Saturday, 07 December 2019 11:55

‹‹የፀረ ሽብር ህጉ ሠለባዎች›› ጥያቄያቸውን በዝርዝር ለመንግስት አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   በአንድነት ፓርክ ውስጥ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸውም ጠይቀዋል

          ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑት በፖለቲካ እስር ምክንያት የፀረ ሽብር ህጉ ሠለባዎች የነበሩ ግለሰቦች ከመንግስት የሚፈልጉትን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፤ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣቸው ዘንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው አመት ጥር ወር ከአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ጋር ስለደረሰባቸው ጉዳትና መንግስት ሊያደርግላቸው ስላቀደው ድጋፍ የተነጋገሩ ቢሆንም እስከዛሬ አለመፈፀሙን የጠቆሙት የፀረ ሽብር ህጉ ሠለባዎች፤ መንግስት አሁንም አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድንጋጌዎችን መነሻ በማድረግ፤ በአለማቀፍ ህግ መንግስትን ለመክሰስ መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት አመታት በፀረ ሽብር ህጉ ምርመራ ሲደረግባቸው በሃይልና በአስገዳጅነት የሠጡት ቃል፣ አሻራና የመሳሰሉት ሰነዶች በይፋ እንዲሠረዙላቸው፤ መንግስት ይቅርታ በጠየቀው መሠረት ለተፈፀመባቸው ግፍ በግልጽና በሠነድ እውቅና እንዲሰጣቸውና ያለፉት ማህደሮች መምከናቸውን እንዲያረጋግጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በወቅቱ ንብረት ሃብታቸውን አጥተው ቤተሰባቸው ተበትኖ ለከፍተኛ ችግርና እንግልት ተዳርገው እንደነበር በማመልከትም መጠለያ እንዲሠጣቸውም ጠይቀዋል፡፡
በምርመራ ወቅት ለአካል ጉዳት፣ ለጤና መቃወስ የተዳረጉም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የህክምና አገልግሎት በነፃ እንዲያገኙ ይደረግ ዘንድ፣ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እንዲደረግ፣ በምርመራ ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶች እንዲመለሱላቸው፣ የታገዱ ንብረቶች እንዲለቀቁላቸው… ከጠየቋቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሽብር ለተፈረጁ ሁሉ በውጭ መንግስታት የተለገሰው የዕርዳታ ገንዘብ በግልጽና ያለ አድልኦ ለተጐጂዎች፣ ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለተወካዮቻቸው በአጣፋኝ እንዲሰጥና ተጐጂዎች በዘላቂነት ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም በፀረ ሽብር ህጉ ሰለባ ሆነው ህይወታቸው ያለፈ ሟቾች አጽም ከያለበት ተሰባስቦ በክብር የሚያርፍበት ሁኔታ እንዲመቻች፣ ገዳዮች በህግ እንዲጠየቁ ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት አመታት በፀረ ሽብር ህጉ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችም ሆኑ በህይወት ያሉ ተጠቂዎች ታሪካቸው ተጽፎ በብሔራዊ ቤተመንግስት (አንድነት ፓርክ ውስጥ) መታሰቢያ ሃውልት እንዲሠራላቸውም ጠይቀዋል - በመግለጫቸው፡፡
በአጠቃላይ “የፀረ ሽብር ህጉ ሠለባዎች” መንግስት የወሰደባቸውን ጤናቸውን፣ ክብራቸውንና ቁሣዊና ሞራላዊ ሃብታቸው እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል፡፡

Read 9497 times