Saturday, 07 December 2019 12:26

ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በኋላ…?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   -  ለ6 ወራት ከዘለቀው ‹‹የዴስትኒ ኢትዮጵያ›› ውይይት ምን ተገኘ?
         - ከሂደቱ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ምን ያተርፋሉ?
         - የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ድባብ ምን ያህል ይለውጣል?


         ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በኋላ ‹‹ምን እጣ ፈንታ ይኖራታል›› በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ 50 የተመረጡ የፖለቲካ አመራሮችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ላለፉት ስድስት ወራት በሚስጥር ውይይት ሲያደርጉ መክረማቸው ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡
‹‹ደስቲኒ ኢትዮጵያ፡- አራት ሴናሪዮዎች ኢትዮጵያ በ2032›› በሚል ርዕሰ የውይይት ፕሮጀክት ለሦስት ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን ተወያዮቹም ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋና ንጋት ለማምጣት ተስማምተዋል፡፡
ውይይቱ ምን መልክ ነበረው? በምን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር? በቀጣይስ 50ዎቹ ሰዎች ምን ሃላፊነት አለባቸው? በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴና ናፍቆት ዮሴፍ በውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩት የተወሰኑትን እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


             ‹‹ሁላችንም የንጋት ሁኔታ ላይ ተስማምተናል››
                    ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

          ከዚህ በፊት አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት አይነት ችግር ውስጥ የገቡ አገሮች፣ ለምሳሌ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉት… ከነበሩበት እንዴት ወጡ? የሚለውን መነሻ በማድረግ፣ እውነታውን በማሳየት እኛ ከዚህ ወዴት እንሂድ? በሚለው ላይ ሲወያይ የቆየ መድረክ ነው፡፡ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ተነስተን ወደፊት ብንሄድ… ከ20 ዓመት በኋላ ልንደርስባቸው የምንችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ያንን በተለያየ ዘዴ መመልከት የመቻል ውይይት ነው። በቀጣይም ከትላልቅ ባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ተመሳሳይ ውይይቶች ይካሄዳሉ። እነዚህ 50 ሰዎች ወደ የመጡበት ድርጅትና ማህበረሰብም ሄደው፣ ያመኑበትንና የደረሱበትን ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። ከንጋት ውጪ ሌላው የትም እንደማያደርስ እነዚህ ሰዎች አምነዋል፡፡ ይሄን ያመኑትን ነው ለሌላው ማሳመን የሚጠበቅባቸው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ መቀጠል የለበትም ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ፣ ፍቃደኛ የሆነ ነገር ግን ደካማ የሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ነው አገሪቷ ሊኖራት የሚችለው፡፡ መንግስቱ ደካማ ከሆነ ደግሞ በርካታ የውጭ ሃይሎችና የአካባቢው አሸባሪ ሃይሎች ይገቡበታል። በርካታ ችግር ይፈጠርበታል፡፡ የማስፈጸም አቅም የሌለው ሰባራ ወንበር የተባለው አይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው። በሌላ በኩል፤ መንግስት እርምጃ ሊወስድ ይገባል፤ ያ የሚጠየቀው እርምጃ ቢወሰድ ደግሞ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት እንመለሳለን፡፡ የመጨረሻው አማራጭ ነገሮችን ቀስ በቀስ እያጠነከሩ ከተሄደ ወደ ንጋት እንሄዳለን የሚል ነው፡፡ ሁሉም የተስማማው ንጋት በሚለው ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ እዚያ ለመድረስ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ መስማማት ተችሏል፡፡ በቀጣይ በየክልሉና በየአካባቢው ስብሰባዎች ይደረጋሉ፡፡ እኛም ባለንበትና በተወከልንበት ተቋም ያመንንበትን እንድናሳምን ይጠበቅብናል፡፡


____________________


                    ‹‹ውይይቱ ተቀራርቦ ለመስራት ጠቃሚ ነበር››
                        አቶ ግርማ ሰይፉ (የኢዜማ አመራር)

           በመድረኩ በፖለቲካ አቋምም በአስተሳሰብ የተለያየን ሰዎች ነን በአመዛኙ የተገናኘነው:: ወይም ተቀራርበን ባለመነጋገር ዝም ብሎ በግምት ‹‹እሱ እንዲህ ነው የሚያደርገው፣ እሷ እንዲህ ነው የምታደርገው›› በሚል ጎራ ለይተን፣ ምንፋተግ የነበርን ሰዎች ነን በዚህ ሂደት ውስጥም የነበረ ነው፡፡ ይሄንን ለማቀራረብ ሃላፊነቱን ወስደው ሲሰሩ የነበሩት የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ቡድን አባላት ‹‹እገሌ አፍራሽ ነው፤ እገሌ ጠቃሚ ነው››፡፡ ከሚል መንፈስ ራሳቸውን አውጥተው፣ ‹‹ሰዎች ተቀራርበው ቢነጋገሩ ለውጥ ይመጣል›› በሚል እምነት ነው ውይይቱን ያዘጋጁት፡፡
‹‹አሁን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ እንደ ሶሪያ ትሆናለች›› የሚል ሀሳብ ማቀንቀን ቀላል ነው፡፡ ከዚህ አይነት ሃሳብ መውጣቱ ነው ከባድ፡፡ ነገር ግን በውይይታችን ከዚህ አይነት ሃሳብ መውጣት አለብን… እንዴትስ ነው የምንወጣው? አገሮች እንዴት ከዚህ ወጡ? ብሎ በተለየ መንገድ የማሰብ ሂደት ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ‹‹እነዚህ ሰዎች አገራችንን ወደፊት ለማሻገር ትራንስፎርሜሽናል አመራር ይፈልጋሉ›› በሚለው ከተስማሙ በኋላ አለም ላይ እንዴት ነው አገራት ትራንስፎርም ያደረጉት ብለው ሲያጠኑ ሲመራመሩ፣ ትልቁን ጉብዝና የሚጠይቀውና ትራንስፎርም የሚያደርገው አንድ ሰው ከማይግባባው፣ በአቋም ከማይታረቀው ሰው ጋር መነጋገርና መስማማቱንም በሰለጠነ መንገድ ማስተላለፍ ሲችል ነው፤ የሚል መስማማት ላይ ነው የተደረሰው፡፡ በዚህ የውይይት ሂደት ለምሳሌ አንድም ሰው ኢትዮጵያ አታስፈልግም ያለ የለም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በምትባል አገር  ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል ማለት ነው። ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ላይ ስምምነት ከፈጠርን በኋላ ኢትዮጵያኖች ከ20 አመት በኋላ የት እንደርሳለን ብለን ስናስብ፣ በሚቀጥለው 20 አመት ውስጥ የምንደርስበት ቦታ የሚወሰነው በፈጣሪ ቸርነት አይደለም፤ እያንዳንዳችን በምናደርገው በምንወስደው አማራጭ ነው:: አሁን ምን እያደረግን ነው የሚለውንም አይተናል። አንዳንዶቻችን ‹‹አፄ በጉልበቱ›› ተብሎ የተለየውን ሥርዓት ሊያመጣ የሚችል ድርጊት እየሰራን ነው፤ አንዳንዶቻችን የፉክክር ቤት ይመስል ያልሆነ ፉክክር ውስጥ ገብተናል፤ አንዳንዶቻችን ደግሞ በሰባራ ወንበር የመሰልነውን ማለትም መንግስት ያለን እየመሰለን ነው፤ ግን መንግስት ቅን ልቦና ሳያጣ በትክክል የሚሰራ አልሆነም፡፡ ሳር ብታስቀምጥበት የሚወድቅ ወንበር አይነት ነው የሆነው፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ የሆነ ሀሳብ እንኳ ብንናገር፣ በቀላሉ አገር ሊፈርስ ይችላል በሚል ነው የተነጋገርነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን እየታየ ያለው የሪፎረም አካሄድ ከተጠናከረ ንጋት ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ንጋት እንዲመጣ ሃላፊነታችን መወጣት አለብን ማለት ነው፡፡ በአቋም መግለጫችን እንዳስቀመጥነው፤ ለቀጣይ ወደ ንጋት ለመሄድ፣ ሌላውንም ወደዚህ ለመምራት ነው ቃል የገባነው፡፡
በቀጣይም እንዲህ ያለው ውይይት ይኖራል፡፡ እዚህ ላይ የተሳተፍነው 50 ሰዎች ነን። እኛ ራሳችንን ‹‹ከበጥባጮቹ ዋነኞቹ ነን›› ብለን ነው የወሰድነው፡፡ ስለዚህ እኛ ወደ ሥርዓቱ ከገባን፣ ሌሎቹ ተከታዮቻችን ወደ ሥርዓቱ ይገባሉ እናስባለን፡፡ ይሄ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ድባብና ሁኔታ ይቀይረዋል፡፡ የፖለቲካ አቋማችንን እንቀይራለን ማለት አይደለም፤ የፖለቲካ አቋማችንን የምናራምድበት መንገድ ይቀየራል ማለት ነው፡፡


__________________________                  ‹‹የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይቻላል የሚለውን አስተምሮናል››
                          ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (የአብን ሊቀመንበር)


            ስብሰባውን ስናደርግ ጉዳዩ ለሕዝብ እንዳይገለጽ ተማምነን ነው የገባንበት፡፡ በአጠቃላይ ውይይቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተመራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ቀድሞ በተጠና መንገድ ሲመራ ነበር፡፡ በጣም ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ የውይይት ዘዴ የተለያዩ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ ነበር፤ በኋላ ላይ የግለሰቦችን ሃሳብ መሰረት ከማድረግ የአገር እጣ ፈንታ ላይ አተኩሮ ሃሳብ ወደ መስጠት ነው የተሄደው፡፡
ወደፊት ምን ሊያጋጥመን ይችላል? ምን ልንፈጥር ይገባል? የሚለው ላይ አተኩረን እንድንሰራ ነበር የቤት ስራ የተሰጠን፡፡ እሱንም በጥሩ ተወጥተነዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሃሳብን በነፃነት ያለ ፍራቻ ማቅረብና ምንም ሃሳብ ቢቀርብ ደግሞ ያለመደንገጥን አይተንበታል:: ከዚህ ሂደት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚጠቅም ነገር አግኝተናል ከተባለ፣ ምንም አይነት ሃሳብ፣ አመለካከት አቋም ቢኖር፣ ቁጭ ብሎ መነጋገር እስከተቻለ ድረስ የጋራ መውጫ መንገድ፣ የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይቻላል የሚለውን አስተምሮን አልፏል፡፡
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ የሴናሪዮ ቡድን አባላት፤ አላማቸው የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከ20 አመት በኋላ ምን መሆን አለበት የሚለውን መለየት ነው፡፡ በዚያ ሂደት ውስጥም አራት እጣ ፈንታዎችን ለይተናል፡፡ ከአራቱ እጣ ፈንታዎች ውስጥ ሶስቱ በጣም ጥሩ ያልሆኑ፣ ኢትዮጵያ በእነዚያ መንገድ ከሄደች ያልሆነ ሁኔታ ውስጥ ልትወድቅ የምትችልበት የአምባገነናዊ ሥርዓትና የመበታተን እድሎችም ሊያጋጥማት ይችላል የሚሉ ናቸው፡፡ አራተኛው ግን በመስማማት ወደፊት ከተራመድን፣ የሕዝቦች የኑሮ ደረጃ የሚሻሻልበት ፍትህ የሚሰፍንበት፣ ዴሞክራሲ የሚያብብበት… አጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ስር የሰደዱ ችግሮቻቸውን ፈትተው የተረጋጋች፣ የተሻለ ልዕልና ያላት አገር ላይ ትደርሳለች የሚል ነው። እንግዲህ ይሄ እንዲሆን ከኛ ምን ይጠበቃል የሚለውንም ተወያይተናል፡፡ በዋናነት አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን፣ የድጋፍ መሰረታችን የሆነው ሕዝብ ‹‹በጎ ሴናሪዮ›› እንዲከሰት ያንን ራዕይ የማሳየት ሃላፊነት ነው ያለብን፡፡ ነገር ግን ይሄ ሂደት ቀጣይ ሂደቶችን ሊጋብዝ ካልቻለ ብዙ ትርጉም የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን በተነሳንባቸው ሴናሪዮዎች ዙሪያ ተመስርቶ ሁሉንም አካታች የሆኑ ብሄራዊ ንግግሮችና ውይይቶች መጀመር አለባቸው፡፡ ‹‹የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ሴናሪዮ›› አባላት ስራቸውን በሚገባ ሰርተዋል ፕሮጀክቱን ያስተባበሩት ወንድም እህቶቻችንም በከፍተኛ ሁኔታ ሙያዊነት የተሞላበት ትልቅ ውጤት ያለው ስራ ሰርተዋል። ነገር ግን መንግሥትንም ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት፤ እነዚህን ተስፋዎች በመተግበርና ወደፊት አሻግሮ አገሪቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትደርስ ብዙ መስራት አለባቸው:: ውይይቱ በራሱ ግብ አይደለም፤ ወደ ቀጣይ ልንሸጋገርባቸው የምንችላቸውን ውይይቶች ለማውጣት እንደ መነሻ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡

____________________________


                       ‹‹ሁሉም ዕጣ ፈንታውን እንዲወስን ምርጫ ያቀረበ ሀሳብ ነው››
                            አርቲስት አስቴር በዳኔ


             ይሄ ስብስብ እስከ ዛሬ ድረስ በአገራችን የተለያየ ዓላማና ሀሳብ ያላቸው ፓርቲዎች፤ እነሱ በሚያራምዱት ሀሳብና በተከታዮቻቸው መካከል ከፍተኛ ውጥረት በመፍጠር በአገሪቱም ቀውስ የተፈጠረበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ይሄ ስብስብ ይህን ውጥረት ለማርገብና በጎ ተፅዕኖ በአገር ላይ ለመፍጠር ሲባል የተሰራ ሥራ ነው:: አየሽ… ከዚህ ቀደም አንዱ ከአንዱ ጋር አብሮ ቁጭ ብሎ መነጋገር ቀርቶ አንዱ ስለ አንዱ መስማትም ማየትም የማይፈልግበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን እነዚህ ቡድኖች “ጫፍና ጫፍ ቆመን አገር ውድቀት ውስጥ ከምትገባ፣ ለምን ተቀራርበን የመፍትሄ አካል አንሆንም” በሚል ተሰባስበው እየመከሩ ያሉበት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡
እንግዲህ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነት የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩ አገራት ችግራቸውን የፈቱበትን መንገድ ለመማር ከተለያዩ የውጭ አገራት ምሁሮች ግንኙነት በማድረግ ጽንፍ ለጽንፍ የቆሙና የተለየ ሀሳብ ያላቸው ግለሰቦችና ፓርቲዎች በቡድኑ እንዲካተት ከተደረገ በኋላ ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ መስራት ተጀመረ፡፡ በቅርቡ በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ የሆነውም 6 ወራት ከተሰራበት በኋላ ነው፡፡
በድብቅ ውስጥ ውስጡን ሲሰራ የነበረው፣ ቀኑ እንዳልደረሰ ልጅ ሀሳብና ሥራው እንዳይጨነግፍ መልክና ቅርጽ እስኪይዝ ድረስ ተብሎ ነው፡፡ በመጀመሪያ ስብሰባው የተካሄደው አርባ ምንጭ ለሦስት ቀናት ነበር:: ከዚያ በኢሜይል እየተገናኘን ሀሳቦችን ስናዳብር ከቆየን በኋላ በየወሩ እየተገናኘን ስንሰራ ቆየን፡፡ በየስብሰባው ካሜራ አይገባም:: ሰው በነፃነት የሚሰማውን እንዲገልጽ ቀረጻ የሚባል አልተከናወነም፡፡ በዚህ ሂደት ነው እንግዲህ ለመተያየት የማይፈቅዱ ሰዎች እንኳን  እየተላመዱ፣ እንደ ቤተሰብ እየተነፋፈቁ መገናኘት የጀመሩት ይሄ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በየቡድን ስራዎቹም ላይ ሆነ ተብሎ የሀሳብና የአላማ ፍፁም ተቃርኖና ልዩነት ያላቸውን ፓርቲ መሪዎች አንድ ላይ በመደልደል እንዲነጋገሩ እንዲከራከሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ብዙ ጓደኝነት፣ ወንድማማችነት ተፈጥሯል::
እንደ ጠላት የሚተያዩ ሰዎች ተቀራርበው ጽንፍ የረገጠ ተቃርኗቸው የረገበበት፣ አንዱ የአንዱ ጠላት ሳይሆን አጋዥ እንደሆነ የታየበት፣ የመገንጠል ሀሳባቸውን በግልጽ ያንፀባርቁ የነበሩ ሰዎች ያንን ሀሳብ የቀየሩበት… በአጠቃላይ ለአንዲት ኢትዮጵያ ሲባል ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ ግን አገር ከመፍረስ እንድትድን እንምከር ብለው ወንድማማቾች የተሰባሰቡበት ስለሆነ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት ተስፋ በውስጤ አድሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም ጠባቂ አምላክ እንዳላት ማመን ችያለሁ፡፡

Read 1834 times