሯል። ኮከብ ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ፤ ፋናን ለሬዲዮ፣ ዋልታን ለዜና አገልግሎት በመመደብ ወደ ሥራ  አስገባቸው:: በአጭር ጊዜ ውስጥም ያልተጠበቀ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ቻሉ፡፡ ይኼ ዕድገት ሁለቱም  በየፊናቸው እንዲከንፉ ሲያደርጋቸው የፋና ባለቤት ተቀየረ። ከህወሓት ኢንዶውመንት ወደ ሜጋ ኮርፖሬሽን፣ ከዚያም ወደ አራቱ የኢህአዴግ ፓርቲዎች ንብረትነት ተዛውሯል፡፡ ፋና፤ አሁን በምሥረታ ላይ የሚገኘው የ”ብልጽግና ፓርቲ” ከሚወርሳቸው ወይም ከሚካፈላቸው ንብረቶች አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡
ከመነሻው ጀምሮ ፋናን የግል ንብረት አስመስሎ ለማቅረብ፣ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል:: የገዢው ፓርቲ ንብረት መሆኑ ግን የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ምናልባት ባለቤቱን መደበቅ ያስፈለገው የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ሥራ ላይ መሰማራት ስለማይፈቀድላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ (በሻላ ማስታወቂያ፣ በኋላ ሜጋ ማስታወቂያ በተባለው) ይነግድ ነበር። ይሄ አካሄድ ህገ ወጥ መሆኑን ሁሉም ያውቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ  ጥያቄ ማንሳት ግን አይቻልም፡፡ በዚህና  መሰል ጉዳዮች ላይ የነበረው የግልጽነት ችግር፣ በሰራተኛውና በሥራ ድባቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡
በወቅቱ አብዛኞቹ የፋና አመራሮች፣ (ከዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሙሉጌታ ገሠሠና አቶ ወልዱ ይመስል በስተቀር) የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት የቀሰሙ አልነበሩም። ይሄ ደግሞ ከአመራሩ ጋር በቅጡ ተግባብቶና ተመካክሮ መስራትን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ በፋና ይሰሩ የነበሩ ታጋዮች በአብዛኛው የዋህ ነበሩ ማለት ይቻላል። በርግጥ የተጠራጣሪነት ስሜትም ይታይ ነበር:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያልጨረሱ ነባር ታጋዮች፣ ለባለ ድግሪ የድርጅቱ ባለሙያዎች አለቃ ሆነው ይሾሙ ነበር። (የተማረኩ መቶ አለቆችም ነበሩበት) በሌላ በኩል፤ ሙሉጌታ ገሰሰ፤ ፋና ሬዲዮን የጸና መሰረት ላይ በማቆም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ሙሉጌታ ከሁሉም ሰው ጋር ተግባብቶ መሥራት የሚችል ሰው ነበር። ከሱ ጋር ውለህ ህወሓትን መጥላት አትችልም፡፡ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢኖርም እንኳን ለጥላቻ ቦታ አይኖርም፡፡ ሙሉጌታ፤ ስለ በረሃ ህይወት መተረክ ከጀመረ የሚያቋርጥ ነገር እንዳይፈጠር እንሳሳለን፡፡ ፋና በመሥራቴ ያተረፍኩት አንዱ ነገር፣ የታጋዮችን ሰብዕናና ለሕዝብ ያላቸውን የከበረ ፍቅር ለመረዳት መቻሌ ነው፡፡
ሙሉጌታ ገሰሰ ሜጋ ማከፋፈያን ደርቦ እንዲሠራ መደረጉን ተከትሎ፣ አመልማል መጀመሪያ በተጠባባቂነት፣ በኋላም በሥራ አስኪያጅነት ቦታውን ተረክባ መስራት ቀጠለች። “የበረሃዋ ንግስት”፣ የህወሓት የትግል ሜዳ አንባቢዋ አመልማል፣ ከሙሉጌታ ጋር የምትስተካከል አልነበረችም፡፡ በዚህም የተነሳ ማኔጅመንቱ ችግር ገጠመው፡፡ ሠራተኞች ፋናን እየለቀቁ መውጣት ጀመሩ፡፡ ስብሰባዎችና ግምገማዎች ወዝና ለዛ አጡ፡፡ ይሁን እንጂ ፋና ሬዲዮ ከግስጋሴው አልተገታም፡፡
የፋና የገበያ አቅም ምስጢሩ፣ የገዥው ፓርቲ ንብረት መሆኑ ነው። ሙሉጌታ፤ ይሄን አቅም እንዴት ከዘመናዊ የማርኬቲንግ ጥበብ ጋር አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል:: የመንግስት የልማት ተቋማት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና የክልል መስተዳድሮች፤ በኃላፊነት በታጀበ ስሜት፣ የጣቢያውን የማስታወቂያና የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎችና ፍላጐቶች ያሟላሉ፡፡ መያዶች፣ የሁለትዮሽ ድርጀቶችና ዓለማቀፍ ተቋማት ደግሞ ከጣቢያውና ከባለቤቱ (ኢህአዴግ) ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚጠቅም በማመን፣ ከጣቢያው ጋር እጅና ጓንት ሆነው ይሰራሉ፡፡ ፋና በፕሮግራሞቹ ጥራት፣ ውበትና ማራኪነት እየገነባ ያመጣው ጠንካራ የተደራሽ አድማጮች መሠረት፣ የግሉን ዘርፍ ገበያ ለመቆጣጠር አስችሎታል። የብሔራዊ ጣቢያው (ኢትዮጵያ ሬዲዮ) የመንግስት አፈቀላጤ መሆንና በአሰልቺ የፖለቲካ ትርኪምርኪዎች መታጨቅ ለፋና ሬዲዮ በእጅጉ ጠቅሞታል፡፡
የቀድሞው የአዲስ ዘመን “ድሮና ዘንድሮ” አምደኛ ግርማ ለማ፣ በሥራ ትጋቱ የተጨበጨበለት የፋና ባልደረባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የስሜቱ ተለዋዋጭነትና የማይተነበየው ቁጡነቱ ከብዙዎች ጋር አራርቆታል። የግርማን ዐመል የሚያውቅበት ሙሉጌታ ገሠሠ ብቻ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የግምጃ ቤት ሰራተኛዋ፣ የግርማን ቢሮ አንኳኩታ ወደ ውስጥ ትዘልቃለች፡፡ የምትፈልገውን ከመጠየቋ በፊት ግን አምባረቀባት፤ “ሂጂ ውጪ፤ ዛሬ 13 መሆኑን ረሳሽው?” በማለት፡፡ በሙስሊም ቤተሰብ ውስጥ አድጋ፣ በቅርብ ጊዜ  አዲስ አበባ ለከተመችው ይህቺ ሴት፣ የግርማ “የዕለተ 13 ገደ-ቢስነት” እንዴት ይገባታል?” ግርማ፤ አመሉ ቢያስቸግርም፣ በሥራው ታታሪና በእድሜው የገፋ ስለነበረ፣ የትዕግስት ኮታው ከሌላው ጨመር ይደረግለት ነበር።  
ፋና በአሁኑ ወቅት የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ነውና፣ የድርጅቱ ሰራተኛ ሳለሁ በአሰራሩ ዙሪያ አንዳንድ የታዘብኳቸውን ላጋራ እወዳለሁ፡፡ የአድማጮች ግንኙነት ውስጥ ስሰራ ከተለያዩ የጣቢያው ደንበኞች የሚደወሉ ስልኮችን አስተናግድ ነበር፡፡ አንድ አድማጭ ደውለው ያሉት አይረሳኝም፡፡ “እንደው ግን ምን አድርገናችሁ ነው የምታባሉን---ተጋብተን ተዋልደን ስንት ዘመናት የኖርን ሰዎቾ?” ሲሉ ስሞታቸውን አቅርበው ስልኩን ዘጉት፡፡ ፋና ሬዲዮ ያኔ የማንነት ተኮር ጥላቻ አቀንቃኝ ነበር። የገዢው ፓርቲ ንብረት ነውና ጠያቂ ወይም ተቆጪ አልነበረውም፡፡ የደዋዩን ስሞታ ለባልደረባዬ ነገርኩት፡፡ አፌን እንድዘጋ አስጠነቀቀኝ። “እርሳው” ነው አለኝ። ግርማም ያንኑ ማስጠንቀቂያ ደገመልኝ፡፡ የአድማጮች አሉታዊ አስተያየቶች ከቢሮዬ እንዳይወጡ ተስማምተን ወሰንን። ከጥቂት ቀናት በኋላም ወደ ሌላ ቢሮ ተዛወርኩ።
በነገራችን ላይ የፖለቲካ አመለካከት ፋና ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ጥበበ ታምራት፤ አቋሙን ግንባሩ ላይ የጻፈ ባልደረባችን ነበረ። አንድ ከሰዓት በኋላ ላይ ለአስቸኳይ ስብሰባ ወደ አዳራሽ ግቡ ተባልን። ሙሉጌታ ነበር ስብሰባውን የሚመራው፡፡ ጉዳዩ ደግሞ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ፣ የቅሌት ክስና እሥራትን የተመለከተ ነበር። አቶ ታምራት ላይኔ ማታ በቴሌቪዥን፣ ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ፣ አዲስ እንዳይሆንብንና ፋና ጉዳዩን እንዴት መዘገብ እንዳለበት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተጠራ ስብሰባ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ጥበበ ታምራት ቢሮ ውስጥ ክርክር አነሳ። የፓርቲው አባል የሆኑ የፋና ሠራተኞች ወጥረው ያዙት፡፡ “ነገ መለስም መታሠሩ አይቀርም!” ሲላቸው ነው ከቢሮ ጥለውት የወጡት፡፡
ጦሱ ግን ቀጠለ፡፡ በማግስቱ ጉዳዩ ፕሮግራም መምሪያ አካባቢ እንደተወራና የተከራከረችው የፓርቲ አባል፤ “ከምድረ መኢአድ ጋር ስቋሰል እየዋልኩ--” ብላ እንዳወራች ተሰማ። ከጥቂት ቀናት በኋላም ጥበበ ታምራት ከሥራው ተሰናበተ። አቶ መለስን ተሳድቦ ጣቢያው ውስጥ መሥራት አይቻልም። ፋና፤ ፍትሕን ይዘግባል እንጂ እምብዛም ከፍትህ ጋር አይተዋወቅም።
ቀኑ ቅዳሜ ከሰዓት ነው። ለሆነ ሥራ ቢሮ ገብቻለሁ፡፡ “ስልክ ደውልልን” አሉኝ የስቱድዮ ሰዎች። ተረኛዋ የቴክኒክ ባለሙያ አልመጣችም። ቢያንስ ከአስራ አምስት እስከ ሰላሳ ባሉት ደቂቃዎች ቀድማ ተገኝታ ጠምዳ መጠበቅ ነበረባት። የኦሮምኛ ፕሮግራም የሚጀምርበት ሰዐት አለፈ። ደቂቃዎች ከነፉ፡፡ ሌላ መሓንዲስ (ባጋጣሚ በላይነሽ ተገኘች) እስክትደርስና ፕሮግራሙ እስኪጀመር 18 ደቂቃዎች አለፉ። ከክልሎች አካባቢ “ፋና ምን ሆኖ ነው? መንግስት ሰላም አይደለም እንዴ?” የሚሉ ስልኮች በዝተው ነበር። ጥፋተኛዋ መሃንዲስ ማስጠንቀቂያና የሃምሣ ብር ቅጣት ተጣለባት። የአስተዳደር ኃላፊው ደብዳቤውን ሲሰጣት በአጋጣሚ እዚያው ነበርኩ። ተቀበለችና ፊቱ ላይ በጫጭቃ ጣለችው። ሳያካብድ “እብድ” ብሏት አለፈ።
ዋሲሁን ዋጋው “ዜና ላይ ስምህን አትጥራ እየተባለ” ይገመገማል። ነገር ግን አልተሳካለትም። አንድ ቀን ግን “እባካችሁ ማክሰኞ የእህቴ መልስ አለብኝና ፈቃድ ስጡኝ” አለ፤ ለሮብ ጧቱ አስፈጻሚነት መሆኑ ነበር። የጧት ዜና አስፈጻሚዎች ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በሰርቪስ ይመጣሉና መልስ ላይ አምሽቶና ቀማምሶ አስፈጻሚ መሆን ፍርጃ መሆኑን ያውቀዋል። ፈቃድ ተከለከለ፡፡ እናም ጧት ስቱዲዮ ተገኝቶ፣ ዜናዎቹን ሰራርቶ አስረከቦ፣ እንደተለመደው ስቱዲዮ ውስጥ ጋደም ብሎ አሸለበ። ድርጊቱ የተለመደ ነበረና አንባቢዋ ለአንድ ሰዓቱ ዜና ተቀመጠች። ዋስይሁን ሕልም አለም ውስጥ ነው። ለጥቂት ደቂቃዎች አርዕስተ ዜናዎቹን ካነበበች በኋላ፣ አየሩ ላይ የመጠጥ የመሰለ ቃና ስትምግ፣ መተንፈስ አዳገታትና የድምጽ ማፈኛውን ተጭና ቆም አለች። ቴክኒሻኖቹም ዋስይሁንን ቀስቅሰው አጣድፈዉ በማስወጣት ዜናው ቀጠለ። ለሰባት ሰኮንዶች ፋና ከአየር ላይ ጠፎቶ ነበር። አንባቢዋ ይቅርታ ጠይቃ ነው የቀጠለችው። ዋስይሁን ከሥራው ተሰናበተ። ጣቢያውን ለ18 ደቂቃዎች ያስተጓጎለችው መሓንዲስ፣ የሃምሳ ብር ቅጣት ሲጣልባት፣ ፕሮግራሙ ለሰባት ሰኮንዶች እንዲቆም ሰበብ የሆነ ጋዜጠኛ ተባረረ:: በፋና አስተዳደር ፍርደ-ገምድልነት ተናደድን:: ዋስይሁንን ለመታደግ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመርን። “እረፉ! እሷ የአቶ እንትና ሚስት ነች።” ተባልንና ዓይናችን እያየ፣ ጓደኛችን ከጣቢያው ሲሰናበት ዝም አልን።
ሌላው የፋና ባልደረባ እምባዬም፤ አንድ ቀን ወደ ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ተጠራ። እምባዬ በደርግ ጊዜ ከሱዳን የተመለሰ የቀድሞ ህወሓት አባል ነው። ወደ ሱዳን የጠፋውም በጉርምስና ዘመኑ  በረሃ ውስጥ ሳለ ከሌላ ጓዱ ጋር ዕለታዊ የሆነ የጎረምሳ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። “ወገቤ ላይ የነበረው ሽጉጥ ይባርቅና የእሱን እግር አቆሰለው። እኔም ሁኔታው አስደንግጦኝ  ጠፍቼ ሱዳን ገባሁ። ሱዳን አልጥምህ ሲለኝ፣ ወደ አዲስ አበባ መጣሁና ኑሮዬን ቀጠልኩ።” ይላል እምባዬ፡፡ ከእምባዬ ጋር ሲታገል የቆሰለውና እያነከሰ ትግሉን የጨረሰው ታጋይ ግን “ሆን ብሎ ያደረገው ነው” ባይ ነው። አመራሮች ያመኑት ታዲያ በወቅቱ የየሆዋ ምስክር ከሆነውና ራሱን ከፖለቲካው አግልሎ ይኖር ከነበረው እምባዬ ይልቅ፣ በትግሉ እስከ መጨረሻው የዘለቀውን ጓድ ነበር። እምባዬ “ይሄን ታሪክ ይዘህ እዚህ መስራት አትችልም።” ተባለና እምባዬ፤ ከስራው ተሰናበተ። ሌላ ክስ ግን አልተመሠረተበትም።
ተርቡ ጋዜጠኛ ግርማ ለማ፤ በአመልማል አመራር ደስተኛ አልነበረም። ሃሳቦቹን መገዳደሯ ያበሳጫዋል። ክብረ ነክ አነጋገሯን አይወደውም። ደግነቱ እሱ ለህወሓት ያለውን ጥላቻ እሷ አታውቅም። ሕይወት ወይስ ህወሓት ትሆን ምርኮኛ አድርጋ ያስቀመጠችው? በአንድ ወቅት እሱና የሽያጭ ክፍል ሰራተኞች እንደተሰበሰብን፣ በኢንተርኮም አመልማል አመናጨቀችው። ለግርማ የሽንፈት ሽንፈት ነበር። ስብሰባውን ቶሎ በተነና ECA ቀጠሮ አለኝ - አለ። የፓርቲው አባል የሆኑ ሰራተኞች ከወጡ በኋላ “አየሃት ይችን ወያኔ...” ብሎ  ወጣ። ግርማ ለማ ከዛች ቀን በኋላ ወደ ፋና አልተመለሰም። “ወደ ፋና ዞሬ እንኳን አልሸናም” ብሎ በውክልና ዕቃዎቹንና ጥቅማ-ጥቅሞቹን ተረከበ።
ፋና ለፓርቲው አባላትና ለሌሎች ሠራተኞች እኩል መመዘኛ አልነበረውም። ይሄን ተቀብሎ የመስራት ኃላፊነት የሲቪል ሰራተኛው ነበር። “ያሉህን አድርግላቸው፤ ወይ ሂድ ትተህላቸው” የሚለውን አባባል በየጊዜው ማስታወስ የግድ ይላል። ፋና ለማንኛውም የመንግስት ድንገተኛ ችግር ፈጥኖ ደራሽ ነው። አንድ ቀን ግንቦት 1990 (May 8, በፈረንጆች 1998) ዓ.ም ለምሳ ወጥተናል። ከባልደረባዬ ጥበበ ታምራት ጋር ነን። ውጭ ሳለን ሰበር ዜና ተነገረ። የአመልማል ድምጽ ነው።
የባድመ ጦርነት ተጀመረ። ወደ ግቢ በግርምት ተሞልተን ግቢ ተመለስን። በሶስት የሥራ አመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈትሸን ገባን። አመልማል ወደ ቀድሞ ተሠጥዖዋ ተመለሰች። የፕሮፓጋንዳ አቅሟን ማሳየት ጀመረች። በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ ከአራት እስከ ስድሰት ገጾች ትቸከችክና፣ ስቱዲዮ ገብታ በቃሏ ታወርደዋለች፡፡ “አከርካሪውን......” የሚለውን ቃል በመደጋገም ትታወቃለች። አመልማል  የፕሮፓጋንዳ ሰው ነበረች።
ከሳምንታት በኋላ ነገሮች ተካረሩ። ወደ ጦርነት ምዕራፍ ተገባ። ኤርትራ የለየላት የኢትዮጵያ ጠላት ተብላ ተፈረጀች። ፋናም ትክክለኛ ቀለሙ መታየት ጀመረ። ግቢው ወደ ፖለቲካ ዘመቻ መምሪያ ካምፕ ተለወጠ። በሌላ በኩል ግን ያልተጠበቀ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተቀጣጠለ፡፡ ኤርትራውያን እየታፈሱ ወደ መጠለያ ይወሰዱ ነበር። አገር ተለዋወጠች። ህወሓትና ሕዝባዊ ግምባር ተጣሉ። ምስራቅ አፍሪቃ ተተረማመሠች። ቀውሱ የብዙዎችን በር ማንኳኳት ጀመረ። የኔንም አልማረም። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ከነበረኝ የስራ ቀጠሮ ተመልሼ ቢሮ ገባሁ። አልጋነሽ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ነች። እጆቿን ደረቷ ላይ አጣምራ፣ አይኖቼን በእዝነት አተኩራ ስታየኝ አስተዋልኩ።
አለፍ ስል… ሓብታምነሽ በርህራሄ አይኖች ስታተኩርብኝ… አንዳች ቅዝቃዜ ከጀርባዬ ወደ ታች ሲወርድ ተሰማኝ። ጥሩ ዜና እንዳልሆነ ገምቼ ሳልጨርስ፣ አልጋነሽ እየፈራች እየተባች፣ ወደ መዝገብ ቤት እንድመጣ ጠየቀችኝ። የተጻፈብኝን ደብዳቤ ተቀበልኩ። ደብዳቤው እንደነ ዮናስ አብርሃምና ሌሎቹ ሠራተኞች በግልጽ ኤርትራዊያነትን ጠቅሶ አላስቀመጠውም። ተራ ትችት  ያዘለና  የቃልም ሆነ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ያልተከተለው ደብዳቤ ተቀበልኩ። በዕለቱ ከተሰናበቱት ሶስት ኤርትራውያን ጋር ተቀላቀልኩ። የወቅቱ አስተዳደር አቶ ብርሃነመስቀል በሰጠኝ የሞራል ድጋፍና በውሳኔው ላይ ባሳየው ተቃውሞ አመሥግኜው ወጣሁ። ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ተመልሼ ኑሮ ጀምሬያለሁ። እነሆ ዛሬ ግን የአመልማል ፊርማ አሰናብቶኛል።
ኤርትራዊ ነኝ ብዬ አላውቅም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኤርትራ ውስጥ ማደግ የበለጠ “አክራሪ ኢትዮጵያዊ” ነው የሚያደርገው። ግን ዕድሜ ለእነ አመልማል! ይኼው ኢትዮጵያዊነቴ ጥያቄ ውስጥ ገባ፡፡ በጦርነት ወቅት ብዙ አይነት ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ የኤርትራ ህይወት አስተምሮኛል።  
የፋና የሥራ ቆይታዬ በአሳዛኝና አሉታዊ ገጠመኞች ብቻ የተሞላ አይደለም፡፡ ብዙ ጥሩ ነገሮች ነበሩበት። ጠንካራ የሥራ ባሕል፣ ያልተጻፈ ካይዘን፣ [የማያቋርጥ የመሻሻል ጉዞ continuous improvement)]፣ የሰራተኛው የትብብርና የወዳጅነት ግንኙነት፣ የአመራሩ ቆፍጣናነት… የጣቢያው አይረሴ በጐ እሴቶች ነበሩ። በመጨረሻም፤ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በዓል እያከበረ ለሚገኘው ፋና ብሮድካስቲንግ ሰራተኞችና አመራሩ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ለማለት  እወዳለሁ፡፡ ቸሩን ሁሉ እመኛለሁ!!


Read 9366 times