Saturday, 07 December 2019 12:10

‹‹ዝም ብንል ብናደባ ዘመን ስንቱን አሸክሞን የጅልነት እኮ አይደለም እንድንቻቻል ነው ገብቶን››

Written by 
Rate this item
(9 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን፣ በአንድ ጫካ ውስጥ፣ አንድ ነብርና አንድ አውራሪስ ይኖሩ ነበር፡፡
በጫካው ውስጥ አንዳች የሚንቀሳቀስ ፍጡር እስኪጠፋ ድረስ፣ ሁሉን በልተው፣ ሁሉን ተቀራምተው ጨረሱት፡፡ ዛፍ ቅጠሎም አልቀረም፡፡  ድሮ፣ ሁለት ሰፋፊ ጫካዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ፣ ግን ከአንዲት ቅርንጫፍ በስተቀር፣ የእፅዋት ዘር ሁሉ ተበልቶ አልቋል፡፡
የሚበላ የሚቀመስ አጡ፡፡ የሚጠጣ ጠብታ ውሃ ጠፋ፡፡ ስለዚህ አንድ መላ መመታት ነበረበት፡፡
አንድ ጠዋት አያ ነብሮ፡-
“አያ አውራሪስ?” አለው፡፡
“እህ አያ ነብሮ - ምን ልርዳህ?”
“ችግሩ የጋራ ነው›› አለ አያ ነብሮ፡፡
“ምን ዓይነት የጋራ ችግር?”
“የኸውልህ አያ አውራሪስ፤ ነጋ ጠባ ለምግብነት የምንገለገልበትና ምግብ የምናገኝበት ጫካ፣ እያደር እየመነመነ መጣ፡፡”
“ታዲያ ምን ዘዴ እንፍጠር? እንዴትስ እናድነው?”
“አንድ መላ አለኝ በበኩሌ”
“እኮ ምን ዓይነት መላ?”
“እነግርሃለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን፣ እንማማል!”
“እንማማል?”
“አዎን እንማማል”
“እሺ ምን ብለን እንማማል?”
‹‹ከዚህ ጫካ አንዳችን ካለአንዳችን ፍቃድ አንዲት ቅጠል እንኳ ላንበጥስ እንማማል”
“ከሕጉ ወይም ከመሀላው ውጪ ቅጠል በጥሰን ብንገኝስ?”
“ወንጀሉ በልጅ ልጆቻችን ይድረስ!”
‹‹ይድረስ፣ ይድረስ›› ተባብለው በመሀላው ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በቃ፣ የጠፋው ጫካ ተመልሶ ይለመልማል፡፡ ጥንቸልና ሚዳቋ ይበረክታል አሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ ሲታይ ግን፣ ባሰበት እንጂ አልተሻለውም፡፡ ለካ፣ አንዱ ከሌላው እየተደበቀ ቀን ከሌት መብላት ጀምሯል፡፡
አንድ ቀን አውራሪስ፣ አንዲት ቅጠል አግኝቶ እየተንጠራራ ለመቀንጠስ ሲሞክር፣ ድንገት ከኋላው ነብር ከተፍ አለ፡፡ አያ ነብር፣ የአውራሪሱን ገላ ሲያይ፣ ጎመዠ፡፡ ሳያመነታ ቸር ብሎ አውራሪሱ ላይ ጉብ ለማለት፣ አንገቱ ላይ ጥርሶቹን ለመትከል ተወነጨፈ፡፡
ሆኖም አውራሪሱን ለማነቅ በጣም ከመጣደፉ የተነሳ፣ አልፎት እቀንዱ ላይ በሆዱ አረፈና አንጀቱ ዝርግፍ አለ፡፡ ይሄኔ፣ አያ ነብሮ፤ መሬት ላይ ወድቆ እያቃሰተ ተናገረ፡፡
“ምነው አያ አውራሪስ፤ ቅጠል ላንነካካ ተማምለን?” ቅጠል የነካ፣ ተባብለን? የሚወጋ ይውጋው ተባብለን? በእርሱና በልጁ ልጆቹ ይድረስ ተባብለን?››
“ያንተ አያትና ቅድመ አያት፣ ከኔ አያት፣ ቅድመ አያት ጋር ምን እንደተማማሉ ይታወቃል?›› አለ አውራሪስ፡፡
*   *   *
በእርግጥም የማይተማመን ባልንጀራ፣ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል ተብሏል፡፡ ምንጩ ጥርጣሬ ነው፡፡ መሠረቱ ሥጋት ነው፡፡
ዛሬ እገሌና እገሌ፣ እጅና ጓንት፣ ፈትልና ቀሰም ናቸው፡፡ አገሪቱን ቀጥ አድርገው ይመሯታል እየተባለ እየተደመደመ ሳለ፤ የቱም ሳይሰምር ‹‹ውይ ተለያዩ’ኮ›› የሚል መረጃ ይወጣል፡፡ ‹‹ዛሬ፣ እጅና ጓንት ናቸው ማለት ይቻላል›› ማለት ሊኖርብን ነው - የነገውን ከጠረጠርን፡፡
ዱሮ፣ የሶማሌ ሬዲዮ እንዲህ ዓይነት ጠርጣራ አባባሎች ነበሩት ይባላል፡፡ በአስረጅነት እንጥቀስ፡-  
“የሶማሊያ ምክር ቤት፣ ዛሬ በሞቃዲሾ ከፍተኛ ውይይት ሲያካሂድ ዋለ፡፡
ነገም ስብሰባውን የሚመሩት፣ የአብዮቱ ከፍተኛ መሪ ጄኔራል ዚያድ ባሬ ናቸው ለማለት ያስደፍራል” የሚል የሬዲዮ ዜና አይጣል ነው፡፡
የፓርቲዎች መብዛት ጥቅምም ጉዳትም አለው፡፡ ጥቅሙ ህዝቡ አማራጭ እንዲያገኝ፣ ቢሻው እንዲገባ፣ ባይሻው እንዲተው ነው፡፡ አንድም ደግሞ ሕዝቡ ሃሳቡን ለማብላላት በቂ ትንፋሽ፣ ይዞ ረዥም መንገድ ለመጓዝ የሚያስችል አቅም (ፊያቶ) እንዲኖረው ይበጀዋል:: ከቶውንም አንዳች ለውጥ ተከሰተ ሲባል፣ አዲስ ልብስ እንደተሰፋለት ልጅ ፍንድቅድቅ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ለውጥ ሁሌም ይኖራል፡፡ (Everything Changes except the law of change እንዲሉ) እያንዳንዱ ነገር ተለዋጭ ነው፣ ከለውጥ ህግ በስተቀር፡፡
አዳዲስ ለውጥ ሲከወን ባየን ቁጥር እንደምንታዘበው፣ ከዚህ ጋር ለረዥም ጊዜ ባየነው አካሄድ ውስጥ፣ የሃይማኖቶች ብዛት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ብዛት እና የከበር - ቻቻ ቤት ብዛት ሞቅ ደመቅ እያለ ነው፡፡
በአንፃሩ ትምህርት በነበረበት - ባለበት ላይ ነው፡፡ ግብረገብነት ባለበት ላይ ነው፡፡ ጤና ግን የተባባሰ ይመስላል፡፡ የወላጆችና የመምህራን ግንኙነት አወዛጋቢ ነው፡፡ የተቃዋሚዎች ነገረ ሥራ ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል፡፡
ምርጫው ደግሞ እየደረሰ ነው፡፡
የአሜሪካ መራጮች፣ ምርጫን በዓለም ላይ ለማስፋፋትና ዲሞክራሲን ለማስፈን ከአለም ዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ ውቅያኖስ አቋርጠው ይሄዳሉ፡፡ የምርጫ ሳጥን ውስጥ ምርጫቸውን ለመክተት ግን እስከምርጫው ሳጥን ድረስ እንኳ መንገድ ማቋረጥ አይችሉም፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሳይሻል አይቀርም፡፡
“ዝም ብንል ብናደባ፣ ዘመን ስንቱን አሸክሞን
የጅልነት እኮ አይደለም እንድንቻቻል ነው ገብቶን”
ከፀጋዬ ገ/መድህን (ማነው ምንትስ?)
ዛሬም ብዙ የለውጥ ዕድል እንዳመለጠን አንዘንጋ፡፡ ገና ብዙም ያመልጠናል፡፡ ምክንያቱም ከትላንት ያለመማር አባዜ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተጫጭኖናል፡፡ አዛውንት ምሁሮቻችንንና አበው የዕውቀት ካህኖቻችንን ተንከባክበን የጠዋት ልህቅናቸውን ለመጋራት እንጣር፣ እንትጋ፣ ለትውልድም እንብቃ!!


Read 13147 times