Print this page
Saturday, 30 November 2019 13:18

ራፋ (ፈውስ) ክሊኒክ ሥራ ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  በየወሩ ለ90 ህሙማን ነፃ ህክምና ይሰጣል
                     
              ፓስተር ዮሴፍ እውነቱ በተባሉ ባለሀብት የተከፈተው ራፋ ክሊኒክ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ ክሊኒኩ በአገራችን በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው የአዕምሮ ሕሙማን በቂ ሕክምና ለማግኘት የሚችሉበትን ዕድል በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በየወሩ ለ60 የውስጥ ደዌና ለ30 የአዕምሮ ታማሚዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ራፋ ክሊኒክ በውስጥ ደዌ ሃኪሞች፣ በአዕምሮ ሃኪሞችና ሳይካቲሪስቶች እንዲሁም በተሟላ ላብራቶሪ የተደራጀ እንደሆነና ለሕሙማን ሁሉን አቀፍ ሕክምና በአንድ ቦታ ላይ መስጠት እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡ ሰሞኑን ተመርቆ ሥራ የጀመረው ክሊኒኩ፣ ታማሚዎች ከሚኖሩበት ወረዳ አቅማቸው ደካማ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዘው ሲቀርቡ ነፃ ሕክምናውን እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡
የክሊኒኩ ባለቤት ፓስተር ዮሴፍ እውነቱ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በርካታ የአዕምሮ ሕሙማን በቂ ሕክምና ማግኘት የሚችሉበት ዕድል በማጣታቸው፣ ለተለያዩ ከፍተኛ የጤና ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ ሕሙማኑ በአንድ ስፍራ ላይ የተቀናጀ ሕክምና ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ በሙያው በቂ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ሕክምናውን ማግኘት እንዲችሉ ክሊኒኩን መክፈታቸውን ተናግረዋል። አንድ የአዕምሮ ታማሚ፤ ከአዕምሮ ሕክምናው ሌላ ሌሎች የውስጥ ደዌ ሕክምናዎች ሊደረጉለትና ጤናው የተሟላና የተስተካከለ ሊሆን ይገባል ያሉት ፓስተር ዮሴፍ፤ ይህንንም ፈውስ የሚል ትርጓሜ ባለው “ራፋ” ክሊክ እውን ለማድረግ መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ክሊኒኩ ከራስ አምባ ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኝ ሲሆን ለአዕምሮ ሕሙማንና ለውስጥ ደዌ ታካሚዎች ሕክምና ለመስጠት መዘጋጀቱ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

Read 3718 times