Saturday, 07 December 2019 11:53

ጠ/ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማታቸውን ማክሰኞ በኦስሎ ከተማ ይቀበላሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   ከኖርዌይ ጠ/ሚኒስትርና ንጉስ ጋር ይወያያሉ

             100ኛውን የኖቤል የሠላም ሽልማት ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የፊታችን ማክሰኞ ህዳር 30 በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ በመገኘት ሽልማታቸውን ይቀበላሉ፡፡
ከሁለት ወር በፊት (መስከረም 30 ቀን 2012) ጠ/ሚኒስትሩ በተለይ ለሁለት አስርት አመታት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ የጨለማ መጋረጃ የሚገፍ ሰላም በሁለቱ አገራት መካከል በማውረዳቸው የ2019 የኖቤል የሠላም ሽልማት አሸናፊነታቸው መበሰሩ ይታወቃል፡፡
የፊታችን ማክሰኞ በኖርዌይ ኦስሎ በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ ሽልማቱ የሚበረከትላቸው ጠ/ሚኒስትሩ፤ በሥነሥርዓቱ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በጊዜ መጣበብ ምክንያት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ግን ቃለምልልስ እንማያደርጉ ተገልጿል፡፡
በኖርዌይ ከሚከናወነው የሽልማት ስነሥርዓት ጐን ለጐን፣ ከሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ኤርና ሶልቤርግ እና ከንጉስ ሃራልድ 5ኛ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉና የሀገሪቱን ፓርላማ እንደሚጐበኙ ታውቋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ይህን በአለም ታላቅ ክብር ያለውን ሽልማት ያገኙት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ሠላም በማውረዳቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም በአካባቢው ሀገራት መካከል ሠላማዊ ግንኙነት እንዲኖር በማድረጋቸው እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ለተሻለ የወደፊት ህይወት ተስፋ እንዲሰንቁ በማነሳሳታቸውም ጭምር የተበረከተላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 11306 times