Saturday, 07 December 2019 11:44

የታሰሩ አመራሮቹና አባላቱ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ አብን ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   ከሰኔ 15 የባለሥልጣናት ግድያ ጋር ተያይዞ የታሰሩ 15 ያህል አመራሮቹና አባላቱ እስር ጉዳይ ፖለቲካዊ መሆኑን የገለፀው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ አመራሮቹና አባላቱ በአስቸኳይ እንዲፈቱና እውነተኛ ወንጀል ፈጻሚዎች ተጣርተው ለሕግ እንዲቀርቡ ጠየቀ፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ክርስቲያን ታደለና የጽ/ቤት ሃላፊው በለጠ ካሳን ጨምሮ በ15 አባላቱ ላይ ከግድያው ጋር በተያያዘ የተመሰረተውን ክስ ያጣጣለው አብን፤ ‹‹ክሱ ንቅናቄያችን ለማዳከም ተብሎ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ክስ ነው›› ብሏል፡፡
የሰኔ 15ቱ ግድያ በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣና ለአማራ ሕዝብ የተሻለ ተቆርቋሪ የሆኑ መሪዎች የታጡበት አሳዛኝ ድርጊትና በታሪክም ጥቁር ወንጀል ሆኖ ተመዝግቦ የሚቀመጥ መሆኑን በመግለጫው ያስረዳው አብን፤ መንግስት ትክክለኛ የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
የአባሎቹና አመራሮቹ እስር ከድርጊቱ ጋር የማይገናኝና ፖለቲካዊ መሆኑን በመግለጽም፤ አባላቱ በአስቸኳይና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱለትም ለመጨረሻ ጊዜ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
አመራሮቹና አባላቱ የማይፈቱ ከሆነም በቀጣይ የቤት ውስጥ አድማን ጨምሮ በተለያዩ የሰላማዊ ትግል መንገዶች በመንግስት ላይ ጫና እንደሚፈጥር ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ አቃቤ ሕግ ባለፉት አምስት ወራት ሲያደርገው የነበረውን ማጣራት አጠናቆ፣ በቅርቡ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ አብን በዚህ መግለጫው፤ ለቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎችን በመመልመል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁሞ፣ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ውስጥ መካሄድ እንዳለበትም አስታውቋል፡፡   

Read 1153 times