Saturday, 30 November 2019 13:15

“ለጤናዬ እጠነቀቃለሁ” የጤና ኤክስፖ ሰኞ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

     - የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማት ይሳተፋሉ
             - ‹‹ለ30 ሺህ ሰዎች ነፃ የምክር፣ የምርመራና የህክምና አገልግሎት ይሰጣል››
              
             በአዲስ አበባ የግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማህበር አዘጋጅነት የሚካሄደው “ለጤናዬ እጠነቀቃለሁ” የጤና ኤክስፖ የፊታችን ሰኞ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል፡፡ እስከ ረቡዕ ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚዘልቀው ኤክስፖ ላይ በቀን ለ10ሺህ ባጠቃላይ ለ30 ሺህ ሰዎች ነፃ የምክር፣ የምርመራና የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤፍራታ አረጋ ባለፈው ረቡዕ ቦሌ በሚገኘው ማርሴን ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የጤና ተቋማት በሚሳተፉበት በዚህ ኤክስፖ፤ ከነፃ የጤና ምርመራ፣ ምክርና ህክምና በተጨማሪ በጤና ጉዳይ ላይ ኮንፍረንስ እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡
የጤና ኤክስፖው በዋናነት ሦስት ትልልቅ አላማዎች ያሉት ሲሆን እነሱም፡- በኤክስፖው ላይ ለሚታደሙ የውጭ ሀገራት ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን በጐ ሀገራዊ ተሞክሮ ማስተዋወቅ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ የግል ጤና ተቋማትን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም የግል የጤና ተቋማትን በማነቃቃትና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በማሳየት፣ ወደፊት ለዓለምአቀፍ የሜዲካል ቱሪዝም ገበያን ለመቀላቀል የሚያስችል ተሞክሮን ማዳበር ናቸው፡፡
በኤክስፖው ላይ የአገር ውስጥና የውጭ ሆስፒታሎች፣ የመድሃኒትና የህክምና እቃ አምራቾች፣ ጤና ላይ የሚሰሩ አማካሪዎችና ከጤና ጋር የተገናኙ ማህበራት ይሳተፋሉ፡፡ ከህንድ አፖሎ ሆስፒታልን ጨምሮ ከ20 በላይ ሆስፒታሎች እንዲሁም የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የደቡብ አፍሪካና የቻይና የጤና ተቋማት በሚሳተፉበት በዚህ ኤክስፖ፤ የጤና ታላላቅ ፕሮፌሰሮችና ባለሙያዎች ይታደሙበታል ተብሏል፡፡
የጤና ምርመራና ህክምናን በተመለከተም ማንኛውም ጤና ነክ ምክርን ጨምሮ የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰር፣ ከአንገት በላይ (የአይን የጆሮና ጥርስ)፣ የኤኮኮርዲዮግራፊ፣ የኦርቶፔዲክ የአጥንት ምርመራና ህክምና እንደሚሰጥ ዶ/ር ሙሴ ቪክቶሪዮ ገልፀዋል በጽኑ ታመው አስቸኳይ ህክምና ማድረግ ለሚገባቸው አምስት ሰዎችም የልብ ቀዶ ህክምና እንደሚደረግ ተናግረዋል:: ለህክምናውም 50 ያህል ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ማህበሩ ማዘጋጀቱን ወይዘሮ ኤፍራታ ጠቁመዋል፡፡

Read 3650 times